ጀርመን የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ለዩክሬን ታንኮች ልትልክ ነው

ጀርመን ሰራሽ የሆኑ 50 ጌፓርድ ፍላክፓንዘር ታንኮች ለዩክሬን ይላካሉ።

የፎቶው ባለመብት, Hans-Hermann Bühling

የምስሉ መግለጫ, ጀርመን ሰራሽ የሆኑ 50 ጌፓርድ ፍላክፓንዘር ታንኮች ለዩክሬን ይላካሉ።

ጀርመን የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ አየር መቃወሚያ ታንኮችን ለዩክሬን ልትልክ ነው።

የጀርመን መንግሥት ከባድ ጦር መሳሪያዎችን ወደ ጦር ቀጠና ያለመላክ ጠንካራ ፖሊሲ ነበረው። ይሁን እንጂ የጀርመን መንግሥት ከምዕራባውያን አገራት ከፍተኛ ጫና በኋላ ለዩክሬን ጸረ አውሮፕላን ታንኮችን ለመላክ ወስኗል።

ጀርመን ሰራሽ የሆኑ 50 ጌፓርድ ፍላክፓንዘር ታንኮች የቴክኒክ ማሻሻያዎች ተደርጎላቸው ወደ ዩክሬን ይላካሉ ተብሏል።

ጀርመን የፖሊሲ ለውጥ አድርጋ ከባድ መሳሪያዎቹን ለዩክሬን እንደምትልክ የተገለጸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በአሜሪካ የጦር ሰፍር ለስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት ነው።

የዚህ ስብሰባ አጀንዳ ለዩክሬን ሊቀርብ የሚችል ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ምዕራባውያን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን አድርገዋል።

ከጀርመን በተጨማሪ ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን ጸረ አውሮፕላን የሆኑ አንስተኛ ቁጥር ያላቸው ተሸከርካሪዎችን እንደምትሰጥ ተገልጿል።

የጀርመን መንግሥት ውሳኔን ይፋ ያደረጉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ክርስቲን ላምበርት፤ "ዩክሬናውያን ለነጻነት እና ለሰላም የሚያደርጉትን ቁርጠኛ ትግል መደገፍ የምንችልባቸውን አማራጮች በሙሉ እያጤንን ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጀምስ ሄፒ የዩክሬን ወታደሮች የምዕራባውያን ጦር መሳሪያዎችን ተጠቅመው በሩሲያ ያሉ የሩሲያን ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ቢያደርጉ ተቀባይነት ያላው ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዩክሬን ጥቃት እንድትሰነዝርብኝ ዩናይትድ ኪንግደም ግፊት እያደረገች ነው የሚል ቅሬታ ከሞስኮ ከተሰማ በኋላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፤ ኔቶ የእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ ገብቷል የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ሰርጌይ ላቭሮቭ ምዕራባውያኑ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ "በእሳት ላይ ነዳጅ እያርከፈከፉ ነው" ሲሉ ትናንት ሰኞ ሚያዚያ 17/2014 ዓ.ም. ተናግረዋል።