ለተማሪ ሲፈተኑ የተያዙት ርዕሰ-መምህር 5 ዓመት ተፈረደባቸው

ርዕሰ መምህሩ ቤንጃሚን ማኒራኪዛ

በአንድ ተማሪ ስም የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ሲወስዱ የተያዙት በቡሩንዲ የሚገኝ የአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር በአምስት ዓመት እስራት ተቀጡ።

ቤንጃሚን ማኒራምቦና ከእስሩ በተጨማሪ ለአስር ዓመታት በመምህርነት እንዳያገለግሉ እና በየትኛውም የመንግሥት ሥራ እንዳይሳተፉ ተበይኖባችዋል።

በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ ነበሩ የተባሉት የሒሳብ ባለሙያው ኤሪክ ንኩሩንዚዛ እና መምህሩ ላዛርድ ኒሄዛጊሬ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።

ሁለቱ ርዕሰ-መምህሩን ተባብረዋል በሚል ነው ቅጣቱ የተላለፈባቸው።

ርዕሰ መምህሩና ተባባሪዎቻቸው

ርዕሰ-መምህሩ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ተማሪዎች መውሰድ ያለባቸውን ፈተና ላይ በአንድ ተማሪ ስም ወደ ፈተና ክፍል ገብተው ሲፈተኑ የተያዙት።

በዋና ከተማዋ ቡጁምቡራ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ቡቴሬሬ የቴክኒክ ኮሌጅ ርዕሰ-መምህር የሆኑት ቤንጃሚን ማኒራምቦና የመጨረሻውን የፈተና ወረቀት እየሰሩ ሳለ ነበር ፖሊስና የሃገሪቱን የትምህርት ሚኒስትርን ጨምሮ ባለስልጣናት ወደፈተናው አዳራሽ በመግባት ያፋጠጧቸው።

እጅ ከፍንጅ ተይዘው ማምለጫ ያላገኙት ርዕሰ-መምህሩ ቤንጃሚን የፈፀሙትን ወንጀል እዚያው ፈተና አዳራሽ ውስጥ አምነው ተናዘዋል።