ድሮግባ ለአይቮሪኮስት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ሳይመረጥ ቀረ

ዲዲየር ድሮግባ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዕውቁ የእግር ኳስ ተጫዋች ዲዲየር ድሮግባ ለአይቮሪኮስት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ቢወዳደርም አልተሳካለትም፡፡

ቅዳሜ ዕለት ከብዙ መዘግየት በኋላ በተደረገው ምርጫ ያሲን ኢድሪስ ዲያሎ አሸናፊ ሆኗል፡፡የቀድሞው የቸልሲ አጥቂ ድሮግባ በዚህ ውድድር ተሸናፊ የሆነው ገና በመጀመርያው የማጣሪያ ምርጫ ነው፡፡

የድምጽ ሰጪዎችን አንድ አምስተኛ እንኳ ድምጽ ማግኘት አለመቻሉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

በሁለተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ የቀድሞው የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የንግድ ሰው የሆነው ዲያሎ የቀድሞ የፌዴሬሽኑን ምክትል ፕሬዝዳንት ሶሪ ዲያያባቲን 63 ለ61 በሆነ ጠባብ ልዩነት አሸንፏል፡፡

ቅዳሜ የተደረገው ምርጫ ከ2020 ዓ/ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲራዘም የቆየ ነበር፡፡ ይህም የሆነው የአንዳንድ እጩዎች ተገቢነት ጉዳይ ላይ ጥያቄ በመነሳቱ ነበር፡፡

ከነዚህ የተገቢነት ጥያቄ ከተነሳባቸው መካከል ዲዲየር ድሮግባ አንዱ ነው፡፡ከብዙ አለመግባባት በኋላ ፊፋ በገላጋይ ዳኝነት ገብቶ ጉዳዩን መልክ ከሰጠው በኋላና ድሮግባም ተገቢ እጩ ስለመሆኑ ካረጋገጠ በኋላ ምርጫው እንዲደረግ ሆኗል፡፡

ድሮግባ ለዝሆኖቹ ከመቶ ጊዜ በላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ይህም በ2006 እና በ2010 የተደረጉትን የዓለም ዋንጫዎች ይጨምራል፡፡

ነገር ግን በነሐሴ 2020 ድሮግባ ለፕሬዝዳንትነት እጩ መሆን እንደማይችል ተነግሮት ነበር፡፡ፊፋ በጉዳዩ ጣልቃ የገባውም ይህን ጊዜ ነው፡፡

የ44 ዓመቱ ድሮግባ 4 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን እና 4 የኤፍ ኤ ዋንጫ እንዲሁም ሻምፒዮንስ ሊግን ያነሳ ሥመ ጥር አጥቂ ነው፡፡ይሁንና ይህ የእግር ኳስ ጀግና ለአገሩ ፌዴሬሽን በፕሬዝዳንትነት ሲወዳደር ገና በመጀመርያው ዙር 21 ድምጽ ብቻ በማግኘት ይሰናበታል ያለ አልነበረም፡፡

ተቀናቃኞቹ ዲያሎ 59 ድምጽ ዲያባቴ 50 ድምጽ አግኝተው ነበር በማጣሪያው ምርጫ፡፡ድሮግባ ለአገሩ እግር ኳስ ማበብ ሰፋፊ መርሐግብሮችን ነድፎ በማቅረቡ ዝናው ከፍ ብሎ ቆይቷል፡፡

ይሁንና ገና በአንደኛው ዙር መሸነፉ በርካታ የአገሬውን ዜጎች ሳያስቆጣ አልቀረም፡፡ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በርካታ ሰዎች ይህን ቁጣቸውን ሲገልጹም ነበር፡፡

‹የአይቮሪኮስት እግር ኳስ ቡድን ፕሬዝዳንቶች ድሮግባን ከዱት፤ የአገሪቱን ተስፋም አጨለሙ፡፡› ሲሉ የጻፉ ሰዎች ነበሩ፡፡አሁን በፕሬዝዳንትነት የተመረጠው ኢድሪስ ዲያሎ ለአራት ዓመታት ያገለግላል፡፡

አይቮሪኮስት ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን የበላች ሲሆን በ2023 የአፍሪካ ዋንጫን ታዘጋጃለች፡