ኢትዮጵያ፡ ወገኖቹን ለመርዳት ጠመኔ የጨበጠው ሐኪም

ዶ/ር መሐመድ አሊ

የፎቶው ባለመብት, Dr. Mohamed Ali

ተማሪ አህመድ አብዲ ዶህ በሶማሌ ክልል የሚገኘው ዋርዴር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሆስፒታል ሲያገለግሉ የሚያውቃቸው ዶ/ር መሐመድ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ነው።

የሕክምና ባለሙያው ወደ ትምህርት ቤታቸው መጥተው ለእርሱና ለክፍል ጓደኞቹ የባዮሎጂና የኬሚስትሪ ትምህርቶች ላይ እገዛ ሲያደርጉላቸው ሲያይ ተደንቋል።

በዋርዴር አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መሐመድ አሊና ዶ/ር አህመድ ናስር አብዱርህማን ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ወደ ዋርዴር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጠመኔ ይዘው ይሄዳሉ።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ስለተላላፊ በሽታዎች፣ ስለንጽህና አጠባበቅ አልያም ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ለማስተማር ሳይሆን የሚገኙት፤ መደበኛ የትምህርት ሥራውን ለማገዝ ነው።

ውለታን የመመለስ ጉዞ

ዋርዴር ከጅግጅጋ 520 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ከተማ ነች። ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ከተማዋ መምጣት የሚፈልግ ቀብሪ በያን፣ ደገሃቡርን፣ ቀብሪ ደሃርን ማለፍ ይጠበቅበታል።

በዚች የገጠር ከተማ በሚገኘው በዋርዴር አጠቃላይ ሆስፒታል ከሚያገለግሉት የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ዶ/ር መሐመድ አሊ አንዱ ናቸው። ተወልደው የፊደል ዘር የለዩትም በዋርዴር መጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሆኑን ይናገራሉ።

ዶ/ር መሐመድ በሚማሩበት ወቅት በትምህርት ቤታቸው የመምህራንና የትምህርት መርጃ መሳሪያ እጥረት በመኖሩ በትምህርታቸው ላቅ ያሉ ተማሪዎች ደከም ያሉትን በመርዳት ያስጠኑ እንደነበር ያስታውሳሉ።

"እኛን ከሚያስጠኑን መካከል እኮ አንዱ መሐመድ ፋራህ ነው። አሁን በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መምህር ነው" የሚሉት ዶ/ር መሐመድ፣ ከዚህ በተለየ ደግሞ በግላቸው ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚያስጠኑ ግለሰቦች ጋርም በመሄድም ያጠኑ እንደነበር ይናገራሉ።

በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ተወልደው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ምሁራን የአካባቢውን ተማሪዎች መማሪያ ክፍላቸው በመገኘት ሲያበረታቱ

የፎቶው ባለመብት, Mohamed farah

የምስሉ መግለጫ, በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ተወልደው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ምሁራን የአካባቢውን ተማሪዎች መማሪያ ክፍላቸው በመገኘት ሲያበረታቱ

በአንድ ወይንም በሁለት ክፍል ይቀድሟቸው የነበሩ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ በማስጠናት በትምህርታቸው እንዲጠነክሩና አሁን የደረሱበት እንዲደርሱ አግዘዋቸዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት አጠናቀው ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመግባት ሕክምና አጠኑ። ከተመረቁ በኋላም እንዲያገለግሉ የተመደቡት የቀለም ዘር በለዩበት፣ እጃቸው እስክርቢቶ ጨብጦ ከወረቀት ባገናኘበት ዋርዴር ሆነ።

እርሳቸውና ጓደኞቻቸው ከትንሽ ብላቴናነት ተነስተው ዶክተር እስኪሆኑ ድረስ በፍቅር አቅፋ፣ በእውቀት እንዲጎለምሱ ያደረገችው ዋርዴር እንደቀድሞው ሆና አልጠበቀቻቸውም።

መስኩ፣ ተራራው ትምህርት ቤቱ ያው ቢሆንም አንድ ነገር ግን ተለውጧል።

ዶ/ር መሐመድ አንደሚሉት የተለወጠው ነገር ከዶሎ ዞን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚገቡት አፍላ ወጣቶች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያነሰ መሄዱ ነበር።

"የተወሰን ነው ምህንድስና፣ የተወሰኑት በሂሳብ ሙያ፣ ቀሪዎቻችን ደግሞ ሕክምና አንዳንዶቹም ዩኒቨርስቲ መምህራን ሆነን ሳለ በአካባቢያችን ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ማነሱ አሳሰበን" ይላሉ ዶ/ር መሐመድ።

ያለ መፍትሔ የማይመጣው ችግር

ከዚያም ሰብሰብ ብለው፤ ለመሆኑ ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት ከአካባቢያችን ወደ ዩኒቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች ቁጥር ምን ያህል ይሆናል ሲሉ ጥናት አደረጉ።

ያገኙት ውጤት ከገመቱት በታች መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር መሐመድ፤ መፍትሄ ያሉትን አስቀመጡ።

ለመሆኑ ተማሪዎቹ ሩ ውጤት ላለማምጣታቸው ምክንያታቸው ምንድን እንደሆነ ለያችሁ?

ዶ/ር መሐመድ፡ አዎ፤ የትምህርት አሰጣጡ ድክመት፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦት አለመኖር፣ የመምህራን እጥረት እንዲሁም አቅም ማነስ መሆናቸውን ለይተናል።

ለይተው ላስቀመጧቸው ችግሮች መፍትሄ ያሉትን ሲዘረዝሩ፤ ለተማሪዎቹ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ቀዳሚው መሆኑን አስቀመጡ።

ለማጠናከሪያ ትምህርቶቹ ደግሞ ከሳይንስ ትምህርቶች ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ ሒሳብና ፊዚክስ ሲመረጡ ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ኢኮኖሚክስ፣ ታሪክና ጂኦግራፊ ተመርጠ። ከቋንቋ እንግሊዘኛም እንዳለበት ዶ/ር መሀመድ ይናገራሉ።

በተማሪዎቹ መካከል የፉክክር መንፈስ ለማኖር በማሰብም ውድድር እንደሚያዘጋጁ፣ እጅ ከሚያጥራቸው ቤተሰቦች ለሚመጡ ተማሪዎች ደግሞ አቅም በፈቀደ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ።

የዋርደር ዞን ተወላጆች ከአካባቢያቸው የሚመጡ ተማሪዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች ላይ ሲወያዩ

የፎቶው ባለመብት, Dr. Mohamed Ali

አቶ መሐመድ ፋራህ በጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ወርዴር ዞን ተወልደውና ተምረው በጅግጅግና በወርዴር የሚገኙ ምሁራን ተገናኝተው በትውልድ ቀያቸው የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት አቀባበል ላይ ያለባቸው ችግር ላይ መወያየታቸውን ያስታውሳሉ።

ከዚህ በመቀጠልም የዞናቸው ተወላጅ የሆኑ ምሁራን በጎ ፈቃደኞችን ለማስተባበር ኃላፊነቱን ከወሰዱት መካከል አንዱ እርሳቸው ናቸው።

ከዋርዴርና አካባቢዋ፣ ዶሎ ዞን፣ የተወለዱና በተለያዩ መስኮች ተመርቀው ሥራ የያዙ እንዲሰባሰቡ ጥሪ በማቅረብም ከ150 በላይ ሰዎች ምላሽ ማግኘታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ስምንት ሰዎች ደግሞ ይህንን በጎ ሀሳብ ለማስተባበር በኮሚቴነት ተመረጡ።

ከዚያም 'ዶሎ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን' በሚል ለስብስባቸው ስም ሰጡ። የሚያደርጉት ድጋፍ በእውቀት፣ በገንዘብ ወይንም በጉልበት ሊሆን እንደሚችል አቶ መሐመድ ፋራህ ያብራራሉ።

ዶ/ር መሐመድ ከሆስፒታል ሥራው በሚተርፈው ሰዓትና በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በዋርዴር ትምህርት ቤት በመገኘት የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የወሰነው ከዚህ መሰባሰብ በኋላ እንደሆነ ይናገራል።

ዶ/ር መሐመድ አሊ በማስተማር ብቻ ሳይሆን የዚህ ኮሚቴ አባል በመሆንም ይሰራል። ኮሚቴው ከተወላጆቹ ገንዘብ በማሰባሰብ ዓላማውን ለመደገፍ እንደሚሰራ የገለፁት ዶ/ር መሐመድ የአካባቢው ማህበረሰብም የተቻለውን ያህል ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆኑን ያብራራሉ።

ዶ/ር መሐመድ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ለማስተማር ሲወስኑ፤ በሚሰሩበት ሆስፒታል እያገለገሉ የሚገኙ ሌሎች ሐኪሞች እነ ዶ/ር አህመድ ናስር እና ተማሪዎቹን ታሪክ ለማስተማር ኃላፊነት የወሰዱት የሒሳብ ባለሙያው ካፊ አህምድ በማስተማሩም ሀሳቡን በመደገፉም አብረዋቸው ለመሆን ተስማምተዋል።

ዶ/ር... አብዛኛውን ጊዜ ተማሪዎች ወገቤን የሚሉት ሒሳብ ላይ ነው። እርስዎ ለምን ባዮሎጂና ኬሚስትሪን ማስተማር መረጡ? ሒሳብ ለምን አያስተምሩም

ዶ/ር መሐመድ እኔ ብቻ ሳልሆን አብዛኛው የሕክምና ተማሪ ሒሳብ ላይ እምብዛም ነው። [ሳቅ] ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ግን የተካንኩበት ነው።

ተማሪ አህመድ አብዲ እነዚህን በጎ ፈቃደኞች ሲመለከት፣ እንደሚበረታታ ይናገራል።"እኛም ለሌሎች አርአያ እንድንሆን፣ ሌሎችን እንድናግዝ እያነሳሱን ነው" በማለት ከእነሱ ቀዬ ወጥተው ተመልሰው ማህበረሰባቸውን በማገዛቸው የተሰማውን ደስታ ይገልጻል።

የዋርዴር ሁለተኛ ደረጃ መምህራኖችም ቢሆኑ ረዳት በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አቶ መሐመድ ፋራህ ያስረዳሉ።

ዶ/ር መሐመድ አሊ እንደሚለው ከሆነ በአካባቢው ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች ያሉ ሲሆን የማጠናከሪያ ትምህርቱና የቁሳቁስ ድጋፉ ለእነርሱም ይሰጣል።

እንደ አቶ መሐመድ ፋራህ ከሆነ በዞኑ ስር በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች የአዳሪ ትምህርት ቤት ለማቋቋም፣ ትልቅ ቤተ መጻህፍት ለመክፈት እቅድ አላቸው።

የአካባቢው አስተዳደርና ማህበረሰብ ምን ይላል?

እነ ዶ/ር መሐመድ ለተወለዱበት አካባቢ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ ለማድረግ ወስነው ወደ ትውልድ ቀያቸው በሄዱበት ወቅት ከአካባቢው አስተዳደሮችና ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር መወያየታቸውን በመጥቀስ በጥሩ መግባባት እንደተቀበሏቸው ይጠቅሳሉ።

"ዶሎሎ ከጅግጅጋ በጣም ሩቅ ነው የምትገኘው። መምህራን ደግሞ ቅርብ ከተሞች ላይ ለመስራት ነው የሚፈልጉት" በማለትም መንግሥት መምህራንን ቢመድብም እጥረት መኖሩን የሚናገሩት አቶ መሐመድ ፋራህ፤ እነርሱ ያለውን ክፍተት በመሙላት እንደሚያግዙ ያስረዳሉ።

በዋርዴር ከተማ ሁለት በአጠቃላይ ዞኑ ደግሞ 19 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራና የቤተ መጻህፍት እጥረት ስላለ የተማሪዎችን አቅም ለማሳደግ ተጨማሪ ድረጋፍ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት አቶ መሐመድ፤ የማጠናከሪያ ትምህርቱን ቅዳሜ አንደሚሰጡ ገልፀው በእውቀታቸው ማገልገል ያልቻሉ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው እንደሚያግዟቸው ያስረዳሉ።

በዋርዴር የተወለዱ እና በጅግጅግ የሚኖሩ በወር አንዴ አልያም ሁለቴ ወደ ስፍራው በመሄድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀው፤ በከተማዋ የሚኖሩና በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ቢሮዎች የሚሰሩ ደግሞ በየሳምንቱ ያስተምራሉ ብለዋል።

አቶ መሐመድ እንዲህ አይነት የበጎ ፈቃድ ሥራ በሰፊው በዞናቸው እንዲሁም በክልሉ እንዲለመድ ፍላጎት እንዳላቸው በመጥቀስም ሌሎች የእነርሱን ጅማሮ ተከትለው መሰባሰብና ሃሳቦችን ማዋጣት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ተማሪ አህመድ በበኩሉ የፈተና ወቅት እየደረሰ መሆኑን በማስታወስ፤ በዚህ ዓመት ባገኘው የማጠናከሪያ ትምህርት ድጋፍ ታግዞ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ተስፋ እንደሚያደርግ ለቢቢሲ ገልጿል።