ከአንደኛ ክፍል ዲግሪ እስኪጭኑ ከልጃቸው ጋር የተማሩት አባት

ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ልጃቸው ረመዳን ካሚል

የፎቶው ባለመብት, Remedan Kamil

የምስሉ መግለጫ, ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ልጃቸው ረመዳን ካሚል

ኢማም ናቸው። የዩኒቨርስቲ መምሕር። የስድስት ልጆች አባት። ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም።

የመጀመሪያ ልጃቸው ረመዳን ካሚልን ትምህርት ቤት ሊያስመዘግቡ ሲሄዱ እርሳቸውም አብረው ለመማር ወሰኑ። የምድር የሰማይ ፈጣሪ ምስጋናዬን እንካ፣ የልጄ አንደበት ፊደል ጠራ፣ እጁ ወረቀት ነካ ብለው ብቻ አልቀሩም። አብረውት ፊደል ቆጥረው፣ ዩኒቨርስቲ ገብተው ተመርቀዋል።

እንዴት?

ሼህ ካሚል የባሌ ጎባ ነዋሪ ናቸው። ከወ/ሮ ዘሀራ ሙሐመድ ጋር ተጋብተው ካፈሯቸው ልጆች መካከል ረመዳን ካሚል አሊዩ ለአቅመ ፊደል ሲደርስ ደብተር፣ ቦርሳ ገዝተው፣ እርሳስ ቀርፀው፣ የደንብ ልብስ አሰፍተው ተዘጋጁ።

የነሐሴ ዝናብ አለቅ ብሎ እኝኝ. . . ቢልም እርሳቸው ልጃቸውን ለማስመዝገብ ወደ ቱሉ ዲምቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አመሩ። ያኔ ቱሉ ዲምቱ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር የሚያስተምረው ይላል ረመዳን።

ከዚያ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ስፍራው ላይ ለሚገኙት መምህራን የልጃቸውን ስም ነገሩ። ሼህ ካሚል በአካባቢው የታወቁ የሀይማኖት አባት ናቸው። ማንም ያጠመደ የማያጣቸው ደግሞ ሲቲ ካፌ ነው። ጎባ አለኝ የምትለው ካፌ ሳይሆን አይቀርም።

ስለዚህ ከመምህራኖቹ ጋር ሰላምታ እየተለዋወጡ፣ እየተቀላለዱ ልጃቸውን አስመዝግበው ሲጨርሱ "እስኪ በዚያው ካሚል አልዩ በልና ፃፍ" አሉት መዝጋቢውን መምህር።

"መዝጋቢው ሳቀ" ይላሉ ሼህ ካሚል። ለመማር ፈልገው እንዲመዘግቧቸው መጠየቃቸውን ያመነ አልነበረም። ሼሁ ግን "ቀለም ሀቀኛ ነው። ዝም ብላችሁ ስሜን ፃፉ" አሉ። አሁንም የመዝጋቢዎቹ ሳቃቸው ተራዘመ እንጂ ያመናቸው የለም። እንዲያውም "በሉ ሥራ አያስፈቱን፤ በኋላ ተገናኝተን ሻይ እንጠጣለን። አሁን ይሂዱ" እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።

እኚህ በአካባቢው ባለ መስጂድ በኢማምነት የሚታወቁ አባት፣ በጎባ የአገር ሽማግሌነት የተከበሩ ሰው፤ ልማር ብለው ፈትረው መያዛቸው መምህሮቹን ስለከበዳቸው መዘገቧቸው።

"ፎቶ ይዘዋል?" ተጠየቁ። ሰጡ።

የእርሳቸውንም የልጃቸውንም መመዝገብ የሚያሳይ ብጣቂ ወረቀት ይዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። አንደኛ ክፍል ገቡ! ይህ የሆነው በ1993 ዓ. ም. ነው።

ትምህርት የተጀመረ ዕለት እርሳቸውም ልጃቸውም ደብተራቸው ሸክፈው የትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲደርሱ፤ መምህር አለማየሁ ግቢ ውስጥ ይንጎራደዳሉ፤ መምህሩ የእንግሊዘኛ አስተማሪ መሆናቸውን ሼሁ ያውቃሉ።

"ልጅ ይዘው መጡ ሼኪ?" አሉ መምህር አለማየሁ፤ እርሳቸውም እንደዋዛ "ልጅም አመጣሁ፤ ራሴም መጣሁ" ሲሉ መለሱ።

የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ገብተው፣ መምህሩም በስፍራው ተሰይሞ በሩ ተዘግቶ ነው የደረሱት።

በሩን ሲቆረቁሩ መምህር አለማየሁ ልጁን ትተው እንዲሄዱ ነገሯቸው። "አይ እገባለሁ" ቢሉም መምህሩ ግን "ሲቲ ካፌ እንገናኝ፤ አሁን ልጁን ትተው ይሂዱ" አሉ። እርሳቸውም ልጃቸውም የተመዘገቡበትን ወረቀት አሳይተው ገቡ።

ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ልጃቸው ረመዳን ካሚል በአርባ ምንጭ ሲዝናኑ

የፎቶው ባለመብት, Remedan Kamil

የምስሉ መግለጫ, ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ልጃቸው ረመዳን ካሚል በአርባ ምንጭ ሲዝናኑ

ቢቢሲ- ትምህርት ቤት ሲጀመር ወደ ክፍል ሲገቡ የክፍሉ ይዞታ ምን ይመስል ነበር?

ካሚል- ክፍሉ አቧራ ነው። እኔ በሕፃናቱ መካከል ስታይ ግመል ነው የማክለው። ክፍሉ ውስጥ መምህሩ ወረቀቴን አይቶ ስገባ ተማሪዎቹ ተነስተው "Akkam bultan barsiisaa?" አሉኝ። (ሳቅ) የደነገጥኩት ድንጋጤ. . . አቦ. . . ላብ አላበኝ አንተ. . . እንደምን አደሩ መምህር አሉኝ እኮ! (ሳቅ) ያው አንድ ኢብራሂም የሚባል ልጅ አለ። እርሱ ልጅ ቢሆንም ከሌሎቹ ረዥም ስለሆነ የመጨረሻ መደዳ ነበር የተቀመጠው። እርሱ ጋር ሄጄ ተቀመጥኩ። ልጆቹ በሞላ ወደ ሠሌዳው ማየታቸውን ትተው እኔን ዞረው እያዩ ክፍለ ጊዜው አበቃ።

ቢቢሲ- በእረፍት ጊዜ ከእነማን ጋር ይጫወቱ ነበር? ጓደኛ ነበርዎ?

ካሚል- በእረፍት ሰዓት ወጥቼ የምጫወተው ጓደኛ የለም። አንድ ቶጎና የምትባል ወንዝ አለች። እርሷ ጋር ወርጄ፣ ተጣጥቤ፣ የእረፍት ጊዜዬን እዚያ አሳልፍ ነበር። ጓደኛ ምንም የለም።

ቢቢሲ- በስፖርት ክፍለ ጊዜስ ከሕፃናት ጋር መሯሯጥ አልተቸገሩም?

ካሚል- ያው የስፖርት ነገር ታውቃለህ [ዝላይ አያጣውም]። አንዱ ጎንበስ ብሎ ሌላኛው በእርሱ ላይ ይዘላል። ተሰልፈን ተራዬ ደርሶ ጎንበስ ስል (ሳቅ) አልቻሉም። ተማሪው መዝለል አቅቶታል፤ ትልቅ ሆኜበት። መምህራችን 'Gadi cisaafii Sheekii gadi ciisaafii' አለኝ።

ቢቢሲ- ምን ማለት ነው?

ካሚል- ተኙላቸው ማለቱ ነው። ልጁ መዝለል ስላልቻለ። አንድ ቀን ዩኒፎርሜን ሳላጓድል። የሰልፍ ሥነ ሥርዓት ሳላጓድል። አንድ ቀን አርፍጄ በር ላይ ሳልቆም ነው [ትምህርቴን የጨረስኩት]።

ቢቢሲ- ለመሆኑ የኦሮሚያን ሕዝብ መዝሙር ዘምረዋል?

ካሚል- (በዜማ) Oromiyaa haadha seenaa guddaa. . . [ኦሮሚያ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት]. . . እያልኩ ነዋ! መዝሙሩ ቀላል መሰለህ። እንደዚያ እየዘመርን ነው ያሳለፍነው። አንድ የማስታውሰው ነገር አለ፤ ታውቃለህ [መዝሙር ብትል] ዘርፌ ትባላለች የሙዚቃ አስተማሪያችን። ክፍል ውስጥ ሙዚቃ እያዘፈነች ማርክ ስትሰጥ፣ ተራው እኔ ጋር ደረሰ። እኔ ደግሞ መንዙማና ነሺዳ እንጂ ይሄ የሚዘፈነውን አላውቅም። ልታልፈኝ ስትል መምህር እኔም ልበል አልኳት።

ቢቢሲ- ሊዘፍኑ ማለት ነው?

ሼክ ካሚል- አዎ አስር ማርክ አለው እኮ። "በል" አለችኝ። ተነስቼ፣ ምንም የማላውቀው ሰውዬ [በዜማ] Iyyaaseen iyyoosaa, yuusee taree. . . (ሳቅ) [ይህ ዜማ በዚያ አካባቢ የሚዜም የሕዝብ ዘፈን ሲሆን ትክክለኛው ግጥሙ እንዲህ ነው። Iyyaaseen iyyoosaa kan foolinn shittoodhaa, siyaadeen marookoo] ግጥሙን ዛሬ ድረስ አላውቀውም። መምህሯ እየሳቀች ተማሪዎቹም እየሳቁብኝ ክፍለ ጊዜው አለቀ።

ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Remedan Kamil

የምስሉ መግለጫ, ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም እና ባለቤታቸው

የአባትና ልጅ ፉክክር

ረመዳን ካሚል ከአባቱ ጋር ሲማር የነበረውን ፉክክር ያስታውሳል። የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳሉ አባቱ ከክፍሉ መጨረሻ ተቀምጠው ከክፍላቸው ግን ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዙ እርሱ "ልጅነት አታልሎኝ በለጠኝ" ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳል።

አባትና ልጅ አንድ ክፍል ተምረው፣ አብረው አጥንተው፣ በአንድነት የቤት ሥራ ሠርተው ለፈተና ሲቀመጡ፤ አንዱ ከአንዱ ለመብለጥ ቀን ከሌት ይጣጣሩ እንደነበር ይናገራሉ።

የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈትነው ዘጠነኛ ክፍል ጎባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ ግን ታሪክ ተቀየረ።

ረመዳን እንደሚለው አባቱ የራሳቸውን የክፍል ጓደኞች አበጁ። እርሱም ጓደኞች አደረጀ፤ ያኔ ፉክክሩ ተሟሟቀ። "እኔ" ይላል ረመዳን፣ "ሒሳብና ፊዚክስ ቶሎ ይገባኛል፤ አባቴ ደግሞ እንዳስረዳው ይጠይቀኛል። አሁን እንደተረዳሁት ትዕግስት የለኝም ነበር። አባቴ 'አንተ ያሳወቅኸውን ለሌሎች ማሳወቅ አትፈልግም እንዴ?' ብሎ የምንጨቃጨቀውን አስታውሳለሁ" ይላል።

እርሳቸውም ቢሆኑ ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ረመዳን የቀዳሚነቱን ደረጃ መያዙን ይመሰክራሉ። እርሱም ይህንኑ ያጠናክራል።

አንድ ቀን ማታ ይላሉ ሼህ ካሚል፤ እርሱም ይህንን አጋጣሚ አይረሳውም፤ አብረው ሲያጠኑ አምሽተው ዞር ብለው ሲያዩት አይኑ እንቅልፍ ተኩሏል። አባትነታቸው ያዛቸውና "እንቅልፍህ መጣ" አሉት። እርሱ ግን ትንሽ ልቡ በፉክክር ዳገት ላይ ልትፈርስ ጫና ጫና ትተነፍስበታለች። "አይ" አለ።

"ሂድ ተኛ" አሉ ሼህ ካሚል። "እሺ" ብሎ እግሩን እየጎተተ ወደ አልጋው አመራ። ጎኑ አልጋ ቢነካም ልቡ ግን እሺ አላለውም። "በብርድ ልብስ ተሸፍኜ አጮልቄ ስመለከተው እርሱ ቁጭ ብሎ ያጠናል" ይላል ረመዳን ሁኔታውን ሲያስታውስ። ከዚያ በፉክክር ሜዳ ሊበለጥ መሆኑን ሲያስብ እመር ብሎ ተነስቶ ውሃ በሳፋ አድርጎ እግሩን ዘፍዝፎ ማጥናት ጀመረ።

ሼህ ካሚል "በነገራችን ላይ እንደዚያ ተነስቶ አጥንቶ በልጦኛል" ይላሉ።

በርግጥ ስምንተኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እርሳቸው ቢበልጡትም፤ 10ኛ ክፍል ግን እርሱ 3.6 ሲያመጣ እርሳቸው 3.4 እንዳመጡ ያስታውሳሉ።

ወደ መሰናዶ መሸጋገራቸውን ሲያውቁ ቁጭ ብለው ተመካከሩ። ምክሩ እንዲህ የሚል ነበር። "ከአንድ ቤት በተመሳሳይ ፊልድ ከምናጠና፤ እኔ ማኅበራዊ ሳይንስ አንተ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ አጥና።"

ምክራቸው ሰመረ። ውጤታቸውን አይተው ባቱ ተራራ መሰናዶ ትምህርት ቤት ሲገቡ እንደተመካከሩት በተለያየ ትምህርት ክፍል ተማሩ።

በኋላም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ጥሩ ውጤት ስላመጡ እርሳቸው መደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ሲመደቡ እርሱ ደግሞ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ደረሰው።

እርሳቸው በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ሲያጠኑ እርሱ ደግሞ ሀይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ተማረ።

እንደው አንተም እርሳቸውም የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆናችሁ ገንዘብ ላኩልኝ ብለህ የምትደውለው ለአባትህ ነበር? የኛ ጥያቄ ነው ለረመዳን።

"እንዴ ታዲያ ለማን እደውላለሁ ብለህ ነው። እናቴ ከየት ታመጣለች" በማለት አባቱ እየተማሩም፣ መስጂድ ውስጥ በማገልገል፤ አነስተኛ ገቢ ያገኙ እንደነበር ያንንም ለቤተሰቡና ለእርሱ በማካፈል እንደተማሩ ያስታውሳል።

እርሳቸው በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ ሦስት ዓመት ተምረው በ2007 ሲመረቁ፤ እርሱ ደግሞ ገና ሁለት ዓመት ይቀረው ነበር። እርሳቸው ከፍተኛ ውጤት ስላመጡ ዩኒቨርስቲው አስቀርቷቸው እዛው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲያጠኑ ተደረገ።

ከዚያም በ2009 ዓ. ም. እርሳቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲይዙ ረመዳን ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪውን ስለጨረሰ አርባ ምንጭ ድረስ ጋወናቸውን ይዘው ሄደው እንዳስመረቁት ያስታውሳሉ።

እኩል ትምህርት ጀምራችሁ ቀደሙህ? ስንለውም፤ "ተቀደምኩ የሚለው ስሜት አለ። ግን እንደምደርስ አውቃለሁ። አባት አይደል? ልጅ አይቀድመውም" በማለት ከሳቀ በኋላ፤ እርሱም የአባቱን ብርታት በመከተል ሁለተኛ ዲግሪውን እየተማረ እንደሆነና በአሁን ሰዓት ለማጠናቀቅ የምርምር ሥራ ላይ መሆኑን አውግቶናል።

እንዲህ አባትና ልጅ ሲፎካከሩ የረመዳን ታናናሾችም ብርታት ሰንቀው መጎበዛቸውን ሁለቱም ያስታውሳሉ።

ሼህ ካሚል ባለቤታቸውን እንዲማሩ እንደገፋፏቸው ነገር ግን ከስድስተኛ ክፍል በላይ መግፋት እንዳልቻሉ ይናገራል። ረመዳንም ስለ እናቱ "እናታችን ባትኖር እኛ ዛሬ የደረስንበት አንደርስም ነበር። አባቴን ሁሌም የምለው እናቴን ስለመረጥክ አመሰግናለሁ ነው" ይላል።

ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም፣ ልጃቸው ረመዳን ካሚል እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Remedan Kamil

የምስሉ መግለጫ, ሼህ ካሚል አሊዩ ቃሲም፣ ልጃቸው ረመዳን ካሚል እና ባለቤታቸው

የአባ ጥበቡ ቁምላቸው ምስክርነት

አባ ጥበቡና ሼህ ካሚል ጓደኛሞች ናቸው። እርሳቸው የሚያገለግሉት ጎባ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ነው። እውቂያቸው የሚጀምረውም ሁለቱም በሀይማኖት አባትነት በሚገናኙበት ወቅት ነው።

ሼህ ካሚል እየተማሩ የጓደኛቸው አለመማር ሲያሳስባቸው "አባ ትምህርት ተምረዋል ወይ? ብለው ጠየቋቸው" ይኼኔ "ለምን ጠየቅከኝ?" ብለው መበሳጨታቸውን አባ ጥበቡ ያስታውሳሉ።

እኔ የሐይማኖት አባት የሆንኩት ሳልማር ነወይ? በሚል ቅሬታ ቢገባቸውም፤ ሼህ ካሚል "ዓለማዊ ትምህርት እኮ ነው ያልኩት" አሏቸው ።

አባ ጥበቡ፤ "እርሱንስ አልተማርኩም" በማለት ሲመልሱ፤ ሼህ ካሚል ደብተርና እርሳስ ገዝተው፣ ኡርጂ በሬሳ የሚባል ትምህርት ቤት እንዳስመዘገቧቸው ያስታውሳሉ።

አሁን ጎባ በሚገኘው እናት ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆኑት አባ ጥበቡ፤ የሼኪን ውለታ አንስተው አይጠግቡም። "እኔ ኤቢሲዲ ቆጥሬ ይበቃኛል ስል እርሳቸው እለት በእለት እያበረታቱኝ ነው የተማርኩት" የሚሉት አባ ጥበቡ፤ ኦሮምኛ ስለማላውቅ የምማርበት ድረስ እየመጡ ያስጠኑኝ ነበር ይላሉ።

ሼህ ካሚል ለአባ ጥበቡ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ትምህርት መቅሰም ምክንያት ሆነዋል። ሼህ ሁሴን ሂፈኑን እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። "ይኸው እኔን አይቶ መማር ጀምሮ አራተኛ ክፍል ደርሷል" በማለት የእርሳቸው መማር ለሌሎች የብርታት ስንቅ መሆኑን ይመሰክራሉ።

ሼህ ካሚል ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመሥራት ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው አጫውተውናል። "እድሉ ከተገኘ አላቅማማም። ጨርቄን ማቄን አልልም" ሲሉም ያላቸውን ቁርጠኝነት ይናገራሉ።

ለመሆኑ ዕድሜዎ ስንት ሆነ? የእኛ ጥያቄ ነው።

ሀምሳ አይሆነኝም ብለህ ነው? ጥያቄያችንን በጥያቄ መለሱ!

ቃለ መጠይቁን ከመቋጨታችን በፊት ዕድሜ ከጤና ይስጥልን አልን!