የዓለማችን 'ጭንቀታም' እና 'ደስተኛ' ሃገራት ደረጃ ይፋ ሆነ

ጭንቀታም ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጆች ተናዳጅ፣ ድብርታም እና ጭንቀታም እየሆኑ መምጣታቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከናወን ጥናት አመለከተ።

በ140 ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ 150 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ድብርት እየተጫናቸው እንደመጣ የተናገሩ ሲሆን፤ ቢያንስ ከአምስቱ በአንዱ የሃዘን እና የብስጭት ስሜት ተመዝግቧል።

ዓመታዊው ጋሉፕ ዓለም አቀፍ የውስጣዊ ስሜት ሪፖርት (Gallup Global Emotions Report) ሰዎችን አዎንታዊ እና አሉታዊ ልምዶቻቸውን ጠይቋል።

ከተጠየቁት ሰዎች መካከል በብዛት አሉታዊ ምላሾቹን የሰጡት የቻድ እና የኒጄር ዜጎች ናቸው። ሪፖርቱ እንደሚለው አዎንታዊ ምላሽ የሰጡት ደግሞ የፓራጓይ ዜጎች ናቸው።

ጥናት አድራጊዎቹ መጠይቁን ካደረጉበት አንድ ቀን በፊት ስለነበራቸው ቀን ነበር ለተሳታፊዎቹ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት።

ለተሳታፊዎች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ''ትናንት ፈገግ ብለው ነበር? ወይም በጣም ስቀው ነበር?'' እንዲሁም ''ትናንት የሚገባዎትን ክብርን አግኝተዋል?'' የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል።

71 በመቶ የሚሆኑት ጥናቱ ከተካሄደበት ቀን በፊት ከፍ ያለ የደስታ ስሜት ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል። 39 በመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ቀን በፊት የጭንቀት ስሜት እንደተሰማቸው እንዲሁም 35 በመቶ ደግሞ ድብርት ተሰምቶናል ብለዋል። የጥናት ውጤቱ እንዳመለከተው የጭንቀት መጠን ከፍ ብሏል።

አዎንታዊ ውጤትን ስመዘገቡ ቀዳሚ 5 ሃገራት

  • ፓራጓይ
  • ፓናማ
  • ጓቲማላ
  • ሜክሲኮ
  • ኤል ሳልቫዶር

አሉታዊ ውትን ያስመዘገቡ ቀዳሚ 5 ሃገራት

  • ቻድ
  • ኒጀር
  • ሴራሊዮን
  • ኢራቅ
  • ኢራን

''በየቀኑ በአዎታዊ ስሜት እንሞላለን'' ሲሉ የላቲን አሜሪካ ሃገራቱ ፓራጓይ፣ ፓናማ እና ጓቲማል ዜጎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በተቃራኒው የአፍሪካዊቷ ሃገር ቻድ ዜጎች ደግሞ "አሉታዊ ስሜት በየዕለት ኑሯችን ይገጥመናል" ብለዋል። ከ10 የቻድ ዜጎች 7ቱ ባለፈው ዓመት ቢያንስ በአንድ ወቅት ላይ የሚበሉት አጥሯቸው እንደነበርም ተናግረዋል።

61 በመቶ የሚሆኑት ቻዳውያን ደግሞ አካላዊ ህመም አለብን ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።