ዩክሬን፡ ዘለንስኪ በብረት ፋብሪካው የመሸጉ ወታደሮች ከተገደሉ ‹ከፑቲን ጋር አልነጋገርም› አሉ

የሩሲያው ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በማሪዮፖል የወደብ ከተማ በብረት ፋብሪካ ውስጥ የመሸጉት ወታደሮቻቸው በሩሲያ ከተገደሉ የሰላም ንግግር በሩ እንደተዘጋ ቁጠሩት ብለዋል፡፡

እጅግ ቁልፍ ከተማ ናት የምትባለው ማሪዮፖል ለሳምንታት አስከፊ ጦርነት ሲደረግባት ከቆየ በኋላ በሩሲያ ወታደሮች እጅ ወድቃለች፡፡

ይሁንና እጅ አንሰጥም ያሉ ወደ 2ሺህ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮችና ሌሎች ነዋሪዎች በአዞስታል ብረት ፋብሪካ መሽገዋል፡፡

ቢያንስ ሕጻናትና እናቶች ከፋብሪካው ለማስወጣት የተደረገው ሙከራ ከሽፏል፡፡

ዘለነስኪ እነዚህን ዜጎቻቸውን ከሞት ለመታደግ ወደ ቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ፖል ፍራንሲስ ጋር መደወላቸውን ተናግረዋል።

የሩሲያ መከላከያ ወታደሮቹን ለመደምሰስ ቀነ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ፑቲን ይህ ሐሳብ እንዳይፈጸም በማዘዛቸው እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካው በሩሲያ ወታደሮች ከበባ ላይ ነው፡፡

ዘለንስኪ ትናንት ከአየር ጥቃት ከለላ በኪየቭ የምድር ባቡር ጣቢያ ሥር ሆነው ለዓለም ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሁን ላይ አገራቸው ዩክሬን በእርዳታ ያገኘቻቸው እጅግ ዘመናዊ ድሮኖችና ውስብስብ የጦር መሣሪያዎች ራሷን ለመከላከል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉ ተስፋ ያለው ንግግር አድርገዋል፡፡

በዚህ ድፍን ሦስት ሰዓት በፈጀ የምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያ ዘለነስኪ ለጋዜጠኞች ዛሬ እሑድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ኪየቭን ይጎበኛሉ ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የዩኬ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ጆንሰን ከዘለንስኪ ጋር የስልክ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በርካታ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ እንደሚልኩም ቃል ገብተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሩሲያ የተለያዩ ምሥራቃዊ የዩክሬን ከተሞች ላይ ጥቃት እያደረሰች ሲሆን በኦዴሳ አንድ የመኖርያ ፎቅ ላይ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ ስምነት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡

ከጦርነቱ ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ ጥረቱ የቀጠለ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጎተሬዝ ነገ ቱርክን ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡ ከቱርክ በኋላ ደግሞ ኪየቭና ሞስኮ የጉብኝት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡

60ኛ ቀኑን የደፈነው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የ10ሺዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን 5 ሚሊዮን ዜጎችም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡