የአየር ንብረት ለውጥ ለወባ በሽታ ሊያጋልጥዎ ይችላል?

የወባ ትንኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በየዓመቱ ከ240 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ እንደሚያዙ ያውቃሉ? በ60 አገራት በየዓመቱ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ምክንያት እንደሚሞቱስ ምን ያህሎቻችን እናውቃለን?

የዓለም የወባ ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 17 ይከበራል።

የዘንድሮው የወባ ቀን የታሰበው ከሁለት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው። አንደኛው የዓለም ጤና ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና የሰጠው የወባ ክትባት ይፋ መደረጉ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የሙቀት መጨመር በሽታውን በላቀ ደረጃ ያስፋፋዋል የሚለው ስጋት።

በአንድ በኩል ክትባቱ ተስፋ ሲሰጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ስጋት አጭሯል።

ሙቀት ሲጨምር የወባ ትንኞች በብዛት ይራባሉ

ዶ/ር ኢዛቤል ፍሌቸር ዌልካም ትረስት በተባለ ድርጅት ይሠራሉ። የዓለም ሙቀት መጠን እየጨመረ ሲሄድ የወባ ትንኝ በሽታውን የምታሰራጭበት ፍጥነት ከፍ እንደሚል ይናገራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ የዓለማችን ክፍሎች ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ እንዲሆኑም ያደርጋል ይላሉ።

"አሁን ቀዝቃዛ የሆኑ ከፍታማ ቦታዎች የዓለም ሙቀት ሲጨምር የወባ ትንኝ መራቢያ ይሆናሉ።"

በተባበሩት መንግሥታት ሥር የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያተኩረው ቡድን እንደሚለው፣ የዓለም መንግሥታት በ2020 የካርበን ልቀትን የተስማሙበት ነጥብ ድረስ ቢያወርዱትም እንኳን ዓለማችን በ3.2 ሴንቲ ግሬድ መሞቋ አይቀርም።

የዓለም አገራት ግባቸው የዓለም ሙቀትን 1.5 ሴንቲ ግሬድ ወይም ከዚያ በታች ማድረግ ነበር።

ከዓለም ሙቀት መጨመር ጎን ለጎን እርጥበታማ አካባቢዎች እንዲሁም ድርቅ የወባ ትንኝ ስርጭትን ይጨምራሉ።

በሽታው ከዚህ ቀደም ባልተመዘገበባቸው አካባቢዎች እየታየ የመጣውም ለዚህ ነው።

ዶ/ር ኢዛቤል እንደሚሉት በካረቢያን አገራት እና ብራዚል ድርቅ ሲኖር ሰዎች የሚያከማቹት ውሃ ለወባ ያጋልጣቸዋል።

የወባ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ የበሽታውን ዝውውር ሊቀንስ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለም ተመራማሪዋ ይናገራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥና የወባ ስርጭት ትስስር በጥልቅ መጠናት እንዳለበትም ይጠቁማሉ።

"ጥናቱ የትኞቹ አካባቢዎች ለወባ የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ በማሳየት ለቅድመ ጥንቃቄ ይረዳናል።"

የወባ ምልክቶች

አደገኛው በሽታ ወባ የሚሰራጨው በወባ ትንኝ ነው። ምልክቶቹም እኒህ ናቸው፦

  • የሰውነት ሙቀት መጨመር፣ ላብና መንዘፍዘፍ
  • ራስ ምታትና መወዛገብ
  • ድካምና እንቅልፍ ማብዛት (በተለይም በሕፃናት ዘንድ)
  • የሆድ ሕመምና ተቅማጥ
  • ምግብ የመብላት ፍላጎት ማጣት
  • የጡንቻ ሕመም
  • የቆዳ ቢጫ መሆንና የዐይን መንጣት
  • የጉሮሮ መድረቅ፣ ሳልና ለመተንፈስ መቸገር

የወባ ክትባት የሰጠው ተስፋ

የአየር ንብረት ለውጥ ከወባ በሽታ ጋር የሚደረገውን ትግል ከባድ ያደርገዋል። በሌላ በኩል የተገኘው አርቲኤስኤስ ክትባት ተስፋ ይፈነጥቃል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ አንድ ሚሊዮን ሕፃናት አንዴ ወይም ሁለቴ ክትባቱ ተሰጥቷቸዋል።

የወባ ክትባት የሙከራ ስርጭት የተጀመረው በማላዊ መንግሥት፣ በ2019 ግንቦት ላይ ነው።

ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ሙከራው አሳይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ከሰሀራ በታች ባሉ አገራትና ሌሎችም ለበሽታው በተጋለጡ አካባቢዎች እንዲሰራጭ የፈቀደውም ሙከራውን ተከትሎ ነው።

ድርጅቱ በ2030 የወባ ስርጭትን በ90% የመቀነስ ዕቅድ አለው።

በወባ በሽታ ሳቢያ የሚከሰት ሞትንም በዛው ዓመት 90% ለመቀነስ ወጥኗል።

በ2030 ወባን ከ35 አገሮች የማጥፋትና በሽታው በሚከሰትባቸው አገሮች እንዳያገረሽ ማድረግም ዐቅዷል።

ድርጅቱ እንደሚለው፣ ክትባቱ በየዓመቱ ከ40,000 እስከ 80,000 የሚደርሱ አፍሪካውያን ሕፃናትን ሕይወት ይታደጋል ተብሎ ይታመናል።

የዓለም ጤና ድርጅት የወባ ክትባት ትግበራ መሪ ዶ/ር ሜሪ ሀሜል "ክትባቱ ለሙከራ ከተሰጠ ከሁለት ዓመታት በኋላ እጅግ አስተማማኝ እንደሆነ ተገንዝበናል" ይላሉ።

በወባ ምክንያት በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር የቀነሰው በዚህ ክትባት ምክንያት እንደሆነም ያክላሉ።

አርቲኤስኤስ ከተባለው ክትባት በተጨማሪ አር21/ሜትሪክስኤም የተባለ ተጨማሪ ክትባትም ሙከራ ላይ ይገኛል።

በቂ ክትባት አለ?

ወባ የሰው ልጅን የደም ሕዋስ በመበጣጠስ ራሱን ያባዛል።

አሁን ጥቅም ላይ የዋለው አርቲኤስኤስ ክትባት ኢላማ ያደረግ በአፍሪካ የሚሰራጨው የወባ ፓራሳይት (Plasmodium Falciparum) ላይ ነው።

ይህ ፓራሳይት ደም ውስጥ ከገባ በኋላ ጉበትን ያጠቃል።

ክትባቱ ፓራሳይቱ ጉበትን እንዳይጎዳ ያደርጋል። ይህም ፓራሳይቱ እንዳያድግ፣ እንዳይሰራጭና ቀይ የደም ሕዋስን እንዳያጠቃ ይከላከላል።

ክትባቱ ውጤታማ እንዲሆን አራት ጠብታ መውሰድ ያሻል።

የመጀመሪያዎቹ 3 ጠብታዎች በየአንድ ወር ልዩነት ይወሰዳሉ። የመጨመረሻው ደግሞ ከ18 ወራት በኋላ ይሰጣል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በተለይም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት በዓመት 80 ሚሊዮን ጠብታ የሚፈለግበት ነጥብ ላይ መደረሱ አይቀርም።

ዶ/ር ሜሪ እንደሚሉት፣ የክትባት ፍላጎቱ ከአቅርቦቱ ሊበልጥ ይችላል።

አሁን ላይ ያለው ብቸኛ ክትባት አምራች ግላክሶስሚዝክሊን (ጂኤስኬ) ብቻ ነው።

"የጂኤስኬ ዕቅድ በዓመት 15 ሚሊዮን ጠብታ ማምረት ነው። በከፍተኛ ሁኔታ ለወባ የተጋለጡ ሕፃናትን ለመታደግ ቁርጠኝነትና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ያስፈልጉናል" ይላሉ ዶክተሯ።