ተፈጥሮ ፡ እውቅና ሳያገኝ ለአደጋ የተጋለጠው የሃላይ ደጌ አሰቦት ጥብቅ ደን

የሜዳ አህያ

የፎቶው ባለመብት, Asebot Alledeghi National Park Facebook

የሃላይደጌ አሰቦት "ብሔራዊ እጩ ፓርክ" በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ብርቅዬ የሆኑ እንስሳትን በውስጡ የያዘ ነው። ከ1960ዎቹ ጀምሮ በጥብቅ ደንነት የኖረው ፓርኩ፣ በብሔራዊ ፓርክ ደረጃ አለማደጉ ግን በበጀትና በአስተዳደር የተደረጃ እንዳይሆንና ለሕገ ወጥ ድርጊት ተጋላጭ አድርጎታል።

በአፋርና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሃላይደጌ አሰቦት ፓርክ፣ 1 ሺህ 90 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እንደሚሸፍንና በርካታ እንስሳትንና የእጽዋት ዝርያዎችን ያቀፈ መሆኑን የፓርኩ ኃላፊ አቶ መቆያ ማሞ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደሃላፊው ገለጻ በፓርኩ ውስጥ 42 አጥቢ የዱር እንስሳት፣ ከ240 በላይ አዕዋፋት እና ከ260 በላይ ደግሞ የዕጸዋት ዝርያዎች ይገኙበታል። አብዛኞቹ እንስሳት ጎብኚዎች ሊያይዋቸው የሚፈልገጨውና ምናልባትም በአፍሪካ ደረጃ በብዛት በዚሁ ፓርክ የሚገኙ መሆናቸውን አቶ መቆያ ይገልጻሉ።

ፓርኩ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ 280 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ፣ ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ብዙም ያልራቀ ምቹ የጉብኝት አካባቢ መሆኑን ኃላፊው ያብራራሉ።

ፓርኩ በብሔራዊ ፓርክ ደረጃ ተመዝግቦ አስፈላጊው የአስተዳደርና የጥበቃ ሁኔታ እንዲሟላላት ጥያቄ ማቅረብ የተጀመረው ከስድስት ዓመታት በፊት በ2006 ዓ.ም ነበር። ነገር ግን እስካሁን ጥያቄው ምላሽ አላገኘም።

በወቅቱ ሁሉንም መስፈርቶች በማሟላት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ይሁንታን በማግኘት እውቅናውን ለማሰጠት ሂደቱ መጀመሩን አቶ መቆያ ያስታውሳሉ። ከሃላይደጌ አሰቦት ጋር ሰባት ፓርኮች ወደ ብሔራዊ ፓርክነት ለማደግ ጥያቄ ቢያቀርቡም እነሱ ግን እስካሁን እውቅና አላገኙም።

"ሰነድ በማዘጋጀት ረገድ የሚጠበቅብንን ሁሉ አጠናቀናል" የሚሉት አቶ መቆያ፣ "ሰነዱ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስፈላጊው ምርመራና ማሻሻያ ተደርጎበት አስተያየት እንድንሰጥ ተመልሶልናል" ይላሉ።

የያንጉድራሳ ብሔራዊ ፓርክ ከሃላይ ደጌ አሰቦት ፓርክ በቅርብ ርቀት ስለሚገኝ፣ የሃይላደጌ አሰቦት ፓርክን በሞግዚትነት ያስተዳድረው ነበር። የያንጉድራሳ ብሔራዊ ፓርክ ቀደም ሲል በፌደራል መንግሥት ሥር ይተዳደር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን የአፋር ክልል በራሱ ሊያስተዳደረው ሂደቶች እየተጠናቀቁ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ የሃላይ ደጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ ብቻውን ያለ ጠባቂ ይቀራል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

በዚህ ምክንያትም ጥበቃው ያልተጠናከረ ከመሆኑ አንጻር የዱር እንስሳቱ ለሕገ ወጥ አደን ይጋለጣሉ፣ ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትም ሊስፋፉ ይችላሉ የሚለው ስጋትም አለ። አብዛኞቹ የአካባቢው የዱር እንስሳት አነስተኛ ዝርያ ያላቸውና በመጥፋት ላይ ያሉ በመሆናቸው እነዚህ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ከነጭራሹ የመጥፋት አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል የሚለውም ሌላኛው ስጋት ነው።

በአፋር በኩል የዱር እንስሳትን የመጠበቅ ጥሩ ልምድ መኖሩ ለፓርኩ ሕልውና አንዱ እድል ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ግን እነዚህን እንስሳት አንዳንድ ሰዎች ለመድኃኒትነትና ለሌሎች ጉዳዮች ስለሚፈልጓቸው በሕገ ወጥ አደን ሊያጠፏቸው ይችላሉ ይላሉ አቶ መቆያ።

በፓርኩ ላይ የተጋረጠው አደጋ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጂራ ይናገራሉ።

ፓርኩን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት የማሳደጉ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ከሚገባው በላይ መጓተቱን የሚያምኑት አቶ ኩመራ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ተስፋ ሰጭ ደረጃ ላይ ነው ያለው ይላሉ።

ፓርኩ በሁለት ክልሎች ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኝ መዋቅርን ማሳተፍ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ እስካሁን ሂደቱ በሚፈለገው መጠን ባይፈጥንም ነገር ግን በሚንስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አስፈላጊው መረጃ ተሰባስቦ በዝግጅት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። በርካታ አደረጃጀቶችና የለውጥ ሥራዎች ስለሚሰሩ ከእነሱ ጋር ማጣጣሙ ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል።

ፓርኩ ለረጅም ጊዜ 'ጥብቅ ክልል' ተብሎ ነበር የሚታወቀው። በዚህ ምክንያትም ፓርኩ ተገቢው ጥበቃና አስተዳደር ሳያገኝ ቆይቷል። ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ግን ፓርኩ ያለውን ጥቅም በመገንዘብ በያንጉድራሳ ፓርክ ጥላ ስር ሆኖ ሲተዳደር ነበር።

ፓርኩ ለቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሃብት ያለው ሲሆን፤ ሳላ የሚባለው እንስሳ በአፍሪካ ደረጃ በብዛት የሚገኝበትም ነው። ይህ እንስሳ በብዛት የሚገኘው ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ከኢትዮጵያ ደግሞ በብዛት የሚገኘው ሃላይ ደጌ አሰቦት መሆኑን አቶ ኩመራ ተናግረዋል።

ሌላኛው ለጥፋት የተጋለጠው የሜዳ አህያ ዝርያም በዚሁ ፓርክ ውስጥ ይገኛል። የዚህ ዝርያ ትልቁ መንጋ የሚገኘው እዚሁ ፓርክ ውስጥ መሆኑን አቶ ኩመራ ዋቅጂራ ይገልጻሉ። በመሆኑም እነዚህ እንስሳትን በዘላቂነት በፓርኩ ውስጥ ህልውናቸውን ለማስጠበቅና ፓርኩ የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ጥረቶች ቀደም ብለው ቢጀመሩም እስካሁን መቋጫ እንዳላገኙ ይገልጻሉ።

ከ40 ዓመታት በላይ በጥብቅ ደንነት ብቻ በመቆየቱ በ2002 ዓ.ም ጥብቅ ደኑ ያሉት ጸጋዎች ተለይተው በያንጉድራሳ ፓርክ ጥላ ሥር ሆኖ ጥበቃ እንዲደረግለት መደረጉም ተነግሯል።

ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ የባለሙያ ቡድን ተዋቅሮ በ2006 ዓ.ም ወደ እጩ ብሔራዊ ፓርክነት እንዲያድግ ሥራዎች ተሰርተው መነሻ ሐሳቡ ለሚመለከተው አካል ጥያቄው ቀርቧል። በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ምክክር ተደርጎ ስምምነት ላይም ተደርሶ እንደነበር አቶ ኩመራ ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ቀሪው ሂደት የነበረው የብሔራዊ ፓርክነት እውቅና እንዲያገኝ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚንስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ማድረግ ነበር። ነገር ግን እዚህ ደረጃ ከተደረሰ በኋላ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በኩል የተወሰኑ ቢሮዎች ጉዳዩን እንደማያውቁትና አካሄዱም ትክክል አለመሆኑን መግለጽ በመጀመራቸው ሂደቱን ማስቀጠል አለመቻሉን አቶ ኩመራ ይገልጻሉ።

ፓርኩ አሰቦት ገዳምንም የሚያካትት ስለነበረ 'ሃላይደጌ አሰቦት' የሚል ስም በመያዙ ከስያሜ ጋር የተያያዘ ቅሬታ አጋጥሞ ነበር። በዚህ መካከል ደግሞ አመራሮች በፍጥነት ስለሚቀያየሩ መጀመሪያ ጉዳዩን ያንቀሳቀሱት አካላት በመቀየራቸው ጉዳዩ እንደገና ተመልሶ ወደ ኋላ ተጎተተ ይላሉ አቶ ኩመራ።

በዚህ ምክንያት ፓርኩን ወደ ብሔራዊ ፓርክነት የማሳደጉ ሂደት ተስተጓጎለ። የሚንስትሮች ምክር ቤት ደግሞ ሁሉም በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የተስማሙበትን ሰነድ ካረጋገጠ በኋላ ነው እውቅና የሚሰጠው።

በሁለቱ ክልሎች በኩል በተነሱ ቅሬታዎች ምክንያትም እነዚህ ሂደቶች እንዲሟሉ ወደ ኋላ ተመልሶ የሁለቱንም ክልል የየደረጃው አመራሮችና ነዋሪዎችን ማወያየት ማስፈለጉም ተነግሯል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኩመራ እንደሚሉትም እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ በአሁኑ ወቅት አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፣ ዝርዝር እቅድ ተዘጋጅቶለት፣ ለእውቅና ሚያበቁት ሂደቶችና የክልሎች ይሁንታ ተጠናቆ የእውቅና ጥያቄው እስከመቼ መቅረብ እንዳለበት በእቅድ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መሰረትም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው ለሚንስትሮች ምክር ቤት የእውቅና ጥያቄ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።