ከፍተኛ ድብርት ምንድን ነው? ምን ያህልስ አሳሳቢ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዮናስ (ስሙ ተቀይሯል) ባጋጠመው ከፍተኛ የድብርት ሕመም ምክንያት ራሱን ለማጥፋት እስከ ማሰብ ደርሶ ነበር።
''ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ከዩኒቨርሲቲ የተመረቅኩት። ስራ እንደማገኝና ቶሎ ብዬ ቤተሰቤን መርዳት እንደምጀምር ነበር የማስበው። ነገር ግን ያላሰብኳቸው በርካታ ነገሮች ተፈጠሩ። ስራም አላገኘሁም፤ የኮሮናቫይረስም ብዙ እቅዶቼን አመሰቃቀለብኝ።'' ይላል።
ዮናስ ይህንን ተከትሎ ቀስ በቀስ ድብርት ውስጥ መግባት ጀመረ። ቤት ውስጥ መቀመጥና ከሰዎች ጋር መገናኘት አስጠላው።
''ቤተሰቦቼ ሁሌም ቤት ውስጥ ሲያዩኝ 'ለምን ስራ ፈልጎ ውጪ አይውልም' እያሉ የሚያስቡ ይመስለኛል። አብዛኛዎቹ ጓደኞቼ ስራ ማግኘታቸው ደግሞ ይበልጥ እንድጨነቅና ድብርት ውስጥ እንድገባ አደረገኝ'' ይላል ዮናስ።
እዚህ ጋር ግን ዮናስ በወቅቱ ድብርት ውስጥ እንደገባና የአእምሮው ጤና እንደተዛባ አላወቀም ነበር። ቤተሰቦቹም ቢሆኑ እንደዚያው።
ድብርት ልክ እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም ስኳር፣ የኩላሊት ህመም አልያም ወባ አይነት የአዕምሮ በሽታ ሲሆን፤ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችልና ተገቢው ህክምና ከተደረገለት መዳን የሚችል በሽታ ነው።
ይህ ሕመም ከሰዎች ጋር አብሮ ለረዥም ጊዜ የሚኖርና ከባድ የሆነ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የአዕምሮ በሽታ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት በአገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ጉዳት ከሚያደርሱ እንደ ስኳር ካሉ በሽታዎች መካከልም አስቀምጦታል።
በተለይ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ ድብርት እንደተሰቃዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የድብርት መንስኤዎች
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የስነ አእምሮ ህክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ኤሊያስ ገብሩ እንደሚያስረዱት በዘር ከሚተላለፈው የድብርት ሕመም በተጨማሪ ለበሽታው መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።
''የሚወዱትን ሰው በሞት ከማጣት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ከባድ ሀዘን፣ የሰውነታችንን ተፈጥሮአዊ አሰራር የሚረብሹ ሕመሞች፣ የአእምሮ ሰላምን የሚነሱ እንደ አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን የመሳሰሉ ጉዳቶች፣ እንዲሁም በአንድም ሆነ በሌለ መንገድ ራስን ከማህበረሰቡ ማግለል ለከፍተኛ የድብርት ሕመም ሊያጋልጠን ይችላል።''
የገንዘብ እጥረትን የመሳሰሉና ሌሎች ማህበረሰባዊ ጫናዎችም ለከፍተኛ ድብርት ሊያጋልጡን እንደሚችሉ ዶክተር ኤልያስ ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴቶች ላይ ተለይቶ ከልጅ መውለድ ጋር ተያይዞ በእርግዝና ወቅት አልያም ከወሊድ በኋላ ድብርት ሊያጋጥም ይችላል።
የአካል ጉዳተኞች እና ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
የድብርት ምልክቶች
ምንም እንኳን የከፍተኛ ድብርት ምልክቶች ከታማሚ ታማሚ፣ በጾታ፣ በእድሜ እንዲሁም ካሉበት ማህበረሰብ አንጻር የሚለያዩ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን በብዙ ሰዎች የሚስተዋሉ ተመሳሳይ ምልክቶች አሉ፡፡
''ዛሬ መጥቶ ነገ የሚሄድ ሳይሆን ለተከታታይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ የድብርት ስሜት፣ መሪር የሆነ ሀዘንና ለሁሉም ነገር ፍላጎት ማጣት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው''
ከእነዚህ ምልክቶች በተጨማሪ ከዚህ በፊት ከእንቅልፋችን ተነስተን ስናደርጋቸው ጥሩ ስሜት ይፈጥሩልን የነበሩ ነገሮች ደስታን መስጠት ማቆም ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹ ሊያስጠሉን እንደሚችሉ ዶክተር ኤልያስ ያስረዳሉ።
ምክንያት የሌለው ጭንቀት፣ የባዶነት ስሜት፣ ደጋግሞ ራስን መውቀስ፣ 'ምንም የማልጠቅም ሰው ነኝ' እያሉ ማሰብ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የሚረዳኝ ሰው የለም ብሎ ማሰብ፣ ከባድ ድካምና አቅም ማጣት፣ የእንቅልፍ መዛባት (በጣም መተኛት አልያም እንቅልፍ ማጣት)፣ ስራና የግል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማጣት እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው።
ዮናስ በበኩሉ ድብርት ሲጀምረው የነበሩትን ምልክቶች ሲያስረዳ ''መጀመሪያ አካባቢ በጣም እንቅልፍ አበዛ ነበር። እናቴ ሁሌም ከአልጋ እንድወርድና ከቤት ወጣ እንድል ትነግረኝ ነበር። እኔ ግን ያው ትንሽ ደብሮኛል፤ መውጣት አልፈልግም የሚል መልስ ነበር የምሰጣት''ይላል።
በእንቅልፍ ማብዛት የጀመረው የዮናስ የአእምሮ መታወክ ቀስ በቀስ ወደ እንቅልፍ ማጣት ተቀየረ። ቀኑን ሙሉ ውጪ ውሎ፤ ደክሞት እንኳን ማታ ላይ እንቅልፍ መተኛት አስቸጋሪ እየሆነበት መጣ።
ከእንቅልፍ በተጨማሪ የምግብ ፍላጎቱ በእጅጉ መቀነሱን ተከትሎ የሰውነት ክብደቱም አብሮ መቀነስ ጀመረ።
''ሰዎች ሲያዩኝ ይደነግጣሉ። ምን ሆነህ ነው የከሳሀው ይሉኛል። በሽታ ይዞኝ ነው የሚመስላቸው። በውስጤ ያለውን ግን ማንም አያውቅልኝም ነበር። ሌላው ቀርቶ እኔ ራሱ ምን እንደሆንኩኝ አላውቅም ነበር።
ዶክተር ኤሊያስ እንደሚሉት በማህበረሰባችን ውስጥ በተለይም የአእምሮ ጤና ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ተከትሎ ቀላልና ጤናማ ድብርትን ለከፍተኛ የስነ አእምሮ ጉዳት ከሚያጋልጥ ድብርት ለይቶ ያለማየት ችግር አለ።
''በዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሌላ ጊዜው በተለየ መልኩ ደብሯቸው ስንመለከት ወይንም ራሳቸው ደብሮኛል ብለው ሲናገሩ በቀላሉ አይተን ማለፍ የለብንም። ተገቢውን ድጋፍና ሕክምና እንዲያገኙ ማበረታታት አለብን። አለበለዚያ እነዚህ ሰዎች በጊዜ ብዛት እራሳቸውን ወደ መጥላትና ራስን እስከ ማጥፋት ሊደርሱ ይችላሉ''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድብርት በኢትዮጵያ
ዶክተር ኤሊያስ እንደሚሉት በኢትዮጵኣ ውስጥ በስነ አእምሮ ጤና ዙሪያ ከፍተኛ ስራ ይጠበቃል። በቂ የሆነ ጥናት አለመደረጉ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ዝቅተኛ ግንዛቤ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ይላሉ።
''በቂ በሚባሉና በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያስችሉ ጥናቶች አልተሰሩም። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች ላይ ከ7 እስከ 20 በመቶ ድረስ የጥናቱ ተሳታፊዎች በስነ አእምሮ ሕመም ተጠቂ እንደሆኑ ይጠቁማሉ።''
ነገር ግን እነዚህ ጥናቶች አጠቃላይ የተማሪዎችን ሁኔታም ሆነ አገሪቱ ያለችበትን ደረጃ መግለጽ የሚችሉ እንዳልሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶክተር ኤሊያስ ያሳስባሉ።
ሌላኛው ዶክተር ኤሊያስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት ጉዳይ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ነው።
''የአእምሮ ሕመም ልክ እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም ማንም ላይ ሊከሰት የሚችል ነው። ጾታ፣ ዘር፣ ሐይማኖት፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም የሚያጠቃ ነው። ማህበረሰቡ ይህንን መረዳት አለበት። መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ላይ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ማህበረሰቡን ስለ አእምሮ ጤና ማስተማር ወደፊት ለሚገጥሙን በርካታ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል።''
በድብርት ሕመም የሚሰቃየው ግለሰብም ሆነ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ችግሩን በትክክል መለየት እስካልቻሉ ድረስ ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አይችልም። ዮናስም ያጋጠመው ይኸው ነው።
ማንም የቤተሰቡ አባልም ሆነ ጓደኞቹ የአእምሮ ጤናው ታውኮ ሊሆን እንደሚችል አልገመተም። በዚህም ምክንያት ዮናስ ከሕመሙ በበለጠ ሕመሙን የሚረዳለት ሰው በማጣቱ ለበርካታ ወራት ብቻውን ተሰቃይቷል።
ነገር ግን በአንድ ወቅት በጓደኛው በኩል ያገኘው ሰው ነገሮች እንዲቀየሩ አድርጎለታል።
''ሁኔታዬን አይቶ 'አንተ ልጅ ግን ልክ አይደለህም' አለኝ። ምነው ስለው፤ 'ድብርት ውስጥ የገባ ሰው ትመስላለህ፤ ለምን ባለሙያ አታናግርም' ሲለኝ በጣም ነበር የደነገጥኩት። እንዴት እንዲህ ትለኛለህ ብየ ተናድጄ ሄድኩኝ። አብደሀል ያለኝ ነበር የመሰለኝ።''
ዮናስ ያን ምሽት ቀን ላይ የሰማውን ነገር ሲያብሰለስል አደረ። በጠዋት ተነስቶ ምልክቶቹን እና ያለበት ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ በስልኩ ኢንተርኔት ላይ መረጃዎችን ማጣራት ጀመረ። ከሞላ ጎደልም ቢሆን የድብርት ተጠቂ እንደሆነ ተረዳ።
ነገር ግን የአእምሮ ጤና ባለሙያ ጋር ለመሄድ አልደፈረም። ለቤተሰቦቹም አልተናገረም።
ዶክተር ኤሊያስ እንደሚሉት የድብርት በሽታ ከቀላል እስከ ከባድ የሚባሉ ደረጃዎች አሉት።
''ሰዎች የድብርት ምልክቶችን ሲያሳዩ ቤተሰብም ሆነ ጓደኞች 'አታካብድ፣ ቀለል አድርገህ እየው፣ ብዙም አያሳስብም' የሚሉ ከሆነ በሽታው አብሮ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። ህመሙ ተገቢውን ሕክምና ሳያገኝ በቆየ ቁጥር ደግሞ ልክ እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም በታማሚው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረና በጤና ተቋማት የሚሰጠውን ሕክምናም ከባድ እያደረገው ይሄዳል።''
ለከፍተኛ ድብርት ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል በተለይ እድሜያቸው በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች፣ አስገድዶ መደፈርን የመሳሰሉ ትልቅ አእምሮአዊ ጫና የሚያስከትሉ ጥቃቶች ያጋጠሟቸው ሰዎች፣ የጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ እንዲሁም ወጣቶች ይጠቀሳሉ።
ድብርትና ሕክምናው
ዮናስ ምንም እንኳን ባለሙያ ጋር ሄዶ ክትትል ለማድረግ ድፍረቱ ባይኖረውም በተቻለው መጠን ነገሮችን ለማስተካከል እየሞከረ ነው። አካላዊ እንቅስቃሴ ያሰራል። ምግቡን ተከታትሎ መመገብ ጀምሯል።
''ድብርት ይዞኛል ብዬ ሀኪም ቤት ብሄድ ቤተሰቦቼ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አላውቅም። እናቴ በተለይ በጣም ስለምትወደኝ 'ልጄ አበደ' ብላ የምትጨነቅ ይመስለኛል። ችግሬን ማወቄ በራሱ ብዙ ነገሮች እንዲሻሻሉ አድርጓል። ስለዚህ በተቻለኝ መጠን ነገሮችን መከታተል ጀምሬያለሁ''
ዶክተር ኤሊያስ ድብርት እንደማንኛውም ሕመም የራሱ የሆነ ሕክምና አለው ይላሉ።
አክለውም " መድሀኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለውና በጣም ለባሰ ሕመም ብቻ መወሰድ እንዳለበት በርካቶች ያስባሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። መድሀኒት ሳልወስድ የአኗኗር ዘይቤዬን ብቻ በመቀየር መዳን እችላለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ሕክምናው ግን በጣም ወሳኝ ነው'' ብለዋል።
ከባድ የሆነ የድብርት ሕመም ሲኖር ብዙ አይነት የሕክምና አማራጮች እንዳሉ ዶክተር ኤሊያስ ያስረዳሉ።
የመጀመሪያው የህክምና ማዕከል ውስጥ አልጋ ይዞ ለረጅም ጊዜ መታከም ነው። በጣም ከባድ የሚባለው ደረጃ ላይ ያልደረሱት ደግሞ በተመላላሽ ሕክምና በክኒንም ሆነ የስነ ልቦና ምክር በመስጠት ሕክምና እንዲያገኙ እንደሚደረግ ዶክተር ኤሊያስ ያስረዳሉ።


















