ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፡ በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ዳሊቲ መንደር ስለተፈጸመው ጥቃት የዓይን እማኞች ምስክርነት

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በደባጤ ወረዳ፣ ዳለቲ በሚባል ሰፍራ ማክሰኞ ጥር 4/2013 ዓ.ም ከ80 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የገለጸ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከዚህ በእጅጉ እንደሚጨምር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ድባጤ ወረዳ ጋሊሳ ቀበሌ ተፈናቅለው የሚገኙ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በወረዳው በሚገኝ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳለቲ በተባለች መንደር ላይ ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉ የ82 ንፁሃን ሰዎችን "አስከሬን አንስተናል" ብለዋል።
ግለሰቡ ከጥቃቱ በኋላ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳትና የሞቱትንም ለማንሳት ወደ ስፍራው ከደረሱ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥርም ከ100 ሊበልጥ እንደሚችል ጨምረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸውና ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቻው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ በቀበሌዋ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦቻቸው በሙሉ እንደተገደሉባቸው ገልጸዋል "እኔ ራሴ 105 አስከሬን አንስቼ መኪና ላይ ጭኛለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማክሰኞ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ2 እስከ 45 ዓመት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች መሆናቸውን አመልክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም በመተከል ዞን ውስጥ ካለፈው ዓመት ማብቂያ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። በተለይ ቡለን በተባለው ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ውስጥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት 207 ንፁሃን ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም ጥቃቱን "ጭፍጨፋ" መሆኑን ገልጸው "በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ" በማለት ሐዘናቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር።
በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂዎች የሚፈፀመውን ግድያ ለማስቀረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የዞኑን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራ ተረክቦ እየሰራ ቢገኝም ጥቃቱ አለመቆሙን ከሰፍራው የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ድባጤ ወረዳ እና በጥቃት የሚናጡት ቀበሌዎቿ
በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ስር በሚገኙት ስምቦሰሪ፣ ቆርቃ፣ አልባሳ፣ ገፈሬ እና ሙዘን ቀበሌዎች ውስጥ ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም እና ኅዳር 5/2013 ዓ.ም ጥቃቶች መፈጸማቸውን እና ሰዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አልባሳ፣ ገፈሬና ሙዘን ቀበሌዎች ውስጥ ኅዳር 5 እና 6/2013 ዓ.ም ጥቃት መፈፀሙን የሚናገሩት ነዋሪ፤ በእነሱም ቀበሌ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ለአካባቢው ኃላፊዎች ከሁለት ወራት በላይ እየገለጹ ቆይተው ጥር 4/2013 ዓ.ም ማክሰኞ ዕለት ዳለቲ ቀበሌ ላይ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎች በአጠቃላይ ተሰባስበው የሚገኙት በጋሊሳ ቀበሌ መሆኑን ገልጸው፤ ለፈናቃዮቹ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥበቃ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ቀበሌዎች ውሰጥ የተለያዩ ብሔሮች ተሰባጥረው እንደሚኖሩ የሚናገሩት ነዋሪዎች ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እንዲሁም የአገው ማኅበረሰቦች በጋራ የሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ላይ ጠቃቱ መድረሱን ተናግረዋል።
የተፈፀመው ማንነትን የለየ ጥቃት እንደሆነ በመግለጽም፣ ለዚህም እንደ ማስረጃ ቤታቸው የተቃጠለባቸውና የሞቱ ሰዎች ከአንድ ወገን መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ግለሰቦቹ ወደ ጋሊሳ ቀበሌ ተፈናቅለው የመጡት ኅዳር 5/2013 ዓ.ም መሆኑን ተናግረው፤ በወረዳው ላለፉት ሁለት ወራት ነዋሪው ያለበትን የደኅንነትና የፀጥታ ስጋት ቢናገርም ሰሚ አለማግኘቱን ይገልጻሉ።
ከአራት ወር ሕጻን ጀምሮ ሴቶች እና አዛውንትን ጨምሮ በርካቶች መገደላቸውን ግለሰቦቹ ያስረዳሉ።
ጥቃቱ የተፈፀመ ዕለት የሆነው ምን ነበር?
ጥር 4/2013 ዓ.ም ሊነጋጋ ሲል 11፡00 አካባቢ ከቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር የሚኖሩ ግለሰቦች የድረሱልኝ ጥሪ ጋሊሳ ቀበሌ ለሚኖሩ ተፈናቃዮች ማሰማታቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የዓይን እማኝ ያስታውሳሉ።
በጋሊሳ ቀበሌ ለሚገኘው የመከላከያ ኃይል ጉዳዩን ማሳወቃቸውንና መኪና ተፈልጎ ወደ ሥፍራው እስኪንቀሳቀሱ ድረስ መርፈዱን በመግለጽ፤ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል ባላቸው መኪኖች ተጭነው የተወሰኑት ደግሞ በእግራቸው ወደ መንደሯ ማምራታቸውን ገልፀዋል።
መንደሯም ከጋሊሳ ቀበሌ በእግር የ3፡30 ተኩል መንገድ መሆኗን የሚገልጹት ነዋሪዎች ለጸጥታ ለኃይሉ ለመሳወቅና ከቦታው እስኪደርስ ድረስ ሰዓታትን ፈጅቷል። በተጨማሪም ቦታው ለመከላከያ ሠራዊት አዲስ በመሆኑ መንገድ በመምራት ወደ ቀበሌዋ እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
ረፋድ ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ ሲደርሱ በመንደሯ የሚገኙ ቤቶች በእሳት ተኩሰው አየሩ በጭስ ተሸፍኖ ከሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ታጣቂዎች ከበባ በመፈፀም ተኩስ ይሰማ እንደነበር ያስታውሳሉ።
"የመከላከያ ሠራዊቱም ከታጣቂዎች ጋር ተኩስ ገጥሞ የተወሰኑትን መማረኩን እንዲሁም የተወሰኑ ደግሞ መግደሉን" በአካባቢው ነበርኩ ያሉ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሉ በቦታው እንደደረሰ በርካታ ንፁሃን ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለው የተወሰኑት ደግሞ ቆስለው የተገኙ ሲሆን፤ የቆሰሉት የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ወደ ጤና ተቋም መወሰዳቸውን አክለው ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊትም በጥቃቱ የተገደሉትን ሰዎች አስከሬን በሁለት አይሱዙ የጭነት መኪኖች መሰብሰቡንና ቢቢሲ ግለሰቡን እስካናገረበት ረቡዕ አመሻሽ ድረስ ሳይቀበሩ መቆየታቸውን የዓይን እማኙ ገልፀዋል።
ሌላ የዓይን እማኝ በደግሞ "ቦታው ላይ በመገኘት ያየሁት እና መኪና ላይ የጫንኳቸው በአጠቃላይ 82 አስከሬኖችን ቆትሬያለሁ" ሲሉ አስከሬኖቹም ወደ ጋሊሳ ቀበሌ መምጣታቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው የአይን እማኝ በበኩላቸው "እኔ ራሴ 105 አስከሬኖችን" መኪና ላይ ጭኛለሁ ሲሉ ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ከዚያ በኋላ መከላከያ ተጨማሪ አስከሬኖችን ማንሳቱን መስማታቸውና በአጠቃላይ በጥቃቱ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር መስማታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ግለሰቦቹ አክለውም ነዋሪዎች ጥቃት ሸሽተው ከሙዘን፣ አልባሳ፣ ገፈሬ ቀበሌዎች ሲፈናቀሉ አስከሬኑ አለመነሳቱን ያስታውሳሉ።
በአሁኑ ጊዜ "የመተከል ዞን በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ፣ ሰላም መሆኑ እየተነገረ እያለቅን ነው። አስከሬኑን ይዘን ለሰሚ አካል አቤት እንላለን" ያሉ ተፈናቃዮች ንዴትና እሮሯቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ ማሰማታቸውን የዓይን እማኙ ይናገራሉ።
በጥቃት ፈጻሚዎቹ ኢላማ ያደረጓቸውን ሰዎች በስለት፣ በጥይትና በቀስት እንደገደሏቸው አስከሬኖቹን የሰበሰቡት የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጋሊሳ ቀበሌ የሚኖሩ ተፈናቃዮች አሁንም ፍርሃት እንዳላቸው ገልፀው፣ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ከሌለ "ታጣቂዎቹ መጥተው ይገድሉናል" ሲሉ ይሰጋሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው ቡድን ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስታውቆ ነበር።
ግብረ ኃይሉ እየወሰድኩት ነው ባለው እርምጃ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የመንግሥት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢዜአ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ካለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር አንስቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም የቆ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ሲሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
















