ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፡ ጥቃት የፈጸመው 'የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ' ነው ሲል የክልሉ ፖሊስ ገለጸ

የቤንሻንጉል ክልልን የሚያሳይ ካርታ
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ የተፈጸመበት የካማሺ ዞን ከመተከል ዞን በስተደቡብ የሚገኝ ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ የሴዳል ወረዳ ከተማ የሆነችውን ዲዛንን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ያዋለው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ (ጉሕዴን) መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ገለጸ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ምስጋናው እንጂፋታ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ታጣቂው በክልሉ ውስጥ ካሉ ሦስት ዞኖች በካማሺ ውስጥ የሚገኘውን የሴዳል ወረዳ ከተማን ተቆጣጥሮታል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ካማሺ ዞን ውስጥ የሚገኘው ሴዳል የወረዳ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሰር መዋሉን ቀድሞ ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነው።

ነገር ግን የኮሚሽኑ መግለጫ ታጣቂው ኃይል የተቆጣጠረው ሴዳል ወረዳን ነው ቢልም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ግን ወረዳው ሳትሆን የወረዳው ከተማ ዲዛ መሆኗን ለቢቢሲ ገልጿል።

የሴዳል ወረዳ ላለፉት ሦስት ሳምንታት "ከፍተኛ ስጋት" ውስጥ እንደነበረች የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው እንጂፋታ ለቢቢሲ የገለጹ ሲሆን፤ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ላይ ታጣቂዎቹ ከሰኞ ሚያዝያ 11/2013 ዓ.ም ጀምሮ የሴዳል ወረዳን "ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መቆጣጠራቸውን" ደረሱኝ ያላቸው መረጃዎችን ጠቅሶ ገልጿል።

ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጥቃት ፈጻሚው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲ ንቅናቄ (ጉሕዴን) መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሴዳል ወረዳ ከመለመላቸው በርካታ ወጣቶች ጋር በመሆን ጥቃቱን ፈጽሟል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂው ኃይል ከዚህ ቀደም በመተከል አካባቢ የተለያዩ ጥቃቶች መፈፀሙን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ "የጉሙዝ ሕዝብን ነጻ እናወጣለን" በሚል እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል።

ጉሕዴን ከዚህ በፊት በሕጋዊነት ለመንቀሳቀስ ተመዝግቦ የነበረ ተፎካካሪ ፓርቲ መሆኑን እና በአምስተኛው ምርጫ ላይም የተሳተፈ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ፓርቲው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሙሉ በሙሉ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱንም አብራርተዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከሱዳን 25 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ስፍራ ላይ 'መርሾ' የሚባል ቀበሌ ውስጥ እነዚህ ታጣቂዎች የአካባቢውን ፖሊስ አዛዥ እንዲሁም ሦስት ንፁሃን ዜጎች ገድለው እንደነበር ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ሸሽተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም ይህንኑ አረጋግጦ የሴዳል ወረዳ ከተማ ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር መዋሏንና በዚህም የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም ብሏል።

ቢቢሲ የቡድኑን አመራሮችንም ሆነ አባላት በማግኘት ስለቀረበባቸው ክስና ስለተፈጸመው ጥቃት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከሴዳል ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ምን ይላሉ?

ከሴዳል ወረዳ ሸሽተው በምዕራብ ወለጋ ወደምትገኘው መንዲ ከተማ የሸሹት አቶ ተክሌ ኪባ ማክሰኞ ዕለት ጠዋት ወደ 11 ሰዓት ገደማ ተኩስ መከፈቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ማክሰኞ ጠዋት 11 ሰዓት አካባቢ ተኩስ ተጀመረ። ጦርነቱ ሲጀመር እኛ ቤት ውስጥ ነበርን። ከሁለት ሰዓት እስከ ሶስት ሰዓት ለሚሆን ጊዜ ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላ ማንነቱ ያልታወቀ አካል ቤት ለቤት በመግባት ሰዎችን በማስወጣት ሌሎቹን በመግደል ቀሪዎቹን አርዷል" በማለት የነበረውን ሁኔታ ይናገራሉ።

በከተማው ሆቴል እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ ተክሌ፣ እነዚሁ ታጣቂዎች ወደ ሆቴላቸው በመግባት ተኝተው የነበሩ አስር ሰዎችን ይዘው መሄዳቸውን ተናግረዋል።

"ቤቴን እና በደጃፌ የነበረውን መኪናዬን እሳት ካያያዙበት በኋላ ልጄንና ከእኔ ጋር የነበሩትን ሠራተኞች ይዤ በጀርባ በኩል ወደ ጫካ ሸሸን" በማለት እንዴት እንዳመለጡም ይናገራሉ።

አቶ ተክሌ ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን ከእርሳቸው ጋር ሲሰሩ የነበሩ ሶስት ሰዎች ይዘው ማምለጣቸውን ይናገራሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ 'የበርካታ' ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይናገራሉ።

ይህ የታጠቀ አካል የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር በመስበር፣ የሳድሌ ወረዳ ከተማ የሆነችውን ዲዛ መቆጣጠሩን የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነር ምስጋናው እንጂታ የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ማነስ እንዲሁም የጦር መሳሪያ አቅርቦት እጥረት ለሰላም አስከባሪዎቹ መሸነፍ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የሴዳሌ ወረዳ ነዋሪዎች በታጣቂዎች ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል ቀድሞ መረጃ እንደነበራቸው እና ይህንንም ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ ጥቃቱ የተፈፀመው "ፀረ ሰላም" ባሏቸው ኃይሎች መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህ ታጣቂዎች በአጎራባቹ የመተከል ዞን ውስጥ ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩና አሁን ወደ ሴዳል በማቅናት ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

በታጣቂዎችና በክልሉ የፀጥታ ኃይል መካከል "ከፍተኛ የኃይል አለመመጣጠን አለ" ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በክልል የፀጥታ ኃይል ላይ እንዲሁም በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ታጣቂው ኃይል ያደረሰውን ጉዳት ለመመከት ክልሉ ያሰማራው የፀጥታ ኃይል ጋር በቂ እንዳልሆነ የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ ይህንንም በወቅቱ ባደረጉት ግምገማ ለመከላከያ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ታጣቂው ኃይል በወረዳው ስር ወደሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በሚጠጋበት ወቅት የክልሉ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል ተቀናጅተው ለመመከት ጥረት ቢያደርጉ አለመሳካቱን ገልፀዋል።

አያይዘውም የክልሉ ልዩ ኃይል በሰው ኃይልና በጦር መሳሪያ በአግባቡ አለመደራጀቱን ተናግረዋል።

በካማሺ ዞን የተከሰተው ምንድን ነው?

ታጣቂዎች ለተከታታይ ቀናት በካማሺ ዞን ውስጥ በሚገኘው የሴዳል ወረዳ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ ወረዳዋን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

ስፍራው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደቡባዊ ክፍል ውስጥ የሚገኝ አካባቢ ሲሆን በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ወድቃለች በተባለችው የሴዳል ወረዳ ውስጥ ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

ታጣቂዎቹ በወረዳው ላይ በሰነዘሩት ጥቃትም በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመሸሽ መገደዳቸውን ጨምሮ አመልክቷል።

በጥቃቱም ወረዳውን የተቆጣጠረው ታጣቂ ቡድን የመንግሥት እና የግለሰብ ንብረቶችን ማውደሙን፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የወረዳውን እንዲሁም የዞን አመራሮችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞችን የገደለና ያገተ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ስለሁኔታው ያነጋገራቸው የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች የታጣቂው ኃይል በአቅራቢያ ካለው የመንግሥት ኃይል አቅም በላይ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፍ ለመስጠት ተልኳል የተባለው ተጨማሪ የፀጥታ ኃይልም ወደ ስፍራው እንዳልደረሰ ተናግረዋል ብሏል።

ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው ላይ ጥቃት ፈጽሞ ወረዳዋን በመቆጣጠር ግድያና የተለያዩ ጥፋቶችን ስለፈጸመው ታጣቂ ኃይል ማንነት ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት በአፋጣኝ የአካባቢውና የክልሉን የፀጥታ ኃይል በማጠናከር ተጨማሪ የሰዎች ሞትና የከፋ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከል ጥሪውን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ እንዳለው "ይህ ክስተት በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ" መሆኑን ጠቅሶ ይህም ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር ክስተት መሆኑን አመልክቷል።

ጨምሮም በአካባቢው የተከሰተውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንና ከሚመለከታቸው የፌዴራል እንዲሁም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ መስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን ገልጿል።

የቤኒሻንጉል ክልል መንግሥት ረቡዕ እለት ባወጣው መግለጫ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች ሲከሰቱ "የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተባባሪዎቻቸው ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እና የቀውስ አዙሪት ሊከቱን ጥረት ማድረግ ጀምረዋል" ብሏል።

ጨምሮም እነዚህ አገሪቱን ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ ለመክተት የሚጥሩ ያላቸው ነገር ግን ስማቸውን ያልገለጸው "የጥፋት ቡድኖች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል" ገልጿል።

የፌዴራል መንግሥቱም ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ "ጽንፈኛ ኃይሎች የሚያራምዱትን የጥፋትና የብጥብጥ አጀንዳ ሥርዓት እንዲያስይዝ" ጠይቋል።

ነገር ግን ይህ የክልሉ መግለጫ በካማሺ ዞን ስለተፈጸመው ጥቃት በተለይ ያለው ነገር የለም።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚፈጸሙ ጥቃቶች

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚዋሰነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሦስት ዞኖች የሚገኙ ሲሆን እነሱም መተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ የሚባሉ ናቸው።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰዎች ከሞትና ለመፈናቀል ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል ለረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት የቆየው የመተከል ዞን በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል የክልሉና የፌደራል መንግሥት የጸጥታ አካላት በጥምረት የሚመሩት የዕዝ ማዕከል (ኮማንድ ፖስት) በዞኑ ውስጥ ከተቋቋመ ወራት ተቆጥረዋል።

ከአራት ወራት በፊት ታኅሣሥ 14/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ኢሰመኮን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

ይህንና ሌሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ በክልልና በፌደራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና በርካታ የታጠቁ ሽፍቶች እንደተገደሉ ተገልጾ ነበር።

የክልሉ መስተዳደር ጥቃቱን የሚፈጽሙት "ጸረ ሰላም ኃይሎችና ሽፍቶች" ናቸው ከማለት ውጪ ጥቃቱን የሚፈጽመው ኃይል ምን አይነት ቡድንና አላማው ምን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

ነገር ግን በበርካታ አካባቢዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚገደሉና የሚፈናቀሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ድርጊቱ የብሔር ማንነትን የለየ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለእርሻ የሚውል ሰፊ ለም መሬት ያለበት አካባቢ ሲሆን ለዓመታት የዘለቀው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን እያወዘገበ ያለው በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚገኝበት ክልል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ወደ 1.1 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ሕዝብ ይገኛል።