ለወራት ሥራው ላይ ባለመገኘቱ የተባረረው ኬንያዊ ፖሊስ 'ኮማ' ውስጥ ነበር ተባለ

ሩበን ኪሙታይ ሌል

የፎቶው ባለመብት, JOAN JEPTOO

የምስሉ መግለጫ, ሩበን ኪሙታይ ሌል

ለዘጠኝ ወራት ያህል ከሥራ ቦታው በመጥፋቱ የተባረረው ኬንያዊ ፖሊስ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ኮማ ውስጥ እንደነበር ታወቀ።

ሩበን ኪሙታይ ሌል የተባለው የፖሊስ ባልደረባ ሆስፒታል መግባቱንም ሆነ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ሲረዳ እንደነበር አልታወቀም ተብሏል።

ሆኖም ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሆስፒታል በህክምና ላይ እንዳለና አሁን በተወሰነ ደረጃ መንቃቱ ተገልጿል።

የሥራ ባልደረቦቹ ለወራት ያህል ሲፈልጉት የነበረ ሲሆን ምናልባትም ከፖሊስ አባልነቱ "ከድቶ" ወጥቷል በሚል ትተውት ነበር።

ደመወዙም ለወራት ያህል ከተከፈለው በኋላ ተቋርጧል።

አስገራሚው ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ቤተሰቦቹም ያለበትን ሁኔታ አለማወቃቸውና እነሱም ሲፈልጉት የነበረ መሆኑ ነው።

የፖሊስ አባሉ በሌለበት የእስር ማዘዣ ወጥቶበት የነበረ ሲሆን ሊገኝ ስላልቻለም የቀረበበት ክስ እንዲተው ተደርጎ ነበር።

ሩበን በሥራ ገበታው ላይ ባልተገኘበት ወራት ሁሉ ሆስፒታል ውስጥ የነበረ ሲሆን ለዘጠኝ ወራት ራሱን ስቶ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ነቅቷል ተብሏል።

ሙሉ በሙሉ ማንነቱ ባይመለስለትም ስሙንና የፖሊስ መኮንን መሆኑን መናገሩን ተከትሎ ዘመዶቹ ተፈልገው መገኘታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ፖሊሱ በባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ የመኪና አደጋ ደርሶበት በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኝ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በሚል ህክምና ሲደረግለት ነበር የቆየው።

በወቅቱም ምንም አይነት ማንነቱን የሚገልፅ መታወቂያ አልያዘም ነበር ተብሏል።

ፖሊስም ወደ ሥራው እንደሚመለስና ደሞዙም እንደሚከፈለው አሳውቋል።