የቤኒሻንጉል ክልልና የታጣቂው የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስምምነት ይዘት

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን እና የታጣቂ ቡድኑ ተወካይ አቶ አጀግናማው ማንግዋ

የፎቶው ባለመብት, Metekel Zone Communication

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትና ታጣቂው ቡድን በትናንትናው ዕለት የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ በክልሉ በተደጋጋሚ በንፁሃን ላይ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊን አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር ለቢቢሲ ተናገሩ።

የክልሉ አስተዳደርና ታጣቂ ቡድኑ የመግባቢያ ስምምነት የፈረሙት በተደጋጋሚ ጥቃት በሚከሰትበት የመተከል ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት መፍትሔ ለማምጣት መሆኑንም የመተከል ዞን ኮሚዩኒኬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ካወጣው መረጃ መረዳት ተችሏል።

ክልሉን ወክለው ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሃሰን እና የታጣቂ ቡድኑ ተወካይ አቶ አጀግናማው ማንግዋ የስምምነት ሰነዱን መፈረማቸው ቢገለፅም የታጣቂው ቡድን ስም በዞኑ መግለጫው ላይ አልሰፈረም።

ለመሆኑ ስምምነቱ የተደረሰው ከየትኛው ታጣቂ ቡድን ጋር ነው? ብሎ ቢቢሲ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድርን ጠይቋል።

የታጣቂው ቡድን ማንነት

ታጣቂው ቡድን በአካካቢው ንጹሃን ዜጎችን ግድያ ይፈጽሙ የነበሩና ከማኅበረሰቡ ወጥተው ወደ ጫካ ገብተው የሚዋጉና በአብዛኛው የጉሙዝ ብሔረሰብ ተወላጆች ናቸው ይላሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ታጣቂዎቹ መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉና የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከእነዚህ እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎችም መረዳት የተቻለው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባላት መሆናቸውን እንደሆነ ኃላፊው ይናገራሉ።

"ድርጅቱን ወክለን እየታገልን ያለነው የሚሉ ነገሮችን ያነሳሉ። በተጨባጭም የድርጅቱ መታወቂያዎችን ይዘናል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ታጣቂዎቹ ከተደመሰሱ በኋላ ኪሳቸው ውስጥ መታወቂያዎችን አግኝተናል" ይላሉ።

ታጣቂዎቹ በዋነኝነት የህዳሴ ግድብ በሚገነባበት አካባቢ የነበሩ ሲሆን በትጥቅ ትግልም ከዓመት በላይ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ መሆናቸውንም አቶ ኢስሃቅ ያስረዳሉ።

ፓርቲው ከዚህ ቀደም ዕውቅና አግኝቶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በዚህ ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ ከሰረዛቸው 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

በወቅቱም ምርጫ ቦርድ እንዳሳወቀው በተለያዩ ምክንያቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም መስፈርት አሟልተው እንዲያቀርቡ የተወሰነ እና የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ በሚል መሰረዙን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ኃላፊው በበኩላቸው "ምርጫ ቦርድ አንድ ድርጅት በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ ፍቃድ ከወሰደ በኋላ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መታገል ሲገባው የታጠቀ ኃይል በመሆኑ ሊሰረዝ ችሏል" ይላሉ።

ድርጅቱ ዕውቅና እንደሌለው አስታውሰው በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ይህንን ኃይል እንወክላለን የሚሉ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ።

ክልሉ የሚያውቀው በጉሙዝ ሕዝብ ዴሞከራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ስም የሚንቀሳቀሱ የታጣቂ አባላትን ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፤ ከውጭ ኃይሎችና ከውስጥ ባሉ ኃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ የሚደረግላቸው እንደሆነ ጠቅሰው በሱዳን በኩልም ይገባሉ ይላሉ።

"በዋነኝነት የህዳሴ ግድብ አካባቢን የግጭት ማዕከል ለማድረግ በተደራጀ እየተሰራ እንደሆነም" ኃላፊው ያስረዳሉ።

አካባቢው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ለዓመታት የሚወዛገቡበት የህዳሴ ግድብ ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ "በርካታ ኃይሎች እጃቸውን የሚያስገቡበትና እነዚህን ታጣቂዎች ከኋላ ሆነው በሎጅስቲክም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የሚደግፉበት ሁኔታ አለ" ይላሉ።

"ወጣቶቹ በተለያየ ምክንያት ተታልለው ነው ጫካ ገብተው ሲታገሉ ነበር። ትግላቸው ይሄንን ያህል የጎላ አልነበረም። በክልሉ መንግሥት መመለስ የሚችሉ ጥያቄዎችን ይዘው ነበር" የሚሉት አቶ ኢስሃቅ "ነገር ግን ያንን ባለመረዳት ጫካ ገብተው ንፁሃን ዜጎች ላይ በተለያየ መንገድ ጥቃት ሲፈፅሙ የነበሩ መሆናቸውን" ያስረዳሉ።

የመተከል ዞን ነዋሪ የነበረው አለሙ በየነ፣ ቤተሰቡን ለመታደግ በአውቶብስ ወደ ቻግኒ ከተማ በታኅሣሥ 3 2013 ዓ.ም ይልካቸዋል። ታጣቂዎች ግን ባለቤቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 44 ተሳፋሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገደሉ። በታኅሣሥ 30 2013 አለሙ በየነ በቻግኒ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ይገኝ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመተከል ዞን ነዋሪ የነበረው አለሙ በየነ፣ ቤተሰቡን ለመታደግ በአውቶብስ ወደ ቻግኒ ከተማ በታኅሣሥ 3 2013 ዓ.ም ይልካቸዋል። ታጣቂዎች ግን ባለቤቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 44 ተሳፋሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገደሉ

የክሉ መንግሥትና የታጣቂው የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስምምነት ይዘት

በአሁኑ ወቅት የተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ የተፈረመውም እጃቸውን በሰላም ከሰጡ ታጣቂዎች ጋር ሲሆን ስምምነቱ በዋነኝነትም በክልሉ ይስተዋላሉ የሚሏቸውና ታጣቂዎቹ የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታት አለባቸው የሚል አለበት ይላሉ።

ኃላፊው የመልካም አስተዳደር የሚሏቸውና ታጣቂዎቹ ከሚያነሷቸውም መካከል ትምህርታቸውን ጨርሰው የቅጥር ምደባ ያላገኙ፣ በተለያየ መንገድ አድሏዊ አሰራር ተፈፅሞብናል ብለው ያመለከቱም አለበት ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያልገቡና ያኮረፉ እንዳሉም ይጠቅሳሉ።

በስምምነቱም መሰረት በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በምጣኔ ሀብቱ፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅሮች እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራም ይሰራል ተብሏል።

"ከዚህ በኋላ ትጥቃችሁን አስቀምጣችሁ በሰላማዊ መንገድ ከሕዝቡ ጋር መኖር አለባችሁ" በሚልም በመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት ላይ የተደረሰው ይላሉ።

በዚህ ሰነድ ከተካተቱት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል እነዚህ ኃይሎች የኃላፊነት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የከተማ የቤት መስሪያ ቦታ፣ የገጠር የእርሻ መሬት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገኙባቸዋል።

በኃላፊነት ቦታ የሚመደቡት አቅምና የትምህርት ደረጃቸውን ባማከለ መልኩ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው በክልል ደረጃ ሁለት፣ በዞን ደረጃ ሦስት እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ አራት ሰዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ልምድ ያላቸው የቡድኑ አባላት በክልሉ ውስጥ ባሉ የፀጥታ መዋቅሮች መመደብ፣ ሴቶችን አካታች ያደረገና በተለያዩ ማኅበራት እንዲደራጁ ማስቻል፣ በተማሩበት የሙያ መስክ እንዲመደቡ ማድረግና የብድር አገልግሎት እንዲመቻች ማድረግ የሚሉ ሃሳቦች በሰነዱ ውስጥ መካተታቸውን ቢቢሲ ከዞኑ መግለጫ መረዳት ችሏል።

መግለጫው አክሎም የክልሉ መንግሥት ስምምነት ላይ የደረሰው መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት ሰልጠና የሚወስዱ ናቸው ተብሏል።

በትናንትናው ዕለት የስምምነት ሰነዱ ሲፈረም ርዕሰ መስተዳድሩ በሰላም የገቡትን የታጣቂ ቡድን አባላት "የሰላም አምባሳደር" ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ሌሎች ወደ ሰላም ያልመጡ የታጣቂ ቡድን አባላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ይህም ከታጣቂው ቡድን ጋር የተፈፀመው የመግባቢያ ሰነድ ሌሎች አባላትንም ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ሊያበረታታ እንደሚችልም አቶ ኢስሃቅ በበኩላቸው ይናገራሉ።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ከሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየው የመተከል ዞን በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል የክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት በጥምረት የሚመሩት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) በዞኑ ውስጥ ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በክልሉ የተለያዩ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ሲሆን ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ መንገድ ማምጣቱ የዚህ ዘመቻ አካል እንደሆነም ኃላፊው ይናገራሉ።

ከሚካሄዱ ዘመቻዎች መካከል መከላከያ የሚወስደው እርምጃ አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው "የታጣቂ አባላቱን መደምሰስ" የሚገኝበት ሲሆን "ጎን ለጎንም ወደ ሰላም መምጣት የሚፈልጉ ታጣቂዎችም እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ነው" ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት 500 የሚሆኑ አባላት የስልጠና ተሃድሶ እየወሰዱ መሆኑን ገልፀው በጫካ ያሉት የታጣቂ አባላት ቁጥር ሙሉ መረጃ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

የክልሉ መንግሥት ለተገደሉት ንፁሃን ዜጎችና ጥቃቶች ኃላፊነቱ የታጣቂዎቹ ነው ከማለቱ ጋር ተያይዞ እጅ የሰጡት ታጣቂዎት በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ? የሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኃላፊው በቀጣይነት በሕግ አካላት የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት በዋነኝነት እየሩ ያሉት አካባቢውን የማረጋጋትና "በሞት ላይ ዳግሞ ሞት እንዳይመጣ ነው" ይላሉ።

"እነዚህ ታጣቂዎች ጫካ ውስጥ የሚቀመጡ ከሆነ አሁንም ሞት ይቀጥላል። ሰው ማፈናቀሉ ይቀጥላል። ይሄ መቆም ስላለበት የክልሉ መንግሥት እየሰራ ያለው ይሄንን ለማስቆም ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ "በተጨባጭ ሰው እየገደለ፣ ወንጀል መስራቱ በማስረጃ የተደገፈ ካለ" የሕግ አካላት ተከታትለው የተጠያቂነት ሥራ የሚሰሩት ይሆናል ይላሉ።

"እነሱ የራሳቸውን ሕግ የማስከበር ሥራ ያከናውናሉ። በአሁኑ ወቅት እናንተ ሰው አፈናቅላችኋል፣ ገድላችኋል፣ መታሰር ይገባችኋል የምንል ከሆነ ነገሮች ይባባሳሉ እንጂ አይበርዱም። ስለዚህ መሆን ያለበት የሞተ ሞቷል፤ ተጨማሪ ሞት እንዳይከሰትና ሌላ ነገር እንዳይመጣ መሰራት አለበት" ብለዋል።

ታጣቂዎቹ በክልሉ ውስጥ ካሉ ሶስት ዞኖች በካማሺ ውስጥ የሚገኘውን የሴዳል ወረዳ፣ ዲዛን ተቆጣጥሮ እንደነበር በባለፈው ወር ተገልጿል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ምስጋናው እንጂፋታ በወቅቱ እንደገለፁት ከሱዳን 25 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ስፍራ ላይ 'መርሾ' የሚባል ቀበሌ ውስጥ እነዚህ ታጣቂዎች የአካባቢውን ፖሊስ አዛዥ እንዲሁም ሦስት ንፁሃን ዜጎች ገድለው እንደነበር በወቅቱ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለእርሻ የሚውል ሰፊ ለም መሬት ያለበት አካባቢ ሲሆን ለዓመታት የዘለቀው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን እያወዘገበ ያለው በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግዙፉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገኝበት ክልል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ወደ 1.1 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ሕዝብ ይገኛል።