ሩሲያ በዩክሬን የባቡር ጣቢያ በአየር ደበደበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ትናንት ሰኞ አንድ የዩክሬን የባቡር ጣቢያን በአየር ደብድባለች፡፡
ይህም ከምዕራባዊያን ለዩክሬን በገፍ እየጎረፉ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎችን ሂደት ለማደናቀፍ ነው ተብሏል፡፡
ትናንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን ኪየቭ በመገኘት ከፕሬዝዳንት ዘለነስኪ ጋር መነጋገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሁለቱ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አገራቸው በአያሌው የጦር መሣሪያን ለዩክሬን መስጠቷን እንደምትቀጥል፣ ወታደሮቿንም እንደምታሰለጥን ቃል ገብተው ነበር፡፡
በትናንቱ የሩሲያ የባቡር ጣቢያ የአየር ጥቃት በትንሹ 5 ሰዎች ሲሞቱ 18 መቁሰላቸው ታውቋል፡፡
ጥቃቱ ያነጣጠረው ቪንቴሲያ ክልል በሚገኝ አንድ ባቡር ጣቢያ ላይ ነው፡፡
ባቡር ጣቢያው ከዩክሬን ለመውጣት እየሞከሩ ላሉ ዜጎችም ጭምር የሚያገለግል ነበር፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሩሲያ በክራማቶርስክ ባቡር ጣቢያ ላይ በወሰደችው የአየር ጥቃት 50 ሰላማዊ ዜጎችን መግደሏ አይዘነጋም።
በተያያዘ ዜና ማሪዮፖል ከተማ ግዙፉ የሶቭየት ዘመን የብረት ፋብሪካ ውስጥ ተጠልለው ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለማስወጣት የተደረገው ሙከራ በድጋሚ ከሽፏል፡፡
ሞስኮ ይህን ለማሳካት በፋብሪካው አካባቢ ለአጭር ሰዓት የሚቆይ የተኩስ አቁም አውጃ የነበረ ሲሆን የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ይህን አስተባብለዋል፡፡.
በተያያዘ ዜና የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን አሜሪካ ሩሲያን የማዳከም ሥራ ትሠራለች ይህም ሩሲያ ለሌሎች አገሮች ዳግም ስጋት እስከማትሆን ድረስ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኪየቭን ጎብኝተው ወደ ፖላንድ ባቀኑበት ጊዜ ነው፡፡አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ የ713 ሚሊዮን ዶላር እርዳታን ሰጥታለች፡፡
የቢቢሲ የጦር ጉዳዮች ተንታኝ ጋዜጠኛ ጆናታን ቢል እንደሚለው ይህ ሁኔታ አሜሪካ በጦርነቱ እጇን ለማስገባት እያደገ ያለ ፍላጎቷን ያሳያል፡፡
በዋሺንግተን የሩሲያ አምባሳደር አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን መጠነ ሰፊ ድጋፍ እንድታቆም የሚጠይቅ የዲፕሎማሲ ማስታወሻ መላካቸው ተዘግቧል፡፡
አሁን ቁልፏ የወደብ ከተማ ማሪዮፖል ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በሩሲያ ወታደሮች እጅ ወድቃለች፡፡
አጣብቂኝ ውስጥ የወደቁት የከተማዋ ነዋሪዎች ታዲያ በመጠለያ ውስጥ በአስጨናቂ ሁኔታ እንደሚቆዩ ዘጋቢዎቻችን ከካምፑ ያመለጡና ወደ ሌላ ከተማ የተሻገሩ የአይን እማኞችን በመጥቀስ ጽፈዋል፡፡
የ49 ዓመቱ ኦላሳንደር አንዱ ነው፡፡ የመጠለያ ጣቢያው ልክ በዓለም ጦርነቶች እንደነበሩት የማጎርያ ካምፖች ዓይነት ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡
የሩሲያ ወታደሮችም ለዪክሬን መከላከያ መረጃን ያቀብላሉ ብለው በጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ እጅግ አሰቃቂ ተግባር እንደሚፈጽሙም አስረድቷል፡፡
ሩሲያ አሁን ሙሉ በሙሉ ጦርነቱን ወደ ምሥራቅ በማዞር በዶንባስ ክልል መጠነ ሰፊ ጥቃት እያካሄደች ነው፡፡
የሩሲያ ግብ የዩክሬን ምሥራቃዊውን ክፍል ማለትም የዶንባስ ክልልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ጦርነቱ በስፖርት ዘርፉም ጥላን አጥልቷል፡፡ባለፈው ሳምንት የዊምብልደን ቴኒስ ውድድር አሰናጆች የቤላሩስና የሩሲያ ተወዳዳሪዎች በዚህ ውድድር እንዳይሳተፉ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡
ይህ ዉሳኔ ታዲያ ስፖርተኞቹ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሳይጠና የተወሰደ መሆኑ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡












