ከፍተኛ ጭንቀት ምንድን ነው? ምን ያክልስ ያሳስባል?

የተጨነቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Vladimir Vladimirov

ሁሉም ሰው ላይ የሚከሰቱና ተፈጥሮአዊ የሆኑ ጭንቀቶች አሉ። ይህን መሰል ጭንቀቶች ጤናማና ሰዎች የተሻለ ነገር እንዲያስቡ አልያም የፈጠራ ችሎታቸው እንዲጨምር ሊያደርግ የሚችል ነው።

ለምሳሌ አንድ ተማሪ ፈተና በቀረበ ጊዜ እንዳልወድቅ ብሎ መጨነቁ ተገቢና ጠንክሮ እንዲያጠና የሚያደርገው ነው።

ጤናማ የሆነ ጭንቀት ከባድ የምንላቸው የትምህርትም ሆነ የሕይወት ፈተናዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ የተሻሉ መንገዶችን ሊያሳዩን ይችላሉ።

በሌላ በኩል ግን አንድ ተማሪ ፈተናውን ልወድቅ እችላለሁ ብሎ ከመጨነቁ የተነሳ ማጥናት እስኪያቅተው ድረስ ከሆነ ይህ ከባድ የጭንቀት ሕመም (Free Floating Anxiety) ሊባል ይችላል።

ጭንቀት ከተፈጥሮአዊው መንገድ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ሲከሰትና ሌላ ነገር ላይ ማተኮር እስኪያቅተን ድረስ ከሆነ እንደ አንድ የአእምሮ ህመም ሊቆጠር ይችላል።

ከባድ ጭንቀት ዋነኛ መንስኤዎቹ እና ምልክቶቹ ምንድናቸው? በህክምናስ መዳን ይችላል ስንል በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ አእምሮ ህክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኤሊያስ ገብሩን አነጋግረናል።

ዶክተር ኤሊያስ እንደሚያስረዱት ከባድ ጭንቀት በዋነኛነት የወደፊቱን ነገር ካለማወቃችን ጋር ተያይዞ ምን ይፈጠር ይሆን? እያልን የምንጨነቀው ነው።

''በአንድ ጊዜ ስለብዙ ነገሮች አብዝቶ መጨነቅ፤ ነገን እንዴት ነው የምሆነው? ብሎ ሌሎች ስራዎችን ትቶ ቁጭ ብሎ ማሰብና ሕይወታችንን እስከማወክ ሊደርስ ይችላል'' ይላሉ።

ከዚህ የአእምሮ ህመም ጋር ተያይዞ ደግሞ አብረው የሚመጡ አካላዊ ምልክቶች አሉ። ከነዚህም መካከል በጣም መድከምና እረፍት ማጣት፣ መቁነጥነጥ፣ ከሀሳብ ብዛት የተነሳ እንቅልፍ ማጣትና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋነኞቹ ምልክቶች እንደሆኑ ዶክተር ኤሊያስ ያስረዳሉ።

የጭንቀት ህመሙ ከዚህም በላይ ከፍ ሲል ደግሞ የልብ ምት መፍጠን፣ መንቀጥቀጥ፣ ማላብ፣ ራስን ሊስቱ እንደሆነ ማሰብና እንዳንዴም እራስን መሳት ይስተዋላሉ።

እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በሰዎች የስራ ሕይወት፣ ትምህርት፣ የፍቅር ግንኙነት እንዲሁም ከቤተሰብና ጓደኞች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በእጅጉ ያበላሸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ ጭንቀትና ከባድ ድብርት አብዛኛውን ጊዜ ተያይዘው የሚመጡ ነገሮች ናቸው።

ከፍተኛ ድብርት በእንግሊዝኛው Depression የሚባለው የአዕምሮ በሽታ ሲሆን ብዙ ጊዜ በዘር ከሚተላለፈው የድብርት ሕመም በተጨማሪ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ከባድ ሀዘን፣ የሰውነታችንን ተፈጥሮአዊ አሰራር የሚረብሹ ሕመሞች፣ የአእምሮ ሰላምን የሚነሱ እንደ አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን የመሳሰሉ ጉዳቶች፣ እንዲሁም በአንድም ሆነ በሌለ መንገድ እራስን ከማህበረሰቡ በማግለል ሊከሰት ይችላል።

''እነዚህን የአእምሮ ህመሞች ከባድ የሚያደርጋቸው አንድ ሕመም ብቻ አለመሆናቸው ነው። በውስጣቸው በርካታ አይነት የአእምሮ ህመሞችን አብረው ይዘው ይመጣሉ።

ስለ አእምሮ ህመሞች በቂ የሆነ እውቀት በሌለው ማህበረሰብ ውስጥ ሲከሰቱ ደግሞ ጉዳታቸው ከፍተኛ ነው። የሁለቱ ህመሞች ጥምረት ብዙ ጊዜ ታማሚዎችን እራሳቸውን ወደ ማጥፋት ነው የሚመሯቸው''

የተጨነቀ ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Colin Hawkins

ከፍተኛ ጭንቀትን እንዴት ማከም ይቻላል?

ከባድ ጭንቀት ልክ እንደ ማንኛውም አይነት አካላዊ ሕመም መታከም የሚችል የአእምሮ ህመም ነው።

ይህንን ህመም በሁለት አይነት መልኩ ማከም የሚቻል ሲሆን የመጀመሪያው የስነ ልቦና ህክምና ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሚዋጡ መድሀኒቶች የሚደረግ ህክምና እንደሆነ ዶክተር ኤሊያስ ነግረውናል።

''የስነ ልቦና ህክምና በራሱ በጣም ሰፊና በርካታ አይነት አማራጮች ያሉት ነው። ከሀኪሙ ጋር ቁጭ ብሎ በማውራትና በመመካከር እንዲሁም የተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመጠቀም ማከም ይቻላል።

የክኒን ህክምናውም ቢሆን ብዙ አይነት አለው። ለምሳሌ ፈተና ሊገቡ ሲሉ በጣም ለሚጨነቁ ሰዎች የሚሆን መድሀኒት አለ። ለረጅም ጊዜ የሚወሰዱም ሲኖሩ ጭንቀቱ ሲያጋጥመን ብቻ የምንወስዳቸውም አሉ'' ይላሉ።

ለመሆኑ ምን ያክሉ የማህበረሰባችን ክፍል ይህንን የአእምሮ እክል እንደ አንድ ሕመም ተቀብሎ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህክምና ያገኛል ስንል ለዶክተር ኤሊያስ ጥያቄ ሰነዘርንላቸው።

''እኛ ጋር ብዙ ጊዜ የሚመጡት ህመሙ ከአቅም በላይ የሆነባቸው ናቸው። እነሱም ቢሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። በዛው ልክ ግን አንዳንዴ ደግሞ ሕመሙን አውቀውት ችግሩ ከመባባሱ በፊት ቀድመው የሚመጡ ሰዎች አሉ። ቁጥራቸው ግን ብዙ አይደለም''

ከባድ የጭንቀት ሕመም እንደ ከባድ ድብርት ባይሆንም ብዙ ሰዎች በተለይ ከስነ እእምሮ ጤና ባለሙያ ጋር በመነጋገርና ምክር በመውሰድ አንዳንዴም መድሀኒቶችን በመውሰድ እንደሚታከሙ ዶክተር ኤልያስ ይገልጻሉ።

አክለውም ህመሙ እንደምናስበው ቀላልና ጥቂት ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃ እንዳልሆነ ያሳስባሉ።

''በዚህ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም። ማህበረሰቡ ስለ ህመሙ ብዙ እውቀት ስለሌለውና የተሳሳቱ አመለካከቶች ስላሉ፤ በርካታ ታማሚዎች በግልጽ ችግራቸውን ስለማይናገሩ ነው እንጂ ጥቂት የማይባል የማህበረሰባችን ክፍል የዝቅተኛም ሆነ ከፍተኛ ጭንቀት ህመም ተጠቂ ነው''

የአእምሮ ህመምና የማህበረሰቡ አመለካከት

ታማሚው ችግሩን ቢያውቀው እንኳን የማህበረሰቡን አስተያየት ፍራቻ በግልጽ አይናገርም። ይህ ጉዳይ በቤተሰብም ሆነ በጓደኛሞች ደረጃ የሚወራ አይደለም።

ሌላው ቀርቶ አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ህመም ተጠቂዎች ራሳቸው የዚህ ህመም ተጠቂ እንደሆኑ ለማወቅ ብዙ ጊዜ ይፈጅባቸዋል፤ አልያም ከነጭራሹ አያውቁትም።

''እዚህ ላይ ማህበረሰቡን ለማንቃት ትልቅ ስራ ይጠበቃል። መንግሥት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ስራዬ ብለው የአእምሮ ህመሞች ልክ እንደ ማንኛውም አካላዊ ህመም ማንኛውም አይነት ሰው ላይ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሊያስተምሩ ይገባል''

''በሌላ በኩል ሰዎች መሰል የአእምሮ ጤና መቃወስ ሲያጋጥማቸው ለሰው ሳይናገሩ በራሴ እወጣዋለሁ እያሉ ይታገላሉ። እባካችሁ ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ አትፍሩ፤ ለምንድነው ብቻችሁን የምትሰቃዩት? ለምንድነው ብቻችሁን እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን የምታሳልፉት? በዘርፉ ብዙ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ሊረዷችሁ ይችላሉ'' በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ዶክተር ኤልያስ።

እንደ ምሳሌም አንድ ሰው በስኳር በሽታ ሲጠቃ በራሴ እወጣዋለሁ ብሎ ቤት ውስጥ ሳይደበቅ ቶሎ ወደ የህክምና ተቋማት ሄዶ መድሀኒት እንደሚወስደው ሁሉ የአእምሮ ህመምም ተመሳሳይ እንደሆነና በጤና ተቋማት እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ይጠቅሳሉ።

ሰዎች ዋናውን ህክምና ሳያደርጉ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግና ከሰዎች ጋር ያላቸውን ትስስር በመጨመር ብቻ መሰል ህመሞችን ማዳን አይችሉም።

በስኳር በሽታ የሚሰቃይ ሰው ሀኪም መድሀኒት አዞለት እየዋጠ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግና አመጋገቡን ቢያስተካክል ጤናው በቶሎ ይመለሳል።

''የአእምሮ ህመምም እንደዛው ነው። በሰዎች ተከበውም በጭንቀት የሚሰቃዩ ሰዎች አሉ። አካላዊ እንቅስቃሴ እያደረጉም አመጋገባቸው የማይስተካከልና እንቅልፍ አልባ ምሽቶችን የሚያሳልፉ ብዙ ናቸው። ስለዚህ ሰዎች መሰል ችግር ሲያጋጥማቸው በቶሎ ሳይባባስ በፊት ህክምና ማግኘት አለባቸው። ከህክምናው ጋር ጎን ለጎን ደግሞ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አመጋገብን ማስተካከልና ከሰዎች ጋር መገናኘት ጠቃሚ ናቸው'' ሲሉም ያስረዳሉ።

በመጨረሻም ዶክተር ኤልያስ ማህበረሰባችን የአእምሮ ህመምን ልክ እንደ ማንኛውም ህመም ሊያየው እንደሚገባና ሰዎች ምልክቶቹን ሲያሳዩ በቶሎ ባለሙያ ማናገር እንዳለባቸው ያሳስባሉ።