ትግራይ፡ ዐቃቢያነ ሕግ ጥያቄያቸው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትግራይ ዐቃቢያነ ሕግ በሌላ ክልሎች እና በፌደራል ከሚገኙ ዳኞች እና ዐቃቢያነ ህጎች ጋር ተመሳሳይ ሥራ እየሰሩ በደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንደተነጠሉ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት፣ ተቋማዊ ነፃነታቸውን በመከልከል ለሥራቸው መሰናክል እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ትግርኛ ገልፀዋል።
ይህንን የመብት እና የፍትህ ጥያቄያቸው ለወራት ለክልሉ ፍትህ ቢሮ ቢያቀርቡም ተገቢ ምላሽ አላገኘንም ይላሉ።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ዐቃቢያነ ሕጎቹ ያነሱት የደሞዝ ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑን ይናገራሉ።
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረው ዐቃቢ ሕግ ዳንኤል በሌሎች ክልሎችና በፌደራል ከሚገኙ ዐቃቢያነ ሕጎችና ዳኞች ጋር ትልቅ የደሞዝ ልዩነት መፈጠሩ አሁን በክልሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ዘንድ ለተፈጠረው ቅሬታ ትልቁ መነሻ እንደሆነ ይገልፃል።
በሌሎች ክልሎችና በፌደራል ለሚገኙ ዐቃቢያነ ሕጎች "ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ድረስ ደሞዝ እየተከፈላቸው እኛ ግን 8700 ብር ብቻ ነው የምናገኘው። ይህ ልዩነት ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የተፈጠረ ነው" ይላል።
በትግራይ ደቡባዊ ምሥራቅ ዞን ዐቃቢ ሕግ የሆነችው ትዝታ ጌታቸውም ይህ ልዩነት እንዲፈታ ቢማፀኑም ሰሚ እንዳጡ ትናገራለች።
"ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የሚል ቢደነገግም እኛ ግን ዝቅተኛ ክፍያ ነው የምናገኘው። ለወራት የፍትህ ቢሮ ኃላፊን ጠይቀናል፤ እስከኣሁን ጥያቄያችን አልተመለሰም" ትላለች።
"ኑራችን ከእጅ ወደ አፍ ሁኗል"
ይህ ልዩነት በክልሎችና በፌደራል ካሉት ዳኞች እንዲሁም ዐቃቢያነ ሕግ አንጻር የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን፤ በክልሉ ካሉ ዳኞችም ጋር ተፈጥሯል።
ዐቃቤ ሕግ ዳንኤል "ለትግራይ ክልል ዳኞች ከ80 እስከ 100 ፐርሰንት የደሞዝ ጭማሪ ተደርጓል። ለዐቃቢያነ ሕጎች ግን በፌደራልና በትግራይ ክልል መካከል ለተፈጠረው ልዩነት ፖለቲካዊ ሁኔታ 'በመመከት ላይ ስለሆንን' አንጨምርላችሁም" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራል።
"በክልሉ ላሉ ዳኞች ደሞዝ ባይጨመርላቸው 'በመመከት ላይ ነን' ያሉት ምክንያታቸው አሳማኝ ይሆን ነበር" በማለት ለድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሳይቀር ጭማሪ መደረጉን በመጥቀስ ለአንዱ ተጨምሮ ሌላውን ማግለል በፍፁም ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም ይላል።
ሌላኛው ዐቃቤ ሕግ ሙዑዝ ፀጋይ ደግሞ የእኩልነት ጥያቄ ቢያነሱም የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ "የዳኞችን ደሞዝ እንቀንሳለን እንጂ የናንተ ደሞዝ አይጨምርም' ከሚል ውጪ ሌላ መልስ እንዳልሰጣቸው በመግለፅ፤ ዐቃቢያነ ሕጎች ተስፋ በመቁረጥ ሥራቸውን እያቋረጡ እንደሆነ ይናገራል።
"ዐቃቤ ሕጉ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ህዝብን ለማገልገል ሲል እስከአሁን ሰርቷል። አሁን ግን እንደዚህ አይነት አመለካከት በተፈጠረበት ሁኔታ በተገቢው መንገድ ማገልገል አይችልም" ይላል ሙዑዝ።
ጨምሮም ኑሮ እየከበዳቸው በመሆኑ በርካቶች ዐቃቤ ሕግነትን በመተው ወደ ጥብቅና ሞያ እየሄዱ ነው ይላል። "አይደለም ወደ ጥብቅና ወጥተው ማመልከቻ ፅፈውም ከምናገኘው ደሞዝ በላይ ነው የሚከፈላቸው" በማለት ዐቃቢያነ ሕጎቹ ተስፋቸው መሟጠጡን ገልጿል።

"ሰጥቶ የሚለምን መንግሥት ነው ያለን"
የክልሉ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ የክልሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ያነሱት ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑ በመግለፅ ጥያቄያቸውን ለመመለስ የዳኞችን ደሞዝ መቀነስ አልያም 'በመመከት ላይ ነን ያለነው' የተባለውን ግን "ውሸት" እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በመመከት ላይ እንዳለን የሚካድ አይደለም። ዐቃቢያነ ሕጎቹ የሚያነሱት ደሞዝ አይመለከታቸውም ማለት ግን አይደለም። በደሞዝና ጥቅማ ጥቅሞች እንዲጨነቁም አንፈልግም። ጭማሪ ሲነሳ ይህን ያህል ነው መሆን ያለበት እየተባለ ነው፤ እና ምን እንበል?
"የመንግሥትን አቅም የምናውቅ እኛ እኮ ነን። አፍሰን መስጠት ብንችል በሰጠናቸው፤ ግን ሰጥቶ የሚለምን መንግሥት ነው ያለን" ይላሉ በአሁኑ ጊዜ የክልሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ከኪሳቸው ለክልሉ መንግሥት ገንዘብ እንዲያዋጡ መጠየቃቸው በመጠቆም።
"መፈናፈኛ የሌለው" የዐቃቢያነ ሕጎች ተቋማዊ ነፃነት
የክልሉ ዐቃቢያነ ሕጎቹ ካነሱት የደሞዝና የጥቅማ ጥቅም እኩልነት ጥያቄ በተጨማሪ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና ፖለቲካዊ ሹመት ተቋማዊ ነፃነት እንዳይኖር በማድረግ ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነ ይናገራሉ።
ዐቃቤ ሕግ ከጅምሩ ራሱን የቻለ ነፃ ተቋም ሆኖ መቋቋም ሲገባው፤ ተጠሪነቱ ለክልሉ ካቢኔ እንዲሆን የተደረገው ፖለቲካዊ ጫና እንዲያድርበት ስለተፈለገ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያዎቹ፤ የዐቃቤ ሕግ ተጠሪነት ከካቢኔው ውጪ እንዲሆንም ይጠይቃሉ።
ዐቃቤ ሕግ ዳንኤል "ተቋማዊ ነፃነት የሚባል ነገር የለም። ማንም ካቢኔ ወይም ከንቲባ መጥቶ ነው የሚያፈጥብን፤ ይህን አድርግ ይህን አታድርግ ይላሉ። በአጭሩ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት አለ። ስለዚህ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በነፃነት ለመወሰን በጣም አስቸጋሪ ነው" በማለት ከደሞዝ ጥያቄ በተጨማሪ የተቋማዊ ነፃነት ጥያቄም እንዳለ አመልክቷል።
"የበላይ ኃላፊ ሊከስ ከፈለገ የሚከስበት ብዙ ክፍተቶች አሉ። የምትወስናቸው ውሳኔዎች ትክክል አይደለም ብሎ ሊከስ አልያም ሊያባርር ይችላል። ነፃነት የሚባል ነገር የለም፤ ምንም አይነት ዋስትና የለም በጣም ከባድ ነው" ይላል።
"የህወሓት አባል እንድንሆን እንገደዳለን፤ ደሞዛችንም ይቆረጣል"
የክልሉ ዐቃቤ ሕግ መተዳደርያ ደንብ ላይ አንድ ዐቃቤ ሕግ የማንኛውም ፖለቲካዊ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችል ቢደነገግም፤ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የገዢው ፓርቲ አመራር በመሆናቸው ዐቃቢያነ ሕጎቹ የህወሓት አባል እንዲሆኑ ጫና እንደሚደርግባቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በክልሉ ደቡባዊ ምሥራቅ ዞን ዐቃቤ ሕገ የሆነው ግርማይ ካሕሳይ የገዢው ፓርቲ አባል ሳይሆኑ ከወርሃዊ ደሞዛቸው ከተቆረጠባቸው መካከል አንዱ ነው።
"ደሞዛችን በባንክ ገቢ ሲደረግ እየተቆረጠ መሆኑን ካወቅን በኋላ ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ የፓርቲው አባልነት ክፍያ ነው ተባልን። እንዲመለስልን ብዙ ጊዜ ብንጠይቅም ሳይመለስልን ከፓርቲው አባላት ጋር ደሞዛችን ሲቆርጥ ሦስት ወር ሆኖናል" በማለት አባል እንዲሆኑ እንደሚጠየቁ ተናግሯል።
የፍትህ ቢሮው ኃላፊ አቶ አማኑኤል ግን ይህ ቅሬታ ከእውነት የራቀ መሆኑን በመጥቀስ "አንድን የሕግ ባለሙያ የፓርቲ አባል መሆን መብት ነው ግዴታ የሚለውን ማንም ሰው ሊነግረው አይችልም። ራሱ ወዶ ነው የአንድ ድርጅት አባል የሚኮነው እንጂ ዝም ተብሎ ደሞዝ አይቆረጥም። ደሞዝ በፍቃደኝነት አልያም በህግ ነው የሚቆረጠው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የዐቃቢያነ ሕግ ድምፅ "ያከሰመው" አዋጅ
ለወራት ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ሲማፀኑ እንደቆዩ የሚናገሩት የትግራይ ዐቃቢያነ ሕጎች መስከረም 25/2013 ዓ.ም የሥራ ማቆም አድማ ለማካሄድ እንዳሰቡ ተነግረው ነበር። ነገር ግን በተደረገባቸው ጫና ያሰቡትን የሥራ ማቆም አድማ ሳያካሂዱ እንደቀሩ ይገለፃሉ።
ዐቃቢያነ ሕጎች በሚተዳደሩበት ደንብ ቁጥር 104/2012 አንቀፅ 68(21) እንዲሁም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ 421፤ ማንኛውም ሠራተኛ አድማ ማካሄድ እንደማይችል እንደሚደነግግና አድማ ያደረገ ወይም ሌሎች እንዲያድሙ ያደረገ ማንኛውም ሠራተኛ በወንጀል ተጠያቂ ሆኖ አንድ ሺህ ብር እንደሚቀጣ ተፅፎ እንደሚገኝ የሚገልፁም አሉ።
ከአሁን በፊት አዲስ ደንብ ሲፀድቅ በክልል ደረጃ ዐቃቢያነ ሕጎች እንደሚወያዩበት የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አሁን ግን ለወራት ሲያነሱት የነበሩትን የመብት ጥያቄያቸውንና ድምፃቸውን "የሚያከስምና የሚያፍን" አዲስ አዋጅ እነዙ ሳያውቁ እንዲፀድቅ መደረጉ እንዳስቆጣቸው ዐቃቢ ሕግ ሙዑዝ ፀጋይ ይናገራል።
"ይህ አዲስ አዋጅ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ያፀደቁት ነው፤ እኛ ጥያቄ ካነሳን በኋላ ደግሞ አሻሻሉት። ይህም በ2011 በወጣው ደንብ ላይ የተገለፁ ጥቅማ ጥቅሞችን ያስወገደና 'በማኅበራዊ ሚድያ ለዐቃቤ ሕግ ሞያ የሚቃረን ስዕልም ይሁን ፅሁፍ የለጠፈ በሥነ ምግባር ማጉደል ይጠየቃል' የሚል ያካተተ ነው" ይላል ዐቃቤ ሕግ ሙዑዝ።
በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና አስተዳደር ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ካሳ አዲሱን ደንብ ነባራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያላስገባና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የተደረገ "የአፈና እርምጃ" በማለት ይገልፀዋል።
"ዐቃቢያነ ሕግና ዳኞች ከሲቪል ሰርቪስ ሴክተሮች በተለየ የየራሳቸው የተለየ ባህሪ ስላላቸው በደንብ የሚወጣ የራሳቸው የሥነ ምግባር ደንብ አላቸው። ይሁን እንጂ ማኅበራዊ ሚድያ በመጠቀም በወሳኝ አካል ላይ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ ስላዩ አፋቸውን ለማስያዝ ተብሎ የወጣ እንጂ ከዐቃቤ ሕግ ክብርና ሙያ ጋር የሚቃረን ነገር ከጻፉ፤ በወንጀል ሕግም፣ በራሳው የሥነ ምግባር ደንብም ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል" ይላል።
ይህ የሥርዓቱ ዋና ችግር እንደሆነ የሚናገረው ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ሕግ አጠቃላይ አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ነው የሚወጣው፤ አሁን እየወጡ ያሉት ሕጎች ግን አንድ ቡድንን 'ዒላማ' ያደረገ ይመስላል የሚል ትዝብት አለው።

የፎቶው ባለመብት, YEMANE KASSA
ፖለቲካዊ ሹመት እስከ መቼ?
በትግራይ ክልል በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው የቀረበ ግንኙነት፣ የትግራይ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም የፍትህ ቢሮ በፖለቲካዊ ሹመኛና በህወሓት ከፍተኛ አመራር የሚመራ መሆኑ በሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
ሕጉ ዐቃቢያነ ሕግ የፓርቲ አባል እንዳይሆኑ ቢከለክልም "ኃላፊው የፓርቲ አባል ከሆነ የታችኛው መዋቅር አባል ባይሆንም የሚያመጣው ለውጥ የለም" ይላል ዐቃቤ ሕግ ሙዑዝ።
በተጨባጭ ያለው አካሄድ ይላል ዐቃቤ ሕግ ግርማይ፤ እንደ ተማርነውና እንደ ተረዳነው እንዲሁም ኅብረተሰቡን ለማገልገል ቃል እንደገባነው ሳይሆን ዐቃቤ ሕግ የአንድ ወገን አገልጋይ ነው የሚል አስተሳሰብ የሚፈጥር ነው።
በተጨማሪም በመንግሥት ጉዳዮች ላይ በተለይም በመንግሥት የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ሲሆኑ ሊከሰሱ የማይገባቸው 'ፍርድ-ቤት የፈለገውን ይበል' እየተባሉ እንዲከሱ እንደሚገደዱ ይናገራል።
እንደ ሦስተኛ የመንግሥት አካል ፍርድ ቤት ብቻ ነው ሕገ-መንግሥታዊ የዳኝነት ነፃነት ያለው የሚሉት የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ግን "ፍትህ አንድ የመንግሥት አካል በመሆኑ ፈፃሚው አካል መንግሥት በፈለገው ጊዜ ክስ የማቋረጥ ሕጋዊ ስልጣን አለው" ይላሉ።
አክለውም ወንጀል ተፈፅሞ ከሆነም ክስ ይመስረትልኝ በማለት ወደ ሚመለከተው የፖሊስ አካል እንደሚመራ ይናገራል፤ የዐቃቤ ሕግ ስልጣን "መክሰስ ብቻ እንደሆነ" ይናገራሉ።
የፍትህ አካላት ከፖለቲካዊና መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን አለባቸው የሚባለው ትክክል ነው የሚሉት ኃላፊው "ፖለቲካዊ ሹመት የፍትህ ሥርዓቱን ያዛባዋል" የሚለውን ግን አይቀበሉትም።
"የፍትህ ቢሮን የሚመሩና የሚሰሩ ሰዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው። እኔም ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ነው። ለፍርድ ቤት ፕሬዝደንትና ምክትልነት ለሹመት መርጦ የሚያመጣው ፖለቲካዊ ስልጣን የተሰጠው ፓርቲ ነው። በሦስቱ የመንግሥት አካል ውስጥም የፖለቲካ ሹመኛ ያልሆነ ሰው አይገኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ አንጻር ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞትዮስ ሹመት እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።
በማከልም በክልላዊ ምርጫ ላይ "ለህወሓት ምረጡ" ብሎ ቅስቀሳ ሲያካሂድ የነበረው የህወሓት አመራር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆኖ፤ የዐቃቢያነ ሕጉን ጥያቄዎች ምላሽ ሲነፍግ "ፖለቲካዊ ስልጣን የጨበጠውን ኃይል ፍላጎት ከማሳካት ወደ ኋላ የሚል አይደለም" በማለት ፖለቲካዊ ሹመት ከተቋማዊ ነፃነት ጋር የሚቃረን መሆኑ ያብራራል።
በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው ጫና
በክልሉ በፍትህና በመልካም አስተዳደር ተበድለናል የሚሉ ቅሬታዎች መስማት አዲስ አይደለም፤ ይህ ገዢው ፓርቲ ህወሓትም ሳይቀር ያመነበት ነው።
የዐቃቢያነ ሕጉ ቅሬታም አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ዐቃቤ ሕግ ዳንኤል እንደሚለው ካለባቸው ተደራራቢ ጫና ጋር ሕዝቡን የማገልግል ፍላጎት ቢኖራቸውም በአንድ መንግሥት ስር ሆነው እኩል አለመታየታቸውና ምላሽ ማጣታቸው የሥራ ሞራሉ እንዲቀንስ በማድረግ በተገቢው መንገድ ለማገልገል እንደሚቸገር ይገልጻል።
የትግራይ ዐቃቤ ሕግ ፍትህ እንዲሰፍን ቢታገልም ለራሱ ግን በፍርሃት ወጥመድ ውስጥ የሚኖር እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፤ "ለሕዝቡ ፍትህ ለመስጠት እየታገልን ለራሳችን ግን በቢሮክራሲው እየተጎዳን ነው" ይላል ዳንኤል።
"አብዛኛው በትግራይ ያለው ዐቃቤ ሕግ ፍትህ ለመስጠት ቢታገልም ለራሱ ግን ፍትህ የማይጠይቅ፣ ተሸማቆ ወይም ፈርቶ የሚኖር ነው" በማለት ሀሳቡን ይቋጫል።
የመቀለ ዩኒቨርሲቲው የሕግ ምሁር ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ካሳ በበኩሉ "የዐቃቢያነ ሕጎቹን ጥያቄ ማፈንም ሆነ ለማሸማቀቅ መሞከር የፍትህ ችግር ላላት ትግራይ ሌላ ተጨማሪ ችግር መጨመር ነው" በማለት መንግሥት እንዲያነጋግራቸውና ጉዳዩ ቶሎ እንዲፈታ ይጠይቃል።
ከዚህ ውጪ ግን ሁኔታው ጊዜ የሚወስድ ከሆነ በትግራይ ያለው የዐቃቢያን ሕግ እጥረት እየባሰ እንዲሄድ፣ ፍትህ እንዲጓተትና እንዲበላሽ የሚያደርግ ነው በማለት አስተያየቱ ይሰጣል።
















