የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ በፊታውራሪነት የመሩት ኮሎኔል ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቀድሞው የሩዋንዳ ጦር ሰራዊትን ይመሩ የነበሩትና ለ800ሺህ ሩዋንዳዊያን እልቂት ተጠያቂ ናቸው ከሚባሉት ሰዎች አንዱ የነበሩት ኮሎኔል ቴዎኖስቴ ቦጎሶራ ከዚህ ዓለም ተለዩ፡፡
በቀድሞዋ ሩዋንዳ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ቁልፍ ሰው የነበሩት ኮሎኔል ቦጎሶራ የሞቱት በማሊ፣ ባማኮ ሕክምና በመከታተል ላይ ሳሉ ነው፡፡
ኮሎኔል ቦጎሶራ የ80 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ነበሩ፡፡
በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ቁልፍ የአመራር ተሳትፎ የነበራቸው እኚህ ኮሎኔል የካጋሜ ሰራዊት ሩዋንዳን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ካሜሮን ቢሸሹም ኋላ ላይ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ ቀርበው ነበር፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ይደገፍ የነበረው የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ኮሎኔል ቦጎሶራን የዕድሜ ልክ እስራት በይኖባቸው ነበር፡፡
ይህ የፍርድ ውሳኔ በኋላ ላይ ወደ 35 ዓመታት እስር ዝቅ ተደርጎላቸው ነበር፡፡
ወንድ ልጃቸው አቺሌ ለቢቢሲ እንደተናገረው አባቱ ኮሎኔል ባጎሶራ የሞቱት የልብ ሕክምና እያደረጉበት ከነበረው ባማኮ ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡
እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1994 ዓ/ም በሩዋንዳ በደረሰ የዘር ፍጅት በመቶ ቀናት ብቻ 800ሺህ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ከሞቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ የቱትሲ ጎሳዎች ቢሆኑም ለዘብተኛ ቱቱዎችም ከሞት አላመለጡም፡፡
ይህ የዘር ፍጅት የወቅቱን የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ጁቬኔል ሐብያሪማናን መገደል ተከትሎ የደረሰ አሰቃቂ ጥፋት ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቱ የተገደሉት ተሳፍረውበት የነበረው አውሮፕላን በሚያዚያ 6፣ 1994 ተመትቶ ተከስክሶ ከወደቀ በኋላ ነው፡፡
ኮሎኔል ቦጎሶራ ያን ጊዜ በመከላከያ ሚኒስትር ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡
በኋላም ፍጅቱን በፊታውራሪነት ከመሩ ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡
ፖል ካጋሜ ይመሩት የነበረው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር አገሪቱን ሲቆጣጠር ግን ኮሎኔሉ ሸሽተው በካሜሮን አገር ለተወሰኑ ዓመታት ተደብቀው ቆይተዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ከተደበቁበት ተይዘው ለፍርድ ቀርበዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ይደገፍ የነበረው የያኔው የጦር ወንጀለኞች የፍርድ ሸንጎ ኮሎኔሉን በጦር ወንጀል፣ በፖለቲከኞች አፈናና ግድያ እንዲሁም በመቶ ሺዎች ሞትና የዘር ፍጅት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
በተለይም ኮሎኔል ቦጎሶራ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን አጋቴ ኡዊሊንጊያማን ማስገደላቸው ተረጋግጧል፡፡
ያኔ በዘር ፍጅቱ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይልን ይመሩ የነበሩት ካናዳዊው ጄኔራል ሮሚዮ ዳላየር ሟቹን ኮሎኔል ‹የዘር ፍጅቱ ሞተር› ሲሉ ይገልጧቸዋል፡፡
ካናዳዊው ጄኔራል ሮሚዮ ዳላየር ‹ሼክ ሐንድስ ዊዝ ዘ ዴቪል› የሚልና በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ላይ የሚያጠነጥን ዝነኛ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡
ጄኔራል ሮሚዮ ዳላየር ሟቹ ኮሎኔል በሩዋንዳ ፍጅት ወቅት እሳቸውንም ጭምር ሊያስገድሏቸው እንደነበረ በዚህ መጽሐፍ ላይ ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት መጨረሻ ኮሎኔል ቦጎሶራ ከእስር እንዲለቀቁ ለፍርድ ቤት አመልክተው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡
ሆኖም የእስር ጊዜያቸውን ለማጠናቀቅ 9 ዓመታት ብቻ ይቀራቸው ነበር፡፡
ኮሎኔሉ በሩዋንዳ የዘር ፍጅት እጃቸው በደም ተጨማልቋል ተብለው ከታሰሩ በርካታ ወንጀለኞች ጋር በማሊ በሚገኘው ኳሊኮሮ እስር ቤት ነበር ሦስት ዐሥርታትን ያሳለፉት፡፡












