የሩዋንዳ የዘር ፍጅት "የባለቤቴን ገዳይ ይቅር አልኩት፤ ልጆቻችንም ተጋቡ"

በህይወታችን ሰዎች ከሚያደርሱብን ህመም ለመፈወስ ምላሹ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር ነው ይባላል።
ከ28 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ በነበረው የዘር ፍጅት ባለቤቷን የገደለውን ሰው ይቅር በማለት ሴት ልጁ የሷን ወንድ ልጅ እንድታገባ የፈቀደች ሴትም ይህንኑ ታምናለች።
በአውሮፓውያኑ 1994 በ100 ቀናት ውስጥ 800 ሺህ የሚያህል ሩዋንዳውያን በተገደሉበት የዘር ጭፍጨፋ የተፈጠረውን የማህበረሰብ ቁስል እንዲሽር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዕርቅና ሰላም ለማምጣት እየሞከረች የምትገኝ ስትሆን በርናዴት መካካቤራም የዚህ ጥረት አካል በመሆን ታሪኳን ስትናገር ቆይታለች።
በርናዴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው "ልጆቻችን ከተፈጠረው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራቸውም። በቃ ተዋደዱ እና ሰዎች እርስ በርስ ከመዋደድ የሚያቆም ጉዳይ የለበትም"
እሷ እና የቀድሞ ባለቤቷ ካቤራ ቬዳስቴ የቱትሲ ማህበረሰብ ተወላጆች ሲሆኑ የጥቃቱ ኢላማ የተደረጉትም የሩዋንዳውን ሁቱ ፕሬዚዳንት የጫነ አውሮፕላን በአውሮፓውያኑ 1994 ከተመታ በኋላ ነው።
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን በተመታ በሰዓታት ውስጥ በአስርት አመታት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የተመረዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሁቱዎች፣ የተደራጁ ግድያዎችንና ጭፍጨፋዎችን ጀመሩ።
በሃገሪቱ ዙሪያ ባሉ ቱትሲ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን መፈጸም ጀመሩ።
ከእነዚህም አንዱ ግራቲየን ኒያሚናኒ ነበር። የግራቲየን ቤተሰቦች በምዕራብ ሩዋንዳ ሙሻካ በተሰኝው ግዛት ነዋሪ የነበሩ ሲሆን የበርናዴት ቤተሰቦችም ጎረቤቶች ነበሩ። ሁለቱም ቤተሰቦች ይተዳደሩ የነበሩት በግብርና ስራ ነበር።
የሩዋንዳ የዘር እልቂት ከቆመ በኋላ፣ የቱትሲ አማፂ ቡድን ስልጣን ሲይዝ፣ በጭፍጨፋው እጃቸው አለበት ተብለው የተከሰሱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል።
ግራቲየን በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንዱ ሲሆን በመጨረሻም በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ጉዳይ ለማየት በተቋቋመው ጋካካ በሚባለው የማህበረሰብ ፍርድ ቤት በአንዱ ቀረበ።
በእነዚህ ሳምንታዊ ችሎቶች ማህበረሰቡ ተከሳሹን ፊት ለፊት እንዲመለከቱ እድል የሰጠ ሲሆን በሁለቱም ወገን ያሉ ሰዎች ግድያዎቹ እንዴት እንደተፈጸመ ማስረጃ ያቀርባሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአውሮፓውያኑ 2004 ፣ ግሬቲን የበርናዴት ባለቤትን እንዴት እንደገደለ ከተናገረ በኋላ ይቅርታ ጠየቃት። እሷም በዚሁ ችሎት ላይ ይቅርታ ማድረጓን ተናገረች።
በርናዴት ይቅርታን በመምረጧ ምክንያት ግሬቲን የ19 ዓመት እስር ሳይፈረድበት ቀረ። ይልቁንም በሁለት አመት የማህበረሰብ አገልግሎት ታለፈ።
'መርዳት እፈልግ ነበር'
ግሬቲን በይፋ ይቅርታ ከመጠየቁ በፊት በእስር ላይ በቆየባቸው 10 አመታት ውስጥ ቤተሰቦቹ በርናዴትና አባቱ ሲገደል የ14 አመት ልጅ የነበረውን አልፍሬድ ጋር የነበረውን ሁኔታ ለማስተካከል ሲጥሩ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, BBC
የዘር ማጥፋት በተፈፀመበት ወቅት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ የነበረችው የግራቲየን ሴት ልጅ ያንኩሪጄ ዶናታ ወደነ በርናዴት ሄዳ በቤታቸው ውስጥ በስራ መርዳት ጀመረች።
"የአልፍሬድን እናት የቤት ስራውን አልፎ ተርፎም በእርሻው ላግዛት ወሰንኩኝ። ምክንያቱም አባቴ ለባለቤቷ ግድያ ተጠያቂ እንደሆነ በማሰብ ሌላ የሚረዳት ስለሌለ ነው" ስትል ያንኩሪጄ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"አልፍሬድ እናቱን በምረዳበት ወቅት በፍቅሬ የወደቀ ይመስለኛል።" ትላለች
በርናዴት በልጅቷ ሩህሩህነትና ቀናነት ልቧ ተነካ "አባቷ ባለቤቴን እንደገደለው እያወቀች በሚገባ ረድታኛለች። ልጄ አዳሪ ትምህርት ቤት ስለነበር ምንም እርዳታ እንደሌለኝ ታውቅ ነበር" በማለት የነበረውን ታስረዳለች።
"ልቧን እና ባህሪዋን ወደድኩት። ለዚህ ነው የልጄ ሚስት ብትሆን ያልተቃወምኩት።" ትላለች
ለግሬቲን ግን ነገሩ ቀላል አልነበረም ። በመጀመሪያ ስለጋብቻው ሲነገረው ሁኔታውን በጥርጣሬ ነበር የተመለከተው።'
ያንኩሪጄ እንደምትለው "እንዴት እና ለምን በርካታ ህመምን የፈጠረባቸው ቤተሰብ ከልጁ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዲኖር ይፈልጋሉ ሲል ደጋግሞ ይጠይቅ ነበር።

በርናዴት በያንኩሪጄ ላይ ምንም አይነት የበቀል ሃሳብ እንደሌላት ፅኑ አቋም በመያዟ በመጨረሻ እሱም አምኖ ለጥንዶቹ ምርቃቱን ሰጣቸው።
በርናዴት " አባቷ ለፈጸመው ድርጊት በያንኩሪጄ ላይ ምንም አይነት በቀል አልያዝኩባትም ነበር" ትላለች።
"ከሌላ ሰው በተሻለ ሁኔታ ስለምትረዳኝ የተሻለ ምራት እንደምትሆን አወቅኩኝ። ልጄን እንዲያገባት አሳመንኩት" በማለትም ታስረዳለች።
ጥንዶቹ በአውሮፓውያኑ 2008 በአካባቢው ባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስነ ስርዓት ተጋቡ።
ግሬቲን የማህበረሰብ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ከሁለት ዓመት በፊት በነበረ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ስለ ግድያው ተናዞ ይቅርታ ጠየቀ።
' እርቅ ከሌለ ቅዱስ ቁርባን የለም'
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአካባቢው ባሉ ማህበረሰቦች መካከል እርቅ ለመፍጠርና መልሶ ለማገናኘት በሚደረገው ጥረት ማዕከል ሆና ቆይታለች።
የሲያንጉጉ ሀገረ ስብከት ተወካይ የሆኑት አባ ንጎቦካ ቴዎገኔ ማህበረሰቡ የቤተ ክርስቲያኗን የእርቅ ፕሮግራም ተቀብለዋል ብለዋል።
ሌሎች በርካታ ቤተ እምነቶች ተመሳሳይ ፕሮግራም እየነደፉ ይገኛሉ።
አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች አብረው ከመኖር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ስለሚገነዘቡ በሰላምና በመግባባት ቢያደርጉት ይሻላል የሚል ምክርን እያስተላለፉ ይገኛሉ።
"በዘር ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች ጥቃት ከፈጸሙባቸው ቤተሰቦች ጋር እስካልታረቁ ድረስ መቁረብ አይፈቀድላቸውም" በማለት አባ ንጎቦካ ያስረዳሉ።
የመጨረሻው እርቅ የሚከናወነው ተከሳሹ እና ተጎጂው በአንድ ላይ በአደባባይ ሲታዩ ነው።
"ተጎጂው በይቅርታ እጆቻቸውን ወደ ተከሳሾቹ ይዘረጋሉ" ይላል።
በቅርቡም የሩዋንዳ የዘር ፍጅትን 28ኛ አመት አስመልክቶ እንዲሁም ማህበረሰቡ በአብሮነት እንዴት መቀጠል ይችላል በሚል በሙሻካ አንድ ዝግጅት ተዘጋጅቶ ነበር።
"ስለ ለውጥ ስንናገር የቆዳ ቀለም መቀየር ሳይሆን መጥፎ ባህሪን መቀየር ነው" በማለት የዝግጅቱ አስተባባሪ አፒያን ናንጉዋሃቦ ይናገራሉ
"የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር ከመወሰን በፊት የልብ መለወጥ አስፈላጊ ነው." በማለትም ኦፒያን ያስረዳሉ።
በርናዴት በዚህም ዝግጅት ላይ ነው ልጇ ከባሏ ገዳይ ሴት ልጅ ጋር መጋባቱን የተናገረችው
"የልጄን ባለቤት በጣም እወዳታለሁ እና ባለቤቴ ከሞተ በኋላ እኔን ለመርዳት እዚህ ባትኖር ኖሮ እንዴት እንደምሆን እንዴት በህይወት እንደምተርፍ አላውቅም." ብላለች
የአልፍሬድ እና የያንኩሪጄ የፍቅር ታሪክ ሌሎች ብዙ ሰዎችን ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ይቅርታ እንዲያደርጉም እንዳበረታታ በማየቷ በጣም እንደተደሰተች ተናግራለች።












