ቦክሰኛው ማይክ ታይሰን አውሮፕላን ውስጥ ተሳፋሪን በቦክስ ዘረረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው ባለ ከባድ ሚዛን ሻምፒዮና ማይክ ታይሰን አውሮፕላን ውስጥ አንድን ተሳፋሪ በቦክስ ደብድቧል፡፡
የታይሰን ቃል አቀባይ እንዳለው ታይሰን ግለሰቡን በቦክስ ለመምታት የተገደደው የውሃ ላስቲክ ስለወረወረበት ነው፡፡
ከአውሮፕላኑ ውስጥ የተቀረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል ማይክ ታይሰን ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደ ግለሰቡ በመሄድ ይህ ማንነቱ ለጊዜው ያልተለየን ግለሰብ በጡጫ ሲነርተው በከፊል ይታያል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳለው ታይሰን ለዚህ መጥፎ አጋጣሚ የተጋበዘው ተሳፋሪው በተደጋጋሚ ሳለስቸገረው ነው፡፡
ፖሊስ ከዚሁ ክስተት ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡
አንዱ ግለሰብ በሳንፍራንሲስኮ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሕክምና እየተደረገለት ሲሆን ጉዳቱ ለሕይወቱ አስጊ አይደለም ተብሏል፡፡
ፖሊስ በትክክል ምን ተከስቶ እንደነበረ ከተጎጂዎች በቂ መረጃን እንዳላገኘ የሳንፍራንሲስኮ ፖሊስ ቃል አቀባይና ባልደረባ ተናግራለች፡፡
በዚህም የተነሳ ምርመራው እንደሚቀጥል፣ ነገር ግን ለጊዜው የተያዙት ሁለት ሰዎችም ከእስር እንደተለቀቁ ገልጻለች፡፡
ፖሊስ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በዚህ ክስተት ውስጥ ይኑሩበት አይኑሩበት ገና እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡
ይህ የማይክ ታይሰን የአውሮፕላን የቡጢ ክስተት የተፈጠረው ረቡዕ ዕለት ሲሆን አውሮፕላኑ ከሳንፍራንሲስኮ ወደ ፍሎሪዳ ለመጓዝ ገና ደንበኞችን በማሳፈር ላይ ሳለ ነበር፡፡
ክስተቱን ያሳያል የተባለው ተንቀሳቃሽ ምሥል የተቆራረጠና ታሪኩን ለመረዳት በቂ መረጃን የማይሰጥ ሲሆን ሆኖም ግን ግለሰቡ የውሃ ላስቲክ በማይክ ታይሰን ላይ ሲወረውርበት አያሳይም፡፡
ቲኤምዜድ፣የዕውቅ ሰዎችን ጉዳይ በመዘገብ የሚታወቅ ሚዲያ፣ እንዳለው ታይሰን በቅድሚያ ከዚህ ጸብ ውስጥ ከገባው ግለሰብ ጋር ፎቶ ለመነሳት ፈቅዶ ነበር፡፡
ነገር ግን ግለሰቡ ታይሰንን ያልተገባ ነገር እየተናገረ ትዕግስቱን ተፈታትኖታል፡፡
ማይክ ታይሰንም ግለሰቡን ‹ተረጋጋ› ሲል አስቀድሞ መልካም ምክርን ሰጥቶት ነበር፡፡
ማይክ ታይሰን ግለሰቡን በቡጢ ከደበደበው በኋላ ሰዎችን ለመገላገል ሲሞክሩ በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ይታያል፡፡
በመጨረሻ ምሥሉ የተደብዳቢው ግንባር ደም በደም ሆኖ ያሳያል፡፡
ማይክ ታይሰን ለእንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ሲጋለጥ የመጀመርያው አይደለም፡፡
እንደ አውሮጳዊያኑ በ1992 ዓ/ም ሴት በመድፈር ተወንጅሎ 3 ዓመት ተፈርዶበት ነበር፡፡
በ1997 ዓ/ም ደግሞ የተጋጣሚውን ሆሊፊልድን ጆሮ በመዘንጠሉ ከቦክስ ለጊዜው ገለል እንዲል መደረጉ ይታወሳል፡፡












