ካናዳ፡ ዓሥር ዓመታት የፈጀው የኤርትራውያኑ የወርቅ ኩባንያ ክስ በስምምነት ተቋጨ

ቢሻ የማዕድን ፍለጋ

የፎቶው ባለመብት, NEVSUN RESOURCES WEBSITE

በኤርትራ የወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የካናዳ ኩባንያ ላይ የተመሰረተው ክስ በስምምነት ተቋጨ።

በኤርትራ ወርቅ በመፈለግ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የካናዳው ኩባንያ ኔቭሰን ሪሶርስስ ላይ ከዓሥር ዓመታት በፊት ተመስርቶ የነበረው ክስ ነው በስምምነት መቋጨቱ ተሰምቷል።

ካናዳዊው ኩባንያ ኔቭሰን ሪሶርስስ፤ በኤርትራ በወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ በተሰማራባቸው አምስት ዓመታት ባደረሰው የጉልበት ብዝበዛ እና ኢሰብዓዊ አያያዝ ክሱ መመስረቱ ተገልጿል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ክሱን ሕግ ፊት ያቀረቡት ሦስት ኤርትራውያኖች መሆናቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከዚህ ቀደም ዘግበውት ነበር።

ጉዳዩን ለዓሥር ዓመታት ስትከታተል የነበረችው ኤርትራዊቷ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቿ ወ/ሮ ኤልሳ ጭሩም ለቢበሲ እንደገለፀችው፤ በወቅቱ ኩባንያው ያሰራቸው የነበሩ የብሔራዊ አገልግሎት ላይ የነበሩ ወጣቶች ምንም አይነት ክፍያ አልተከፈላቸውም።

ኔቭሰን ሪሶርስስ ኩባንያ ለብሔራዊ አገልግሎት አባላቱ ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይከፈላቸው እያወቀ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመመሳጠር "ጉልበታቸው መበዝበዙን" በመጥቀስ በካናዳ ክስ ተመስርቶበታል።

ክሱን የመሰረቱት አካላት እኤአ ከ2008 እስከ 2012 ኔቭሰን ሪሶርስስ በኤርትራ ቢሻ በሚባል አካባቢ የወርቅ፣ ዚንክና መዳብ ማዕድኖች ፍለጋ ሲያካሂድ፤ ከ1000 በላይ በሚሆኑ የብሔራዊ አግልግሎት አባላት ላይ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በማበር የጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል ሲሉ መክሰሳቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

በካናዳ ፍርድ ቤት ሲታይ የቆየው ይህ ክስ በሽምግልና መጠናቀቁን የገለፁት ወ/ሮ ኤልሳ፤ በስምምነቱም ደስተኞች መሆናቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ ክፍል ተናግረዋል።

ኩባንያው ጉዳዩ በኤርትራ ላይ አልያም በሌሎች የአፍሪካ አገራት እንዲታይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር ተብሏል።

ሆኖም የካናዳ ፍርድ ቤት ጉዳዩ የዓለም አቀፍ ሕግ መጣሱን የሚመለከት በመሆኑ በካናዳ መታየቱ እንዲቀጥል ወስኖ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል።

የብሔራዊ አገልግሎት አባላቱ እአአ ከ2008 እስከ 2012 በማዕድን ቁፋሮ በሚሠሩበት ጊዜ የሰብዓዊ መብታቸው እንደተጣሰና፣ አያያዛቸውም መጥፎ እንደነበር በመጥቀስ ተከራክረዋል።

ኔቭሰን ሪሶርስስ በበኩሉ ክሱን በመቃወም ለሠራተኞቹ ኃላፊነት እንዳልነበረው ሲከራከር ቆይቷል።

ኩባንያው እና ክሱን የመሰረቱት አካላት የደረሱበት ዝርዝር ስምምነት ምን እንደሆነ አልተጠቀሰም።