የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሽግግር አስተዳደር ምስረታን እንደ አማራጭ አቀረበ

የቦዴፓ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Boro Democratic-Party

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ክልላዊ የሽግግር መንግሥትን ጨምሮ ጊዜያዊ አስተዳደርና ባለአደራ መንግሥት በክልሉ እንዲመሰረት የሚሉ አማራጮችን አቀረበ።

ፓርቲው ለዚህም እንደ ምክንያትነት የጠቀሰው በክልሉ በተወሰኑ ቦታዎች ምርጫ ካለመደረጉ ጋር ተያይዞ "የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር" በማለት መሆኑን አስታውቋል።

የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ቢደረግም በክልሉ በመተከል፣ በካማሽ እና በከፊል አሶሳ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ምርጫ አልተደረገም።

የክልሉ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ለዚህ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ያለው ብቸኛ አማራጭ በምርጫ ቦርድ በሚወጣ መርሃግብር መሰረት በሚደረግ ምርጫ እንጂ በሌላ መልኩ የሚቋቋም አስተዳደር እንደማይኖር አመልከቷል።

በክልሉ ሊደረግ የነበረውና በድጋሚ የተራዘመው ምርጫ መስከረም 20 ሊከናወን ቢታሰብም ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባለመሻሻሉ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20/2014 በክልሉ ምርጫ እንዳይደረግ መወሰኑን ገልጿል።

ፓርቲው የክልሉን ሕገ መንግሥት ጠቅሶ በክልሉ ምክር ቤት አብላጫ ወንበር ያለው ፓርቲ መንግሥት እንደሚመሰርት ቢደነግግም ምርጫ ተደርጎ አብላጫ ወንበር ያገኘ ፓርቲ የለም ብሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ክልሉን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሲያስተዳድር የነበረው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ የሥልጣን ጊዜው ስለሚመጠናቀቅና በተወሰኑ ቦታዎችም ምርጫ ባለመደረጉ ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሕጋዊ መሰረት የለውም ብሏል።

የምክር ቤቱ ስልጣን በ2012 ዓ.ም ቢጠናቀቅም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተሰጠው ውሳኔ ሥልጣኑ እስከ መስከረም 24/2014 ለአንድ ዓመት መራዘሙንም አስታውሷል።

ነገር ግን ከመስከረም 25 ጀምሮ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደሌለበት፣ ፓርቲው በሕዝብ ሳይመረጥ ክልሉን ማስተዳደር እንደማይችልና ድጋሚም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግና የሥልጣን ጊዜ ማራዘም አይቻልምም ብሏል።

"ያለ ምርጫ ሥልጣን ላይ መውጣት እንደማይቻል ሁሉ ስልጣን ላይ መቆየትም አይቻልም" ብሏል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ።

ስለዚህም ምርጫ ተካሂዶ ክልላዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ የክልሉ ገዢ ፓርቲ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ክልላዊ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰርቱ ጥሪው አቅርቧል።

በሁለተኛ ደረጃ ፓርቲው ያቀረበው አማራጭ ሃሳብ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም የሚል ነው።

በመተከል እና ከማሽ ዞኖች የፀጥታው ችግር ተባብሶ በዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል አድርሷል ያለው ፓርቲው፤ በአብዛኛው አካባቢዎች መሰረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶች መቋረጣቸውንና የጸጥታ ችግሩንም በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሂደት መቆጣጠል ስለማይቻል ምርጫ ማካሄድ አዳጋች መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሰረት የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት አዋጅ መሰረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የፌዴርሽን ምክር ቤት ክልሉን የሚያስተዳድር ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ጠይቋል።

በሦስተኛነት ፓርቲው እንደ አማራጭ የጠቀሰው ባለአደራ አስተዳደር ማቋቋም ነው። በክልሉ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገለልተኛ የሆነ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር እንዲደራጅም ጠይቋል።

"ክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ፤ ከሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር የምንጋራበት ቀጠና በመሆኑ፤ ለአራት ዓመታት የቆየ የጸጥታ ችግርና አለመረጋጋት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር" መደረግም እንዳለበትም ፓርቲው አሳስቧል።

ከእነዚህ ሕገ መንግሥታዊ አማራጮች ውጪ ሌላ አማራጭ መኖሩን እንደማያምን ፓርቲው ጠቅሶ ውይይትና ድርድር እንዲጀመር ያለ ምርጫ ከመስከረም 25 በኋላ ክልሉን ለመምራት የሚደረግ "ሕገ ወጥ አካሄድ ተቀባይነት የለውም" ብሏል።

አክሎም "ምርጫ አልተደረገም ማለት መንግሥት የለም ማለት አይደለም። ነገር ግን የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሳይመርጥ ብቻውን የሚመራው መንግሥት ሊኖር አይችልም" በማለት አስፍሯል።

ይህንንም ለማመቻቸት ለክልሉና ለፌደራል መንግሥት ውይይትና ድርድር እንዲጀመር ጠይቋል። ሆኖም ይህ ካልሆነ "በክልሉ ውስጥ ለሚፈጠርው ማንኛውም ችግር እና ሥርዓት አልበኝነት የክልሉ ገዢ ፓርቲ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እናሳስባለን" ብሏል።

ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ በክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በኩል ለፓርቲው ጥያቄ በሰጠው ምላሽ "ምርጫ ማድረግና አለማድረግ የምርጫ ቦርድ ስልጣን ብቻ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ ይህ ፓርቲ ከጡት አባቱ የወረሰውን የፖለቲካ ሴራ በመጠቀም የክልላችን ሕዝብ ወደ ግጭትና ብጥብጥ ለመምራት የተዘጋጀ ፓርቲ" ነው ብሏል።

ብልጽግና ፓርቲ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አብላጫ ድምፅ በማግኘት መስከረም 24 መንግሥት ለመስረት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

"መላው የክልላችን ሕዝባች የሥልጣን መገኛ መንገድ የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑን ተረድቶ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚወጣን የምርጫ ጊዜ ሠሌዳ ጠብቀው ይሆነናል ያሉትንና ያመኑትን ፓርቲ እንዲመርጡ" ጠይቋል።

ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ የመጀመሪያውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ከምርጫ ቦርድ ያገኘ ፓርቲ ሲሆን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዱ ነው።

ፓርቲው ከምስረታው በፊት ብሎም ከተመሰረተ በኋላ ከከልሉ መንግሥት ጫና ይደርስብኛል ሲል ለምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል።