ትግራይ፡ ለ10 ማረሚያ ቤቶች 10 ሺህ መጻሕፍት

ወጣቶች

በመቀለ ከተማ እየተካሄደ ባለው "መጽሐፎች የማሰባሰብ ዘመቻ" በትግራይ ክልል ለሚገኙ 10 ማረሚያ ቤቶች የሚውሉ 10 ሺህ መጽሐፎች ለመሰብሰብ መታቀዱ አስተባባሪዎቹ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሃሳቡን ያመነጨው ወጣት ሳሙኤል ደስታ እንደሚለው ከሆነ ዘመቻው ከመስከረም 20፣ 2013 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ይቀጥላል።

መጽሐፎቹን ከተለያዩ ለጋሾች ለማግኘት ማቀዳቸውን የገለጸው ሳሙዔል፣ ሃሳባቸው በበርካታ ሰዎች ተቀባይነት እንዳገኘ ተናግሯል።

ዘመቻው መስከረም 20 ላይ ከተጀመረ ጀምሮ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 700 ያህል መጽሐፎች መሰብሰብ ችለዋል።

"ብዙም ትኩረት የማይሰጠዉ ጉዳይ ስለሆነ 'ለመሆኑ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ቤተ መጻህፍት አለን እንዴ?' ያሉን ሰዎች አሉ። ሰምተውና አስበውት ስለማያውቁ በጣም ነው ደስተኛ የሆኑት። ብዙ ሰዎች መጽሐፎች ሊለግሱልን እና ለስራችን አጋዥ የሆኑ መረጃዎች መስጠት ጀምረዋል" ይላል።

ሳሙኤል ሐሳቡን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ቆርጦ በሚነሳበት ጊዜ፣ በተለይም ሰዎች መጽሐፎች እንዲለግሱ በማነሳሳትና የሚለገሱትን በማሰባሰብ ሊረዱት የሚችሉ ወጣት ሴቶችን ለማነጋገር እንደወሰነ ይገልጻል። ለዚህም በተለያዩ የቁንጅናና ሞዴሊንግ መድረኮች ተሳትፎ ያላቸውን ሴቶች እንደመረጠ ያስረዳል።

"የቁንጅና ወይም ሞዴሊንግ ውድድር አላማው፣ አርኣያ በመሆን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ለውጥ ማምጣት ነው። ሆኖም ግን በእነዚህ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ሴቶች ከውድድሩ በኋላ ይህንን ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል አያገኙም። ስለዚህ ይህን ከግምት በማስገባት ነው እንዲረዱኝ ያነጋገርኳቸው" ብሏል።

በዚህም መሰረት በተለያዩ የቁንጅናና ሞዴሊንግ ውድድሮች ላይ የተሳተፉ አራት ሴቶች በመምረጥ ወደስራው ገባ። አዱኛ ዳኘው፣ ቢዚ መብራህቱ፣ ማክዳ ፍሰሃና ሮዳስ ሚዛንን የሚባሉት እነዚህ ወጣት ሴቶች "ኮኾባት ትግራይ" [የትግራይ ኮኮቦች] በሚል ስያሜ መጽሐፍ የማሰባሰብ ዘመቻውን እያስተባበሩ ይገኛሉ።

"ሳሙኤል ሐሳቡን ሲያቀርብልን በጣም ደስተኞች ነበርን። ምክንያቱም ሞዴሎች ወይም የቁንጅና ውድድር አሸናፊዎች ከሙዚቃ ክሊፖችና ፊልሞች ውጪ በዚህ ዓይነት ተሳትፎ ላይ ብዙም አይታዩም" ትላለች ከወጣቶቹ መካከል አንዷ የሆነችው አዱኛ ዳኘው።

መጻሕፍቶቹ፡ ታራሚዎች በእስር ቆይታቸው እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ከማድረግ በተጨማሪ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንዲያልፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ታምናለች።

ስለሆነም እሷና ጓደኞቿ በዚህ ዘመቻ ላይ መሳተፍ መቻላቸው እንደ መልካም ዕድል ትቆጥረዋለች።

መነሻ ሐሳቡ ምን ነበረ?

ወጣት ሳሙኤል በፕሮሞሽን እና ኪነጥበብ ዘርፍ የተሰማራ ባለሙያ ነው። ለታራሚዎች የሚሆኑ መጽሐፎች ለማሰባሰብ ሲነሳሳ የታሰረ የቤተሰቡ አባል፣ ጓደኛው ወይም የቅርብ ሰው ኖሮት እንዳልሆነ ይናገራል።

ከ ዘጠኝ ዓመታት በፊት የ ስምንተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ያሉትን ቤተ መጻህፍቶች የመጎብኝት ዕድል አጋጥሞት ነበር። ታዲያ ለዛሬው ሐሳቡ መነሻ የሆነው ይኼው አጋጣሚ እንደሆነ ያስረዳል።

"ያኔ ተማሪ ሆኜ የተማሪዎች ፓርላማ አባል ስለነበርኩ፣ በትግራይ ወደሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በመሄድ በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ያሉትን ቤተንባቦች ጎብኝተን ነበር። የያኔው ሁኔታ በውስጤ ስለቆየ ዛሬ ጊዜው ሲደርስ በተግባር ለመንቀሳቀስ ውሳኔ ላይ ደረስኩ" ይላል።

ታራሚዎች የፈለጉትን መጽሐፍ በቀላሉ የሚያገኙበት ዕድል አለመኖሩን በመታዘቡ ከዓመታት በኋላ ዛሬ የድርሻውን ለመወጣት እንደወሰነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በትግራይ 10 ማረሚያ ቤቶች አሉ። በቂ መጻሕፍት ባይኖራቸውም ላይብራሪዎች [ቤተ መጻህፍት] ግን አሏቸው። ታራሚዎቹ ነገ ወደ ኅብረተሰቡ ስለሚቀላቀሉ የእነርሱ ሙሉ መለወጥ ደሞ በቤተ መጻሕፍት ውስጥም ልናገኘው እንችላለን። ስለዚህ እውቀታቸውን እና ስነልቦናቸውን ገንብተው ቢወጡ በሚል ነው ወደ ስራው የገባነው" ሲል ይገልጻል።

ከማራሚያ ቤቶቹ መካከል አንዱ ለሆነው መቀለ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ስለጀመሩት እንቅስቃሴ በሚመለከት ባነጋገሩበት ሰዓት 'ቤተ መጻሕፍት ቢኖረንም ታራሚዎች ግን የሚፈልጓቸውን ለማግኘት ይቸገራሉ። ስለዚ የጀመራችሁት ዘመቻ መልካም ነውና ለእኛም እንድትረዱን እንፈልጋለን' የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ሳሙኤል ያስታውሳል።

የለጋሾች ተሳትፎ

ከ 'መጻሕፍት ለትግራይ ማረሚያ ቤቶች ዘመቻ' አስተባባሪዎች አንድ የሆነችው ወጣት አዱኛ ከህዝቡ የተሰጠ ምላሽና ተሳትፎ እጅግ የሚያኮራ እንደሆነ ትገልጻለች።

"ሰዎች ሐሳቡን ተቀብለውታል። በማህበራዊ ገጾችም እየተነጋገሩበት ነው። አንድም ይሁን ከዚያ በላይ መጽሐፍ ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች እንድንቀበላቸው ደውለው ያሳውቁናል። እኛም ወዳሉበት ቦታ በመሄድ እንቀበላቸዋለን" በማለትም ታስረዳለች።

ከመቀለ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ስልኮች እየተደወሉ "መጽሐፍ ተቀበሉን' የሚል ጥሪ ስለሚደርሳቸው ለጊዜው በመቀለ ብቻ ለሚቀርቡ ልገሳዎች አራቱም በመመካከርና በመተጋገዝ ይቀበላሉ።

ከሌሎች አካባቢዎች የሚቀርቡ ስጦታዎች እንዴት መቀበል እንደሚችሉም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ናቸው።

መጽሐፎቹን ለመቀበል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመጓጓዣ ወጪ ስለሚኖር ከኪሳቸው ይሸፍኑታል። ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አንዳንድ ሰዎች ደሞ ለዚህ ዓላማ በማሰብ ለትራንስፖርት የሚሆን የተወሰነ ጥሬ ገንዘብ እንደሚሰጧቸው አዱኛ ትናገራለች።

ሳሙኤል በበኩሉ "እኛ ስንጀምረው ለ10 ማረሚያ ቤቶች የሚከፋፈሉ 10 ሺ መጻሕፍት ለማሰባሰብ በማቀድ ነው። አሁን ባለው የሰዎች ተፋትፎ ግን ከዚያም በላይ ማሰባሰብ እንደምንችል አሳይቶናል" ይላል።

ስለሆነም ለአንድ ማረሚያ ቤት ከ 1 ሺ መጽሐፎች በላይ እንደሚደርስ ያምናል።

የመጻሕፍቶቹ ይዘቶች?

ሳሙኤልና አዱኛ እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች ምን ዓይነት መጽሐፍ መለገስ እንደሚችሉ የወጣ መለኪያና የተነገረ መመሪያ የለም።

ይህም ሆኖ ግን ሰዎች "ለታራሚዎች" የሚለውን ሃሳብ ከግምት በማስገባት እስካሁን የሚያስረክቧቸው መጻሕፍት በማረሚያ ቤተቹ ውስጥ ለሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ሊቀመጡ የሚችሉ ናቸው።

"በርግጥ ወደ ዘመቻው ከመግባታችን በፊት በክልሉ ጸጥታ ቢሮ ጉዳዩ ከሚመለከትው አካል ጋር በመነጋገር ዳሰሳ ለማድረግ ሞክረናል" የሚለው ሳሙኤል ለታራሚዎቹ ምን ዓይነት መጻሕፍት እንደሚያስፈልጉ መረዳታቸውን ይገልጻል።

"በንግድ፣ ባህላዊ አልባሳት ዝግጅት፣ የብረታ ብረትና እንጨት ስራዎች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ታራሚ ወጣቶች ስላሉ ለዚህ ሊረዳቸው የሚችል የኢንዳስትሪና ፈጠራ መጽሐፍ በብዛት ይፈለጋል። በታራሚዎቹ ስነልቦናና እውቀት ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው የሚችሉ ሌሎች መጻሕፍቶችም እየተቀበልን ነው" በማለት ያስረዳል።

እስካሁን 'ይህ አስፈላጊ አይደለም' በሚል የመለሱት መጽሐፍ እንደሌለ በማስታወስም የስነጽሑፍ ውጤቶች የሆኑ መጻሕፍቶችም በብዛት እየተቀበሉ መሆናቸውን ገልጿል።

አዱኛ በበኩሏ "ብዙ ዓይነት መጽሐፍት ነው እየተቀበልን ያለነው። ሁሉም ጥሩ የሆነ ይዘት አላቸው" በማለት ከታራሚዎች መካከል ምሁራንም ስለሚገኙ 'ኣካዳሚያዊ' እንዲሁም ሌሎች እውቀቶችን ሊያዳብሩ የሚችሉ በእንግሊዝኛ ጭምር የተጻፉ እንደሚቀበሉ አስታውሳለች።