ተመራማሪዎች ጭንቀት ለምን ሽበትን እንደሚያስከትል ደርሰንበታል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተመራማሪዎች የሰዎችን ጸጉር ነጭ የሚያደርገው ወይም እንዲሸብት የሚያደርገው ጭንቀት መሆኑን ደርሰንበታል፤ ሽበትን ማስቆም የሚያስችል መፍትሄም ይዘን ብቅ ብለናል እያሉ ነው።
ባለሙያዎቹ የሰሩት ይህ ምርምር በአይጦች ላይ ተሞክሯል ተብሏል። አይጦቹ ከባድ ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ሲደረጉ የቆዳ እና የጸጉር ቀለምን የሚቆጣጠረው ሴል ጉዳት ደርሶበታል።
ጸጉሩ ጠቆር ያለ አንድ አይጥ ይህ ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በሳምንታት ውስጥ የጸጉሩ ቀለም ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት ተቀይሯል።
የአሜሪካ እና ብራዚል ተመራማሪዎች በጥምረት በሰሩት ምርምር ላይ የጸጉር ቀለም እንዳይለወጥና እንዳያረጅ የሚያደርግ መድኃኒት ለማዘጋጀት የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎች እንደተገኙ አስታውቀዋል።
ተመራማሪዎቹ ወንዶችም ሆነ ሴቶች በአማካይ ከ30ዎቹ አጋማሽ አካባቢና በኋላ ጸጉራቸው መሸበት ይጀምራል ያሉ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያትነት ያስቀመጡት ልጆችን ማሳደግ የመሳሰሉ አስጨናቂ ነገሮች ናቸው።
ምንም እንኳን ተፈጥሯዊው የማርጀት ሂደትና የዘረመል አሰራር የጸጉር ቀለምን የመለወጥ ኃይል ቢኖራቸውም፣ ጭንቀት በራሱ ግን ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንደሚያደርስ ተረድተናል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።
ነገር ግን አሁንም ተመራማሪዎቹ ጭንቀት እንዴት ባለ መልኩ ጭንቅላታችን ላይ የሚገኝ ጸጉርን ቀለም እንደሚቀይር አልደረስንበትም ብለዋል።
ጭንቀትን ከጸጉር መሸበት ጋር ለማያያዝ ተመራማሪዎቹ ከሙሉ የሰውነት ለውጦች ተነስተው ወደ ግለሰብ የሰውነት አካላት፣ ሴሎችና የተለያዩ ሂደቶችን በማጥናት በመጨረሻ የሚያገናኛቸውን ቦታ መለየት ችለዋል።
ይህንንም የጥናት መንገድ ጭንቀት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚያመጣውን ለውጦች ለማጥናት እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ።
'ኔቸር' መጽሔት ላይ በታተመው በዚህ የምርመር ወረቀት ላይ ከሳኦ ፖሎ እና ከሃርቨርድ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።
ተመራማሪዎቹ ይህንን ምርምራቸውን በአይጦች ላይ በሚያከናውኑበት ጊዜ ጭንቀት የጸጉር ቀለም ለውጥ ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው አስተውለዋል።
"አሁን ላይ በእርግጠኝነት ጭንቀት የጸጉር ቀለም ለውጥ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ደርሰንበታል" ይላሉ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያ ሲዬህ ህሱ።

የፎቶው ባለመብት, WILLIAM A GONCALVES
በሙከራው ላይ አይጦቹ ሕመም እንዲሰማቸው ሲደረጉ ሰውነታቸውን 'አድሬናሊን' የተባለው ኬሚካል ያመነጫል። በዚህ ጊዜ ደግሞ ልባቸው በፍጥነት መምታት ይጀምራል፤ የደም ግፊታቸው ይጨምራል፤ የነርቭ ሥርዓታቸውም ይዛባል፤ ታዲያ ይሄኔ አይጦቹ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ።
ይህ ሂደት ደግሞ ሜላኒን የተባለውን ንጥረ ነገር የሚያመነጩት ሴሎች ከባድ ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደርጋል።
"ጭንቀት በሰውነታችን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ቀድሞም አውቃለሁ። ነገር ግን ተጽዕኖው በዚህ ደረጃ የጸጉር ቀለም እስከመቀየር ይሆናል ብዬ ከገመትኩት በላይ ሆኖ ነው ያገኘሁት" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
"ከጥቂት ቀናት በኋላ የጸጉር ቀለምን የሚቆጣጠሩት ሴሎች ተጎድተውና መንሰራራት አቅቷቸው ተመልክተናል። እነዚህ ሴሎች አንድ ጊዜ ከጠፉ በኋላ ተመልሰው አያድጉም፤ ጉዳቱ ዘላቂ ነው።"
በሌላ የምርምር ሥራ ደግሞ ተመራማሪዎቹ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነገር አግኝተናል እያሉ ነው። በሙከራው ላይ ተመራማሪዎቹ አይጦቹን ከባድ ጭንቀት ውስጥ ካስገቧቸው በኋላ ለደም ግፊት ህክምና የሚውለውን 'አንቲ ሃይፐርቴንሲቭ' የተባለውን መድኃኒት ሰጥተዋቸዋል።
መድኃኒቱ የተሰጣቸውና ያልተሰጣቸውን አይጦች ሲነጻጽሩ ከፍተኛ ልዩነት ተስተውሏል። መድኃኒቱ የጸጉር ቀለም የሚቆጣጠሩት ሴሎች ከባድ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና እንዳይሞቱ ከለላ ሆኗቸዋል።
በዚህም ምክንያት መድኃኒቱ የተሰጣቸው አይጦች የጸጉር ቀለማቸው ካልተሰጣቸው አንጻር በተሻለ ደረጃ ላይ ተገኝቷል።
ይህ ግኝት ተመራማሪዎች ከዚህ በኋላ የጸጉር ቀለም ለውጥን ለመከላከል በሚያደርጓቸው ሙከራዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና ሌሎች በሮችን እንደሚከፍትላቸው ተገምቷል።
"እነዚህ ግኝቶች ለጸጉር መሸበት ህክምና አይደሉም። ነገር ግን በአይጦች ላይ በሰራነው ሙከራ መሰረት ከዚህ በኋላ በየትኛው መንገድ ብንሄድ ውጤታማ እንደምንሆን ትልቅ መረጃ ይሰጠናል" ይላሉ ፕሮፌሰር ያ ሲዬህ።
"በተጨማሪም ጭንቀት እንዴት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ መረጃ ይሰጠናል።"












