የወሲብ ጥቃት የተንሰራፋበት የኬንያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ስፖርት

በኬንያ የቀድሞ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ወሲባዊ ጥቃቶች በሴቶች ጨዋታዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ለዓመታት ያህል ቢንሰራፋም በርካቶች በፍራቻ ምክንያት ድምፃቸውን ማሰማት አልቻሉም ትላለች።
በአሁኑ ወቅት በ30ዎቹ እድሜ ላይ የምትገኘው የቀድሞ ተጫዋች እሷም ገና ጨዋታ በጀመረችበት ወቅት በአሰልጣኟ ጥቃት እንደደረሰባት ትናገራለች።
ባለፈው ሳምንት በማሊ ቅርጫት ኳስ ጨዋታዎች ውስጥ "ተቋማዊ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት" እንደሚደርስና አስርት ዓመታትን እንዳስቆጠረ መዘገቡን ተከትሎ የአፍሪካ የሴት ቅርጫት ኳስ ጨዋታዎች ትኩረት አግኝተዋል።
"በየትኛውም የኬንያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ይህ ነገር እንደሚፈፀም ያውቃሉ፤ ነገር ግን ዝምታን መርጠዋል" ትላለች የቀድሞ ቅርጫት ኳስ ተጫዋቿና ማንነቷንም ለመጠበቅ ራሄል ብለን የምንጠራት ግለሰብ።
"በርካታ ታዳጊ ሴቶች ጥቃት ቢደርስባቸውም በዝምታ ተሸብብዋል" ትላለች።
"በትልልቅ ክለቦች ላይ የማያቸውም ሴቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው ባውቅም ከፍራቻ ነው መሰለኝ ሁሉም ዝም ብለዋል" በማለት ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ አስረድታለች።
ትክክለኛ ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችው የቀድሞ ተጫዋች ጥቃት የደረሰባቸው አብዛኞቹ ታዳጊዎች በነበሩበት ወቅት ሲሆን ይህም ሙያቸውን ለማሳደግም ቃል ከመግባት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ትገልፃለች።
በኬንያ የቅርጫት ኳስ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶችን አስመልክቶ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራው ሂውማን ራይትስ ዋች ምርመራ እያደረገ ሲሆን ራሄል ስለዚህ ጉዳይ ሳታውቅ ነበር ለቢቢሲ የቀጠለውን በደል ስታስረዳ የነበረው።
በማሊ ለረዥም ዓመታት የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን፣ ፊባ ሪፖርቱን ማውጣት ተከትሎ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተከፍቷል፤ ይህም ዘመቻ ለጥቃቱ ሰለባዎች እርዳታ ለማድረስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ፊቱን በአሁኑ ወቅት ወደ ኬንያ አዙሯል።
"ሂውማን ራይትስ ዋች በኬንያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ታዳጊና ወጣት ሴት አትሌቶች ላይ የወሲብ ጥቃቶች ይደርሳሉ የሚሉትን ሪፖርቶች እየተመለከትናቸው ነው ስጋትም አጭረውብናል" በማለት የድርጅቱ ግሎባል ኢኒሺየትቭ ዳይሬክተር ሚንኪ ዎርደን ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።
"በብሔራዊ ቅርጫት ኳስ ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ታዳጊ ተጫዋቾችን የመጠበቅ እና ደኅንነታቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው። ዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽ፣ ፊባ በስፖርት ውስጥ የሚፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን ዝም ብሎ አይመለከትም፤ ወሲባዊ ጥቃቶችን የመከላከል ቁርጠኝነት አለን" ብለዋል።
"ለታዳጊ ተጫዋቾች ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ማረጋገጥ፣ ጥቃትን የሚፈጽሙትን ከስፖርቱ ማስወገድ፣ ወሲባዊና ፆታዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸው ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ የፊባ እና የሁሉም ብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ኃላፊነት ነው" በማለት ያስረዳሉ።
"ራሴን ማዳን አለብኝ"
ምንም እንኳን ሂውማን ራይትስ ዋች ይህንን ይበል እንጂ ከአንድ ወር በፊት የኬንያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆነ ግለሰብ የ22 ዓመቷን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል በሚል ክስ ቢቀርብበትም ነፃ ሆኗል።
በሐምሌ ወር በአገሪቱ ውስጥ በጣም ስኬታማ ከሆኑት አሰልጣኞች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚታየው እና ቀደም ሲል የኬንያ የታዳጊ ሴቶች ቡድኖችን ያሰለጠነው ፊሊፕ ኦንያንጎ፣ ፖሊስ በተጫዋቾቹ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ላይ የከፈተውን ምርመራ ተከትሎ በፈቃደኝነት ከተለያዩ የአሰልጣኝነት ቦታዎቹ ለቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀጣዩም ቀን የኬንያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የራሱን የመጀመሪያ ምርመራ ተከትሎ ፊሊፕ ኦንያንጎን ከሁሉም የቅርጫት ኳስ ኃላፊነቶቹ አባሯል።
በተደራቢነት የቅርጫት ኳስ ጋዜጠኛ ሆኖ የሚሠራው ፊሊፕ ኦንያንጎ ምንም ጥፋት አላጠፋሁም ሲል አጥብቆ አስተባብሏል።
ፖሊስም በቂ ማስረጃ አላገኘሁም በሚል ነፃ አውጥቶታል ። ሆኖም እስካሁን ድረስ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ወደነበረው የቀድሞ ኃላፊነቱ አልተመለሰም።
ጥቃት የደረሰባት የ22 ዓመቷ ወጣት ቢቢሲ በደወለላት ወቅት በፖሊስ ምርመራ ውጤት መበሳጨቷን ገልጻለች።
"ማስረጃ ስለሌለ ጉዳዩ ተዘግቷል፤ በጣም ነበር ተስፋ ያስቆረጠኝ" ብላለች።
ጥቃቱ ይፋ የሆነው የ22 ዓመቷ ወጣት ገደኛዋ ስለደረሰባት ጥቃት በዝርዝር ስታስረዳ መቅረጿን ተከትሎ ነው። የተቀረፀው ድምፅም ለኬንያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን ለቅርጫት ኳስ ማኅበረሰብም ተልኳል።
ራሄል የደረሰባትን ጥቃት እንደገና እንድትኖረው ቢያስገድዳትም በቅርብ በተፈጠሩ ክስተቶች ምክንያት ድምጿን ለማሰማት እንዳነሳሳት ትናገራለች።
"የኬንያን ቅርጫት ኳስ ነፃ የሚያወጣ ነገር ከሆነ ለምን አላደርገውም?" ሌሎችንም ሆነ ራሴን ማዳን አለብኝ። እኔ በማገገም ሂደት ውስጥ የፈውስ ምንጭ እየሆነልኝ ነው"ትላለች።
ጥቃት በደረሰባት ወቅት አልታመንም በሚል ፍራቻ ሪፖርተር አላደረገችም እናም በአሁኑ ወቅት ስለደረሰባት ግፍ ስታወራ ልክ እንደሷ በርካቶችም በቡድናቸው ውስጥ መጫወት አንችልም በሚልም ሪፖርት እንዳላደረጉ ተረድታለች።
በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ጥቃት የደረሰባቸውና ተደጋጋሚ የወሲብ ጥቃት የተሞከረባቸው ሌሎች ሦስት ሴቶችን ቢቢሲ ምስክርነትም አግኝቷል።
"ገና ታዳጊና ራሳችንንም በደንብ መግለፅ የማንችልበት ወቅት ነበር። በዚያን ጊዜ የሚሰማንም ሰው አልነበረም። እየዋሸንም ይመስላቸዋል" ብላለች አንዷ።
"ወሲባዊ ጥቃት ይቁም"
ፖሊስ ምርመራውን በሚያካሂድበት ጊዜ ኬንያ ውስጥ "የወሲብ ትንኮሳ ይቁም" የሚል ዘመቻና ፊርማ ማሰባሰብ በኢንተርኔት የተጀመረ ሲሆን የኬንያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን "እንዳላየ ሆኗል" በሚልም ተከሷል።
አቤቱታው ይፋ በሆነበት ወቅት ጊዜ 2 ሺህ ፊርማዎችን ሰብስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል የተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን በቸልተኝነት አይቷቸዋል ወይም "ተባብሯል" የሚሉ ክሶችን አስመልክቶ ለፌዴሬሽኑ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስም "የኬንያ የወሲብ ሕጎችን የጣሰ ማንኛውንም ሁኔታ በጥብቅ ያወግዛል" በማለት መልሷል።
"ከባለሥልጣናቱ ጋር ለመተባበር ያለንን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት ለማሳየት ይህንን ሕግ የጣሰ ማንኛውንም እርምጃ የያዘ መረጃ ያላት ሴት አትሌት ይህንን ለመመርመር ከተቋቋመው የሚኒስትር ኮሚቴ ጋር እንድትገናኝ ጥሪ አቅርበናል" ሲል አክሏል።
በሐምሌ ወር የኬንያ መንግሥት በአገሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ላሉ ሴት አትሌቶች ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት በማሰብ በስፖርቱ ውስጥ የሥርዓተ -ፆታ ደኅንነት ኮሚቴን መስርቷል።
የስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ "ጥቃት ወይም ትንኮሳ ደርሶባቸው ሪፖርት ቢያደርጉ ሊጎዱ የሚችሉ አትሌቶች" ለኮሚቴው እንዲያሳውቁ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ የኮሚቴው ግኝት ለሕዝብ ገና ይፋ አልሆነም።
የቡድን ድጋፍ
የኬንያ ከፍተኛ የሴቶች የቅርጫት ኳስ ቡድን ካፒቴን አዳዲሶቹን እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ ገልፃለች።
ጥቃት እንዳልደረሰባት የምትናገረው ሮዝ አማ "ምንም ለማውራት ፈታኝ ጉዳይ ቢሆንም እንዲህ አይነት ትኩረት ማግኘቱ መልካም ነው" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በአሁኑ ወቅት የጥቃቶቹ ሁኔታ ይፋ መሆኑ በሴት ልጆቻችን ላይ ደጋግሞ የሚከሰት ዑደት እንዳይሆንና እኛ እንደ ሴቶች የምንፈልገውን ትኩረት እያገኙ ነው ማለት ነው" ብላለች።
"በስፖርት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡም ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸው ታዳጊዎች መውጣት አለባቸው። የየትኞቹ አካባቢዎች ደኅንነታቸው የተጠበቁ አለመሆናቸውን እንድናወቅና ለሌሎችም ለማሳወቅ ይረዳናል" ትላለች።
በካሜሩን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሴቶች የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ኬንያ ተሸንፋ ወጥታለች።
በማሊ ባለፈው ሳምንት የወጣውን ሪፖርት ተከትሎ የአገሪቱ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ሰባት አባላት በቅርጫት ኳስ የበላይ አካል ፊባ ታግደዋል።
የምርመራው ውጤት እንዳረጋገጠው የማሊ ፌዴሬሽን በሠራተኞቹ አማካኝነት የሚፈጸመውን በደል ሸፍኗል። የቀድሞው የታዳጊ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ አማዱ ባምባ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ውስጥ ፍርድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ግለሰቡ ወንጀሎቹን አልፈፀምኩም ብሎ አስተባብሏል።
ሃያ ሁለት ምስክሮች ለመናገር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሰላሳ አንድ ምስክሮች ላይ በመመርኮዝ የፊባ ሪፖርት ከአውሮፓውያኑ 1999 እስከ 2007 የማሊ ፌዴሬሽንን ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሃማኔ ኒያንግን ነፃ አድርጓቸዋል።












