በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተው ጎርፍ 23 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ሌሊት ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ቢያንስ የ23 ሰዎችን ሕይወት ማጥፋቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
አርብ ምሽት ጀምሮ ሌሊቱን በሙሉ የጣለው ከባድ ዝናብ በርካታ ሰዎችን በማስጠም እና በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ ከሞቱት በተጨማሪ ወደ 30 የሚደርሱት ከአደጋው መትረፋቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በጎርፉ ሳቢያ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ መንገዶችም ተዘግተው ነበር። በመኪኖች ውስጥ መውጫ ያጡ ሰዎችን ለማዳን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት በጎዳናዎች ላይ ተሰማርቶ ነበር።
ወደ ዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚመጡ የነበሩ በርካታ የአውሮፕላን በረራዎችም በዝናቡ ምክንያት ወደ የባሕር ዳርቻ ከተማዋ ሞምባሳ እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል።
ፖሊስ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እንዳስታወቀው "የጣለው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ ጎርፍ አስከትሎ ለ23 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፣ መንገዶች ተዘግተዋል እንዲሁም ነዋሪዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የናይሮቢ ወንዝ ዳርቻውን ጥሶ ወጥቶ በውስጣቸው ሰዎችን የያዙ መኪኖችን እና የተለያዩ ነገሮችን ጠራርጎ ሲወስድ መመልከታቸውን የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል።
ዝናቡ በፈጠረው ከባድ ጎርፍ ምክንያት የናይሮቢ ዋና መንገዶች የሆኑት ሞምባሳ፣ ኡሁሩ እና ኪሪያጋ መንገዶች እንዲሁም ዌስትላንድስ የሚባለው አካካቢ በውሃ ተውጠው ነበር።
በሳምንቱ ማብቂያ አርብ አመሻሽ ላይ በከባድ ሁኔታ የጣለው ዝናብ ወትሮም በከፍተኛ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የሚጨናነቁትን የናይሮቢ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ አድርጓቸው ነበር።
ይህ አደጋ ከመድረሱ በፊት የኬንያ ሜቲዮሮሎጂ መሥሪያ ቤት የተራዘመ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር እና በከተሞች አካባቢ ከባድ ጎርፍ እንዲሁም ለዕይታ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንደሚፈጠር አስጠንቅቆ ነበር።
በተጨማሪም አስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ በአገሪቱ የሚገኙ ወንዞች የውሃ መጠን ከፍ እንደሚል አሳስቧል።
ዋና ከተማዋ ናይሮቢ እና የአገሪቱ ማዕከላዊ ከፍታማ ቦታዎች እንዲሁም የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናት ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖራቸው መሥሪያ ቤቱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ባለፈው ዓመት በኬንያ እና በጎረቤት ታንዛኒያ ውስጥ የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለኅልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል።















