ዝማሬዋ የጠፋባት ወፍ በአውስትራሊያ

የፎቶው ባለመብት, David Stowe
አውስትራሊያ ውስጥ በዝማሬዋ ትታወቅ የነበረች ብርቅዬ የወፍ ዝርያ በድንገት ዝማሬዋ ጠፍቶባት የተምታታና ለዛ የሌለው ዜማ እያሰማች ነው።
'ዘ ሬጀንት ሐኒ ኢተር' ተብላ የምትጠራዋ ወፍ በዓለም ለመጥፋት ከተቃረቡ የወፍ ዝርያዎች መካከል አንዷ ናት።
ከዘመናት በፊት የእሷ ዝርያ ወፎች በደቡብ ምሥራቅ አውስትራሊያ በብዙ ቁጥር ይኖሩ ነበር። አሁን ግን ከዛሬ ነገ ዝርያቸው ለዘላለሙ ይጠፋል ተብለው ከተሰጋላቸው ወፎች መካከል ሆናለች።
አሁን በዚህ 'ሬጀንት ሐኒ ኢተር' ዝርያ ውስጥ ከሚገኙ ወፎች ተደምረው በሕይወት የቀሩት 300 ብቻ ናቸው።
"ይህች ወፍ ለጊዜው ከዝርያዎቿ ጋር አብሮ ጊዜ ለማሳለፍ ዕድሉን አላገኘችም ነበር፤ ለዚያ ይሆናል ዝማሬዋን የዘነጋችው" ብለዋል ዶ/ር ሮዝ ክሬተስ።
ዶ/ር ሮዝ በአውስትራሊያ ካንቤራ ዩኒቨርስቲ አንድ የወፍ ዝርያዎች የጥናት ቡድን ውስጥ የሚሠሩ ሲሆን ዝማሬ የጠፋባትን ወፍ የዘመዶቿን የዝማሬ ቅኝት እያስተማሯት ይገኛሉ።
እነዚህ የወፍ ዝርያዎች በምድር ላይ ጥቂት የቀሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በአንድ አካባቢ አለመገኘታቸው ፈተና ሆኗል።
በጉዞ የሚሸፍኑት ቦታ ስፋት የታላቋ ብሪታኒያን ሦስት እጥፍ ይሆናል፤ ከዚህ ሁሉ ሰፊ ቦታ እነዚህን ዝርያዎች መፈለግ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ የማሳለፍ ያህል ከባድ ሆኗል።
ወፎች ዝማሬ የሚማሩት የሰው ልጆች ቋንቋን በሚማሩበት መንገድ ነው።
"ገና ትንሽ ወፍ ሳሉ የወፍ ጎጇቸውን ጥለው ይወጡና ከዝርያዎቻቸው ጋር መዋል ይጀምራሉ። ታላላቆቻቸው ሲዘምሩ ይሰሙና ያንን ይደግማሉ፤ ዝማሬ የሚማሩትም በዚህ መንገድ ነው" ይላሉ ዶ/ር ሮዝ።
አሁን ትልቁ ፈተና የሚዘምሩ ወፎች በተመሳሳይ ስፍራ ባለመሆናቸው አንዱ ከሌላኛው ዝማሬ ሰምቶ መቅዳትና መማር አልሆንላቸው ማለቱ ነው።
ወፎችን ዝማሬን በክፍል ውስጥ ማስተማር
ሳይንቲስቶች አሁን ከወፎች የቀዷቸውን ዝማሬዎች ዜማ ለተቃወሰባቸው ወፎች እያስደመጡ 'መሠረተ ዜማን' እያስተማሩ ይገኛሉ።
ዝርያቸው እየተመናመኑ ያሉትን ወፎች በቤተ ሙከራ እያባዙ ወደ ጫካ መልቀቅ ፕሮጀክት በሙከራ ላይ ሲሆን ይህም ምናልባት የወፎቹን ዝርያ ጨርሶውኑ ከመጥፋት ይታደጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ነገር ግን ወፎቹ ዜማቸው ማራኪ ካልሆነ ሴት ወፎች ከእነሱ ጋር መገናኘት አይፈልጉም። እነ ዶ/ር ሮዝ ወፎቹን መሠረተ ዜማ እያሰለጠኑ የሚገኙትም ይህን ችግር ለመቅረፍ ነው።
















