አደይ አበባ፡ አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? ለምን በአዲስ ዓመት?

የክረምቱ ወቅት ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ አንስቶ የዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ጋራና ሸንተረሩ አረንጓዴ ከመልበሱ ባሻገር የተለየ ሕብር የሚፈጥረው አደይ አበባ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አብሳሪ ነው።
በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ አደይ አበባ የአዲስ ዓመት አብሳሪ የመስከረም ወር መለያ ተደርጎ ይወሰዳል። ለበርካቶች የመስከረም ወር፣ የመስቀል ደመራና አዲስ ዓመት ከአደይ አበባ ውበትና መዓዛ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው።
እንዲያውም አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እፅዋት፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ መለያ የሆነ ያህል ጠንካራ የስሜት ትስስር ተፈጥሯል።
በእርግጥ አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? ለምን በአዲስ ዓመት? ሳይንሱ ምን ይላል?
አደይ አበባ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዝሃ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአማርኛ አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ፣ በኦሮምኛ 'ኬሎ'፣ በትግርኛ ደግሞ ገልገለ መስቀል ተብለው የሚጠሩት የእፅዋት ዓይነቶች በሳይንስ መጠሪያቸው 'ባይደንስ' እንደሚባሉ ያስረዳሉ።
የእነዚህ እፅዋት ቤተሰቦችም 'አስትሬይሲያ' ወይም 'ኮምፖሲታይ' ይባላል።
ተመራማሪው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ሃያ የሚሆኑ የባይደንስ ዝርያዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል 'ባይደንስ ማክሮፕተራ'፣ 'ባይደንስ ፕሬስቲናሪያ' እና 'ባይደንስ ፓክሎማ' የተባሉት ዝርያዎች ብርቅዬና ሰፊ ሥርጭት ያላቸው ናቸው።
እነዚህን ሦስት ዝርያዎች በደንብ ቀረብ ብለው ካላይዋቸው ወይም በጥናት ካልተለዩ በስተቀር ለዕይታ የመመሳሰል ባህርይ አላቸው ይላሉ- ፕሮፌሰሩ።
እንደ ተመራማሪው ከሆነ 'ባይደንስ ማክሮፕተራ' የሚባለው ዝርያ የሚገኘው በኢትዮጵያ ብቻ ነው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችም ይበቅላል። 'ማክሮፕተራ' የተባለው ዘሩ ክንፍ የመሰለ ትንሽ ነገር ስላለው ነው። ዝርያውን መለየት የሚቻለውም ይህንኑ ክንፍ በማየት ነው።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው 'ባይደንስ ማክሮፕተራ' ነው የተባለው ፤ 'ባይደንስ ፕሬስትራኒያ' የተባለው ዝርያ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ሱዳን ውስጥ ስለሚበቅል እንጂ እርሱም ቢሆን ሌላ አገር ውስጥ አይገኝም።
በመሆኑም 'ማክሮፕተራ' በኢትዮጵያ ብቻ ስለሚገኝ 'ብርቅዬ' ሲባል 'ፕሬስትናሪያ' ደግሞ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሱዳን ስለሚገኝ 'የቅርብ ብርቅዬ' እንደሚባል ፕሮፌሰር ሰብስቤ ያስረዳሉ።
'ባይደንስ ፓክይሎማ' የተባለው ዝርያ ግን አፍሪካ ውስጥ በብዛት ይገኛል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ [ባይደንስ ማክሮፕተራ] በዓለም ብርቅዬ እፅዋቶች መዝገብ ውስጥ አይስፈር እንጂ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የመጤዎችና አገር በቀል እፅዋቶችን መረጃ የያዘ ጥራዝ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዋል።
የሰይጣን መርፌ (ባይደንስ ፒሎሳ)
ከሃያዎቹ የባይደንስ ዝርያዎች መካከል አንዱ 'ባይደንስ ፒሎሳ' ይባላል። ይህ የአደይ አበባ ዝርያ ቀለሙ ነጭ ነው። የሚበቅለው ግን ቢጫው አደይ አበባ በሚበቅልበት ወራት ነው። በተለምዶ 'የሰይጣን መርፌ' ይባላል።
"የሰይጣን መርፌ የተባለው ጫፉ ላይ እሾህ መሳይ ነገር ስላለውና በቀላሉ ስለሚጣበቅ ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።

የፎቶው ባለመብት, GASHAW LENE
ለመሆኑ የሱፍ አበባ እና የአደይ አበባ ዝምድና አላቸው?
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት ኑግ፣ ሱፍና ግራዋ የአደይ አበባ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
ሁሉም የሚገኙት 'አስትሬይሲያ' በሚባል የእፅዋት ቤተሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ የቤተሰብ አባላት በብዛት የሚገኙትና የሚስፋፉት ብዛት ያላቸው ዘሮችን ስለሚያፈሩ ነው።
አደይ አበባ ዓይናችንን የሚስበውም የተለያዩ ዝርያዎች ብዙ ዘሮች ኖሯቸው በአንድ ላይ ሲያብቡ ብዙ ስለሚሆኑ ነው።
ከዚህም ባሻገር የየአካባቢው ባህል እንዲሁም ሐይማኖታዊ በዓላት ይበልጥ እንዲጎሉ አድርጓቸዋል።
"እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ እፅዋት ቤተሰብ አለው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እነዚህ ዝርያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ናቸው ይላሉ። እንደ ተመራማሪው ከሆነ በቁጥር ምን አልባት የአተር ዝርያዎች ቢበልጧቸው ነው።
አደይ አበባ የመስከረም ጌጥ ነው። በተለይ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ታዳጊዎች ይህ ወቅት የሚቦርቁበት ነው።
በአረንጓዴ የተሸፈነው ለምለም ሜዳ በአደይ አበባ ተቀይጦ አንዳች ውበትን ያላብሳል። ወደ መስክ ወርዶ አደይ አበባ መልቀም የተለመደ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በከተሞች አካባቢ አደይ አበባ በቀሚስ እና በካናቴራ ላይ ታትሞ አሊያም ተጠልፎ እስከመቸብቸብ ደርሷል።
አደይ አበባ ውበት ብቻም አይደለም። የእለት ጉርስም ይሆናል። እናቶች፣ ወጣቶች ኑሯቸውን ለመደገፍ ከቄጠማ ጋር ቀላቅለው ይሸጡታል።
የመስቀል በዓል ላይ ደመራውን ከሚያስውቡት አንዱ አደይ አበባ ነው። ጫፉ ላይ ከቄጠማ ጋር ይታሰራል። ከደመራው ሥርም ይጎዘጎዛል።
በኦሮሞ ማሕበረሰብ ዘንድ በድምቀት በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓልም የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ወደ በዓሉ ቦታ የሚያመሩት አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው ነው።
በተፈጥሮ በለመለመው ሳርና በፈካው አበባ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑበታል። ልምላሜንና በጎ ምኞታቸውንም ይገልጹበታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አደይ አበባ በአንዳንድ አካባቢዎች ከነሐሴ ወር መገባደጃ ጀምሮ ጳጉሜን ይዞ በየጫካውና በየጥሻው ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራል።
መስከረም አንድ ብሎ ከጀመረ በኋላ እስከ ኅዳር ድረስ ግን መስኩ፣ ተራራው፣ ሜዳው በዚሁ አበባ ያሸበርቃል። ቢበዛ ከሦስት ወራት በኋላ ግን አደይ አበባን ማግኘት ዘበት ነው።
'የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ' እንዳለው ገጣሚው።
አደይ አበባ ለምን በእነዚህ ወራት ብቻ ታይቶ ይጠፋል?
ፕሮፌሰር ሰብስቤ የአደይ አበባንና የመስከረምን ቀጠሮ የሚያመሳስሉት ከሰዓት ጋር ነው።
"ማታ ተኝተን ጠዋት እንድንነቃ ሰዓት እንሞላለን፤ ልክ እንደዚያው እፅዋት የራሳቸው ጉዳዮች ከተሳካላቸው፣ የሚፈልጉትን ያህል ዝናብና ፀሐይ ካገኙ 'አሁን ነው የምታብቡት' በሚል ውስጣዊ ግፊት ያብባሉ" ይላሉ።
ይህም 'ባዮሎጂካል ክሎክ' በመባል ይታወቃል።
አበቦቹ ምንም እንኳን ማበቢያ ጊዜያቸው አዲስ ዓመትን ተንተርሶ ቢሆንም እንዲያብቡ የሚያደርጋቸው ግን ውስጣዊ ባህርያቸው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
"ግንዳቸው ጠንከር ያላሉት የአደይ አበባ ዝርያ ዓይነቶች ለማበብና ለማፍራት ባላቸው ተፈጥሯዊ ሒደት አንድ ዓመት ይቆያሉ" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
ከዚያም ለውስን ጊዜያት አብበው ይሞታሉ። ይሞታሉ ሲባል ይጠፋሉ ማለት ሳይሆን ዘራቸው መሬት ውስጥ ይገባል ማለት ነው።
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት አደይ አበባ መሃል ላይ ያለው ፍሬው የእሾህነት ባህርይ ስላለውና በብዛትም ስለሚመረት በቀላሉ መሬት ውስጥ ለመግባት ያስችለዋል።
መሬት ውስጥ ሲቆይ ልክ ጉንዳን ለክረምት ምግብ እንደሚሰበስበው ሁሉ አደይ አበባም ለዘር የሚያበቃውን ምግብ ይዞ ይቆያል።
"አመቺ ሁኔታ ሲያገኝ፣ ዝናብ ሲዘንብ፣ ከዚያም ፀሐይ ሲወጣ፤ 'አሁን ነው ማበብ ያለብህ' የሚል የተፈጥሮ ግፊት ይገፋፋዋል። ይህ የተፈጥሮ ባህርያቸው ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
አደይ አበባ ዓመቱን ሁሉ ማበብ ይችላል የሚሉት ተመራማሪው፤ የመስከረም ወር ግን ለእነዚህ ዝርያዎች ይበልጥ አመቺ ነው ይላሉ።
አደይ አበባን ልዩ የሚያደርገውም ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እና ተከታትለው ከሚመጡ በዓላት ጋር መገናኘቱ ነው።
"አደይ አበባ እና የዘመን መለወጫ መገጣጠም ግን ያጋጣሚ ጉዳይ ነው" ብለዋል ተመራማሪው።
በኢትዮጵያ አደይ አበባ የማይበቅልበት ቦታ አለ?
ተመራማሪው እንደሚሉት አደይ አበባ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ይበቅላል።
ይሁን እንጂ በመሬት አቀማመጥ ከፍታና ዝቅታ መጠኑና ቆይታው ሊለያይ ይችላል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው 'ባይደንስ ማክሮፕተራ' በብዛት የሚገኘው ከመሬት ወለል በላይ ከ2000 እስከ 3600 ሜትር ከፍታ ባሉ ደጋማ አካባቢዎች እንደሆነ ተመራማሪው አስረድተዋል። ከ1750 ሜትር በታች ባሉ አካባቢዎች ግን አይበቅልም።
የእፅዋት ሥርጭት ከመሬት ወለል በላይ ባለ ከፍታ ይወሰናል የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ አደይ አበባ በትግራይ፣ በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሐረር፣ ደሴ፣ ወለጋ፣ ነቀምት፣ ጂግጂጋ እና ሌሎች ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ይበቅላል ይላሉ።
"ለምሳሌ አፋር ውስጥ ከፍተኛ ተራራ ላይ ሊገኝ ይችላል። ወደ ዳሎል ወረድ ሲባል ግን ሊገኝ አይችልም" ሲሉም ያስረዳሉ።
አደይ አበባ ከውበትና ከድምቀት ሌላ . . .
አደይ አበባ ውበቱ፣ ለሥነ ምኅዳሩ፣ ለሐይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ያለው አስተዋፅኦ ራሱን የቻለ እሴት ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
ከዚህ ባሻገር ግን የመድኃኒትነት ባህርይ ያላቸው የአደይ አበባ ዝርያዎች እንዳሉም ተናግረዋል።
በተለምዶ 'የሰይጣን መርፌ' ተብሎ የሚጠራው የአደይ አበባ ዓይነት በባሌ አካባቢ ሰው በእባብ ሲነድፍ በባህላዊ እውቀት ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀሙበት ምሳሌ አጣቅሰዋል።
"ምንም እንኳን በተፈጥሮ የተሰጠን ፀጋ እና በረከት በገንዘብና በአገልግሎት መመዘን ብቻ ተገቢ ባይሆንም፤ ኬሚካላዊ የሆነ ባህርያቸውን አልሰራንባቸውም እንጂ ቀለሙ ቢመረመር ማቅለም የሚችል ይመስለኛል" ይላሉ ተመራማሪው።
አንዳንድ ጥናቶችም አደይ አበባ ለስኳር በሽታ እና ለጭንቅላት ካንሰር ሕክምና መዋል እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
ኢኮኦፒያ የተባለ በኢትዮጵያ ያለ ድርጅትም ከአደይ አበባ የተሠራ የውበት መጠበቂያ ክሬም ለገበያ እንዳበቃ መዘገቡ ይታወሳል።
ምክረ ሃሳብ
ኢትዮጵያ እንደ አደይ አበባ መጠሪያዋ የሆኑ ብርቅዬ እፅዋቶች እንዳሏት የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ ልክ እንደ ብርቅዬ እንስሳት ሁሉ እነዚህን እፅዋት ለመጠበቅና ለማክበር አንዱ ዝርያ ተመርጦ 'አገራዊ አበባ' ቢደረግ የሚል ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።














