በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው አምስት የዱር እንስሳት ዝርያዎች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, EWLA/Getty Images
ኢትዮጵያ በዱር እንስሳት ሀብት ስብጥር ስሟ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትነሳ አገር ናት። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በሚገኙ የዱር እንስሳቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን የዱር እንስሳት ባለሙያው አቶ ጨመረ ዘውዴ ያስረዳሉ።
የዚህ ስብጥር ምክንያት ያሉትንም ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ሲያስረዱ የአገሪቱ የመሬት አቀማመጥ፣ አዋሳኝ አገራት፣ ከደጋ እና ቆላ መካከል የምትገኝ አገር መሆኗ የዱር እንስሳት ስብጥር በርከት ብሎ የሚገኝባት እንዳደረጋት ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ቀጭኔን ኢትዮጵያ ውስጥ ማየት ቀላል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ፈተና ሆኗል። ቀይ ቀበሮዎች በሰሜንና በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮች፣ በሰሜን ወሎ አቡነ ዮሴፍ ተራራ ላይ እና በመንዝ ገሳ አካባቢ ይገኝ ነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቁጥሩ ተመናምኖ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው እንስሳት መካከል ስሙ ሰፍሮ ይገኛል።
ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ስሟን ሊያስጠራ የሚችል የዱር እንስሳት ሀብት ቢኖርም የአብዛኞቹ ይዞታ ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየተመናመነ መምጣቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር መኮንን በኢትዮጵያ የዱር እንስሳቱ የመኖሪያ አካባቢያቸው በትክክል ባለመጠበቁ እና በመረበሹ የመራባት ዕድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱም ለመጥፋት የተጋለጡ እንዳሉ ያስረዳሉ።
ለመሆኑ በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው የዱር እንስሳት መካከል አምስቱ የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Wild Life Authority
የስዋይን ቆርኬ (የኢትዮጵያ ቆርኬ)
ይህ እንስሳ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ የዱር እንስሳ ነው። ቀደም ሲል በአምስት የተለያዩ ጥብቅ ስፍራዎች ይገኝ ነበር ያሉት አቶ ጨመረ፤ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ ያቤሎ የዱር እንስሳት መጠለያ፣ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የነበሩት ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸውን ተናግረዋል።
የስዋይን ቆርኬ (የኢትዮጵያ ቆርኬ) አሁን በደህና ቁጥር የሚገኘው በሻሸመኔ አቅራቢያ ስንቅሌ በሚባል ቦታ በሚገኝ የቆርኬ መጠለያ ውስጥ ነው። በደቡብ ክልል በሚገኘው ማጎ ብሔራዊ ፓርክም እንደሚገኝ አቶ ጨመረ ጠቅሰዋል።
ትልቁ የሜዳ አህያ (ግሬቪ ዜብራ)
በኢትዮጵያ ሦስት አይነት የአህያ ዝርያዎች አሉ የሚሉት አቶ ጨመረ ከሦስቱ የአህያ ዝርያዎች መካከል ትልቁ የሜዳ አህያ አንዱ ነው።
ይህ የአህያ አይነት ዝርያው በከፍተኛ ሁኔታ እየተመናመነ መሆኑንም ባለሙያው አክለው ገልፀዋል።
በዓለም ላይ የዚህ አህያ ዝርያ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ ተናግረው፣ በኢትዮጵያ ቁጥሩ በጣም እየተመናመነ አነስተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላሉ።
እነዚህ እንስሳት የተለየ ጥበቃ እስካልተደረገላቸው ድረስ "ከአለን ወደ ነበረን" የምንሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ጥቁር አውራሪስ
በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት የአውራሪስ ዝርያ (ነጭና ጥቁር) እንደሚገኝ የሚናገሩት ዶ/ር መኮንን፤ ለቀንዱ በሚል ብቻ ከፍተኛ ጥቃት እንደሚደርስበት ያስረዳሉ።
በኢትዮያ ውስጥ ጥቁር አውራሪስ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን "አለ ከማይባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል" ይላሉ።
አቶ ጨመረ ስለ አውራሪስ ሲናገሩ "ስሙ ብቻ ነው የቀርን እንጂ እንስሳው የለም" በማለት ነው።
ባለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት አውራሪስን አጥተናል የሚሉት አቶ ጨመረ በተደረጉ በርካታ ጥናቶች አንድም ቦታ ላይ ሊገኝ አልቻለም ብለዋል።
ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩት ዶ/ር መኮንን፣ አውራሪስ ኢትዮጵያ ውስጥ ታየ የሚባለው በኦሞ ሸለቆ ውስጥ እኤአ በ1985 መሆኑን ይናገራሉ።
በርግጥ አሁንም በዚህ አካባቢ አለ የሚል ወሬ ቢኖርም ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ በመግለጽ፣ በዚህም ምክንያት አውራሪስ ከኢትዮጵያ እንደጠፋ ነው የምንገምተው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Education Images
ቀይ ቀበሮ (አቢሲኒያ ዎልፍ)
ቀይ ቀበሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ የዱር እንስሳ ነው።
ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የቀበሮ ዝርያ በዓለም ደረጃ ለመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ሥጋ በል የዱር እንስሳት መካከል አንዱ ነው።
ቀይ ቀበሮ በኢትዮጵያ ሰባት ስፍራዎች ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየተመናመነ መጥቶ፣ በአሁኑ ሰዓት ከ450 የማይበልጥ ብቻ እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል።
እንደ ዶ/ር መኮንን ከሆነ ለእነዚህ እንስሳት መጥፋት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በሽታ ነው።
ምንም እንኳ እነዚህን የቀበሮ ዓይነቶች አምስት አይነት በሽታ ቢያጠቃቸውም፣ በተለይ የእብድ ውሻ በሽታ በአካባቢው ከሚኖሩ ውሾች በቀላሉ ወደ እንስሳቱ እንደሚተላለፍ እና ለሞት እንደሚዳርጋቸው ተናግረዋል።
ቀይ ቀበሮዎች አኗኗራቸው በሕብረት ስለሆነ ከመካከላቸው አንድ ቀበሮ በበሽታው ከተያዘ ቀሪዎቹ ለበሽታው በቀላሉ ይጋለጣሉ ሲሉም ያክላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Cameron Spencer
ዝሆን
ዶ/ር መኮንን ዝሆን በመላው አፍሪካ በሰው ልጆች አማካኝነት ጥቃት ከሚደርስባቸው የዱር እንስሳ መካከል አንዱ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ካሏት የዝሆን ሀብት መካከል 80 በመቶ ያህሉን ማጣቷን ጥናቶች ያመለክታሉ ሲሉ አቶ ጨመረ ይናገራሉ።
ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩት ዶ/ር መኮንን ኢትዮጵያ ከ1980ዎቹ ወዲህ 80 በመቶ ያህል የሚሆነውን የዝሆን ሀብቷን አጥታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አይነት የዝሆን ንዑስ ዝርያ አለ እንደሚባል የሚገልፁት አቶ ጨመረ፤ የባቢሌ የዱር እንስሳት መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች በየዓመቱ ቁጥራቸው እየቀነሰ መሆኑን ያሰታውሳሉ።
በኦሮሚያ ጉጂ ውስጥ ከ20ዎቹ በታች በሆነ ቁጥር ዝሆኖች እንደሚገኝ በመግለጽ፣ በዚህ ሳምነት እንኳ ሦስት ዝሆኖች እንደተገደሉ መስማታቸውን ተናግረዋል።
በዝሆን ሀብቱ የሚታወቀው ኦሞ ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥም ከዕለት ወደ ዕለት የዝሆኖች ቁጥሩ እየተመናመነ መምጣቱንም ይጠቅሳሉ።
ዝሆኖች አሁን በተሻለ ቁጥር ይገኛሉ የሚባለው ትግራይ ውስጥ ቃፍታ ሽራሮ እንዲሁም ባቢሌ እንዲሁም በትንሽ ቁጥር ኦሞ ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ መሆኑን ይናገራሉ።
አእዋፋት
የአቢያታ ሻላ ሐይቆች ፓርክ ከሰሜን ዋልታ የሚመጡ አእዋፋት የሚታዩበት ስፍራ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚመጡ ወደ 241 ያህል ገደማ ተጓዥ አእዋፋት መኖራቸውን፣ ወደ 20 የሚጠጉ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አእዋፋት እንደሚገኙ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ከ30 ዓመት ወዲህ በደረሰው የሰው ሰራሽ ጫና የሐይቆቹ የውሃ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ አእዋፋቱ መኖሪያ እና የሚመገቡት እያጡ ቁጥራቸው ቀንሶ ነበር።
ነገር ግን ከሁለት ዓመት ወዲህ የሐይቆች ውሃ እየጨመረ በመሆኑ አእዋፋቱ እየተመለሱ ነው ይላሉ።
መፍትሄ
የዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን በዓለም ላይ ያለ ክስተት ነው። በዚህም የተነሳ በአህጉራችን አፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ይገኛል።
ለዚህ ደግሞ የተለያየ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ቀዳሚው የሕዝብ ብዛት ጨመር መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ሌላው ለዱር እንስሳቱ ቁጥር መቀነስ እንደምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ መኖሪያቸው እየተጣበበ መምጣቱ ነው። ሕገወጥ አደን ያለባቸው አካባቢዎችም ለዱር እንስሳቱ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መመናመን እና መጥፋት ተጠቃሽ ምክንያት ሆኖ ይገኛል።
የኢንቨስትመንቶች መስፋፋት፣ የዱር እንስሳት አካባቢዎች መበጣጠስ እንዲሁ ለእንስሳቶቹ ቁጥር መመናመን እና ብሎም መጥፋት የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ይላሉ ባለሙያዎቹ።
"የዱር እንስሳትን የምንጠብቀውና የምንንከባከበው ስለሚያምሩ ወይንም ፍጡር ስለሆኑ ብቻ አይደለም" የሚሉት አቶ ጨመረ "ለሰው ልጆች ሕልውና መቀጠል አስፈላጊ በመሆናቸው ነው" ብለዋል።
የዱር እንስሳት መኖር ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቦ፣ መንግሥት በመላ አገሪቱ ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንዲያበጅም ይመክራሉ።
ወጥ የሆነ የመሬት ፖሊሲ ሲኖር ለደን፣ ለልማት፣ ለዱር እንስሳት መኖሪያ የሚለውን በአግባቡ መከለል ይቻላል ሲሉ ይመክራሉ።
የዱር እንስሳቱ በሚኖሩበት ስፍራ የሚገኙ ማኅበረሰቦችንም የመሰረታዊ ፍላጎት ማሟያ አማራጭ መንገዶችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ሲሉም ይናገራሉ።
"የዱር እንስሳት የአገር ቅርስ የትውልድ ውርስ ናቸው" የሚሉት አቶ ጨመረ በገንዘብ የማይተኩትን እነዚህን የተፈጥሮ ቅርሶች እንዳይጠፉ በመጠበቅና በመንከባከብና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ አሁን ካለው ትውልድ ይጠበቃል ይላሉ።















