ኤለን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት ስምምነት ላይ ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የማህበራዊ ሚዲያው ትዊተር ቦርድ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር የዓለማችን ባለጸጋ ለሆነው ለለኤለን መስክ ለመሸጥ ተስማማ።
ከሁለት ሳምንት በፊት ትዊተርን ለመግዛት አስደንጋጭ ሃሳብ አቅርቦ የነበረው ኤለን መስክ ትዊተር ገና ያልተፈተሸ "ትልቅ አቅም እንዳለው" ተናግሯል።
በተጨማሪም የማህበራዊ ሚዲያውን ይዘት ከማላላት በተጨማሪ ሃሰተኛ አካውንቶችን እስከ ማጥፋት ተከታታይ ለውጦች እንዲደረጉም ጠይቋል።
ኩባንያው መጀመሪያ ላይ የኤለንን ትዊተርን ልግዛ ሃሳብ ውድቅ ቢያደርግም በአሁኑ ወቅት ግን ባለ ድርሻ አካላት ስምምነቱን ለማጽደቅ ድምፅ እንዲሰጡም ሊጠይቅ ነው።
በፎርብስ መጽሄት መረጃ መሰረት 273.6 ቢሊዮን የሚገመት የተጣራ ሃብት ያለው ኤለን መስክ የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ነው። ይህም በዋነኝነት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች በሆነው ቴስላ ባለው ድርሻ እንዲሁም ስፔስ ኤክስ የተባለውን የኤሮስፔስ ድርጅትም ይመራል።
"ነፃ ንግግር የዲሞክራሲ መሰረት ነው፤ ትዊተር ደግሞ ለሰው ልጅ የወደፊት ህይወት ወሳኝ ጉዳዮች የሚከራከሩበት የዲጂታል ከተማ አደባባይ ነው። "ሲል ኤለን መስክ ስምምነቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ አስታውቋል።
"በተጨማሪም ትዊተርን አዳዲስ ይዘቶች በመጨመር ማሻሻል እንዲሁም የትዊተርን አልጎሪዝም ክፍት በማድረግ መተማመንን ለመጨመር፣ አይፈለጌ ሃሰተኛ አካውንቶችን በማስወገድ እና ሁሉንም ሰው በማረጋገጥ ትዊተርን ከምንጊዜውም በላይ ማድረግ እፈልጋለሁ" ሲል አክሏል።
"ትዊተር ትልቅ አቅም አለው። ይህንንም አቅም ለማሳየት ከኩባንያው እና ከተጠቃሚው ማህበረሰብ ጋር ለመስራት እጠብቃለሁ።" በማለት አስረድቷል።
ትዊተር በይዘቱ ላይ ከፖለቲከኞችና ተቆጣጣሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየጨመረ ባለበትም ወቅት ነው ኤለን መስክ ይህንን ያሳወቀው።
የተሳሳቱ መረጃዎች በትዊተር መድረኮች ላይ መንጸባረቃቸው ከበርካታ አካላት ትችት እንዲቀርብበት ምክንያት ሆኗል።
ትዊተር ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል በርካታ ተከታይ ያላቸው የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ማገዱ ነው።
በወቅቱም ኤለን መስክ ይህንን ውሳኔም አስመልክቶም ኩባንያው "የመናገር ነጻነት ዳኛ የመሆን ሚና በመጫወቱ በርካቶች ደስተኛ አይሆኑም" ብሏል።












