በወለደች በ30 ደቂቃ ውስጥ የተፈተነችው ተማሪ ስንት አስመዘገበች?

የፎቶው ባለመብት, ILU ABBA BOR ZONE COMMUNICATION OFFICE
ልጇ ሦስት ወር ሆኖታል። የደከምሽበት ነውና ስም የማውጣቱ እድል ላንች ተሰጥቶሻል ስለተባለች 'ይዲዲያ' ብለዋለች። እሷ እንዳለችው 'ይዲዲያ' የመፅሐፍ ቅዱስ ስም ሲሆን 'እግዚአብሔር ይመስገን' ማለት ነው።
ስሙ የተወለደበትን ሁኔታ ገልጦልኛል ትላለች። በእርግጥ የአካባቢው ሰው፤ ጎረቤቱም የተለያዩ መጠሪያ ስሞችን አውጥተውለታል። ከእነዚህ መካከል በተማረችበት ትምህርት ቤት ስም 'አብዲ ቦሪ' ብላችሁት ጥሩት ያሏቸውም ነበሩ።
'አብዲ ቦሪ' ማለት የኦሮምኛ ቃል ሲሆን 'የነገ ተስፋ' ማለት ነው ብሎናል የሕፃኑ አባት አቶ ታደሰ ቱሉ። ሌሎችም ስሞች ወጥተውለታል። ግን እናቱ ያወጣችለት ይበልጣል ብለው እርሱ ቢፀድቅም 'አብዲ ቦሪ' ሁለተኛ መጠሪያው ሆኗል።
አልማዝ ደረሰ ባሳለፍነው ዓመት በ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሃገር አቀፍ ፈተና ወቅት ከወለዱ ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። አልማዝ ከወለደች ከ30 ደቂቃ በኋላ ነበር ፈተና ላይ የተቀመጠችው።
የኢሉአባቦራ ዞን፤ መቱ ከተማ ነዋሪ የሆነችው አልማዝ ደረሰ ነፍሰጡር ሆና ትምህርት ቤት ተመላልሳ፤ ከወለደች ከ30 ደቂቃ በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ሆና ፈተና ላይ ብትቀመጥም ያመጣችው ውጤት ግን ለመላው ቤተሰቡ ደስታን የሸለመ ነበር። አልማዝ 3.0 ውጤት በማስመዝገብ ወደ 11ኛ ክፍል አልፋለች።
"ስፈተን ሕመም ላይ ስለነበርኩ ይህንን ውጤት አልጠበቅኩም ነበር፤ ቢሆንም አሁን ላይ ውጤቴን ሳይ በጣም ደስ ብሎኛል" ትላለች አልማዝ።
አልማዝ እንደምትለው በፈተና ወቅት ምጥ ባይፈትናት ከዚህ በላይ ውጤት ልታስመዘግብ እንደምትችል ትናገራለች።
ፈተናው ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የትምህርት ጊዜም ነፍሰጡር ሆና ነው ትምህርቷን የተከታተለችው። የእርግዝናዋ የመጀመሪያዎቹ ወራት ፈታኝ ቢሆኑም ፅንሱ እየገፋ ሲመጣ መነሳት፣ መቀመጥ፣ መተኛት ቢቸግራትም አልተሸነፈችም። እንዲያውም "ማታ ማታ ለመተኛት ስለማይመቸኝ፤ ቁጭ ብየ አጠና ነበር" ስትል አለመመቸትን ወደ ውጤት መለወጥ እንደቻለች ታስረዳለች።
አልማዝ በትዳር 4 ዓመታትን አስቆጥራለች። እስከ ሰባት ዓመቷ ድረስ ከወላጆቿ ጋር ሆና ብታሳልፍም፤ የሚኖሩት ገጠር በመሆኑ ከሰባት ዓመቷ በኋላ እናስተምራታለን ያሉ ዘመዶቿ ጋ ወደ ከተማ ሄዳ እንደነበር ታስታውሳለች። በወቅቱም በቤት ውስጥ የሥራ ጫና ነበረባት። በመሆኑም ትምህርቷን በተለያየ ጊዜ ለማቋረጥ ተገዳ ነበር።
በዚያ የተነሳ ትዳር ወደ መመስረቱ እንዳዘነበለች እና ትዳር ከመሰረተች በኋላም ትምህርቷን እንደቀጠለች ከዚያም ሳታቋርጥ እዚህ እንደደረሰች ትናገራለች።
"ባለቤቴ እንድማር ብቻ ነበር የሚፈልገው፤ ተማሪ በርቺ እያለ ሁሉንም እያሟላ ይደግፈኝ ነበር" ስትል ስለባለቤቷ ያልተቆጠበ ድጋፍ ታስታውሳለች።

የፎቶው ባለመብት, AlMAZ DERESE
ወደፊት መሐንዲስ መሆን እንደምትፈልግ የምትናገረው አልማዝ አሁንም ትምህርቷን ጠንክራ እንደምትቀጥል ትናገራለች።
"ልጅ እያደገ ሲመጣ ያጓጓል" የምትለው አልማዝ ልጇን ባየች ቁጥር፤ ያኔ የነበረባትን ጭንቅ፣ ፈተናው፣ ነፍሰጡር ሆና ወደ ትምህርት ቤት መመላለሷ ትውስ እንደሚላት ትገልጻለች።
አልማዝ ከባላቤቷ ባሻገር በትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራንና ተማሪዎች ድጋፍ እና እንክብካቤ ያደርጉላት እንደነበር ግን ሳትጠቅስ አላለፈችም።
የእንጨት ሥራ ባለሙያ የሆነው ባለቤቷ አቶ ታደሰ ቱሉ በወቅቱ አልማዝ በምጥ ተይዛ ሆስፒታል ውስጥ ጭንቅ ላይ እያለች፤ በሠላም እንደምትወልድ እርግጠኛ በመሆኑ ፈተናዋ እንዳያልፋት ለማመቻቸት ላይ ታች ይል ስለነበር በሠላም የመገላገሏ ዜና የተነገረውም በስልክ ነው።
ከዚህ ቀደም በፈተና ወቅት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉና መፈተን እንደሚችሉ ግንዛቤው ስለነበረው፤ ባለቤቱ የደከመችበት በከንቱ አይቀርም በማለት ከልጁን በሰላም የመወለድ ዜና ባሻገር የፈተናዋን ጉዳይ በቅርበት ይከታተል ነበር።
"ባለቤቴ ነፈሰጡር ሆናም በጣም ጠንካራ ነበረች፤ ስትንቀሳቀስ የነበረው ነፍሰጡር እንዳልሆነች ሴት ነበር። በቤት ውስጥ እኔና እሷ ብቻ ስለነበርን እኔንም ለመርዳት ጥረት ታደርግ ነበር" ይላል። ታዲያ እሱም ቢሆን ከጎኗ ነበር።
ጥንዶቹ በእርግዝናዋ ጊዜም ቢሆን ትምህርቷን ስለማጠናቀቅ እንጂ አንድም ቀን ስለማቋረጥ በጭራሽ አስበውትም፤ ተነጋግረውበትም አያወቁም።
"ፈተናው ከተጀመረ በኋላ ምጥ ይመጣባታል የሚል ፍራቻ ነበረኝ፤ ግን ቀደም ብሎ ነው ምጥ የመጣው፤ ከፈተናው በፊትም አስቀድማ ወለደች፤ እኔም በጣም ደስ አለኝ'" ይላል።
አቶ ታደሰ እንደሚለው ባለቤቱ ፈተና ላይ ምጥ ባይገጥማት ከዚህ በላይ ውጤት እንደምታስመዘግብ እርግጠኛ ነበር- በትምህርቷ ከፍተኛ ውጤት የምታስመዘግብ ተማሪ እንደነበረችና ከክፍሏም የደረጃ ተማሪ እንደነበረች በመጥቀስ።
ቢሆንም ግን ያንን ሁሉ ፈተና ተቋቁማ ይህንን ነጥብ በማስመዝገቧ መደሰቱን ገልጿል።
ወደ 11ኛ ክፍል መግቢያ የመቁረጫ ነጥብ ለመደበኛ፣ ለማታ እና ለግል ተፈታኝ ተማሪዎች ለወንድ 2.00 እና ከዚያ በላይ ለሴት ደግሞ 1.86 እና ከዚያ በላይ መሆኑን የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል።
በ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወቅት በመላ አገሪቱ 28 ሴት ተማሪዎች መውለዳቸው ይታወሳል፤ ነገር ግን ምን ያህሎቹ ወደ የሚቀጥለው ደረጃ እንደተሻገሩ ከኤጀንሲው ለማወቅ በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።














