"ብልጽግናን የሚቀላቀሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ይኖራሉ" ነብዩ ስሁል

ነብዩ ስሁል

የፎቶው ባለመብት, ETV

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው ያለው በትግራይ ክልል የታቀደው ምርጫ ዛሬ እየተካሄደ ነው። አገሪቱን እየመራ የሚገኘው ፓርቲ ብልጽግና የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል ምርጫው ሕጋዊ አይደለም ይላሉ።

አቶ ነብዩ በትግራይ ክልል ስለሚካሄደው ምርጫና ፓርቲያቸው በክልሉ ውስጥ ስላለው እንቅስቃሴ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ዋዜማ ላይ ነን ብዙ ሲባል ነበር፤ ሁሉን አልፎ እውን ሊሆን ነው ትልቅ መነጋገያ ለመሆን በቅቷል እናንተ ምርጫው ሕገ ወጥ ነው ብትሉም ለመካሄድ ጫፍ ላይ ደርሷል። ታዲያ በዚህ ወቅት ከሕዝባችሁ የመነጠል ስሜት አይሰማችሁም?

ምርጫ እየተካሄደ አይደለም። ህወሓት እያካሄደ ያለው ምርጫ ሳይሆን እንዲሁ የዲሞክራሲ ልምምድ እያደረገ እንደሆነ ነው እኛ የምናየው፤ የምንገመግመው። ምክንያቱም አንድን እንቅስቃሴ ምርጫ ለማለት መስፈርቶች አሉ። ምርጫው ደግሞ እነዚያን መስፈርቶች አያማሏም።

ከመሠረታዊ ነገር ስንጀምር ሕጋዊ አይደለም። ሕጋዊ ያልሆነው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ስለማይፈቅደው ነው። ሁለተኛ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ አለ። በተደጋጋሚ ነው ይሄንን ውሳኔ ያሳለፈው። ከቀናት በፊትም አጽድቆታል። ስለዚህ አንድ ምርጫ፤ ምርጫ እንዲባል የመጀመሪያው መስፈርቱ ሕጋዊ መሆኑ ነው። ስለዚህ ሕጋዊ ስላልሆነ ምርጫ ብለንም መጥራት የለብንም።

በሌላ በኩል ምርጫ የይስሙላ ምርጫ ነው። ህወሓት አጀንዳ ስላጣ እያደረገው ያለው ቀቢጸ ተስፋዊ ሂደት ነው። ይሄ ደግሞ ምንም ዋጋ የለውም። አብዛኛዎቹን መስፈርቶች አላሟላም፣ የሕዝባችንም ፍላጎት አይደለም፣ እውነተኛ የምርጫ ሂደትን የተከተለና ተአማኒ አይደለም። ስለዚህ በዚህ መልኩ ስናየው ምርጫ ብለን መጥራት አንችልም።

እኛ ህጋዊ ምርጫ እስከሚመጣ ድረስ እየጠበቅን ነው። ከሕዝባችን የመለየት ስሜት ፍጹም ሊሰማን አይችልም። ሕዝባችንም ሕጋዊ ምርጫ እየጠበቀ እንደሆነ ነው እኛ የምናውቀው።

የትግራይ ሕዝብም ሕግ አክብሮ፣ ሐሳቦች በትክክል ተንሸራሽረው፣ እውነተኛ ምርጫ ተካሂዶ፣ በሕዝብ የተመረጠ ፓርቲ መንግሥት ሆኖ እንዲመራው ነው የሚፈልገው፤ ለዚህም ነው የታገለው።

ከትግራይ ሕዝብ ታሪክም አንጻር ስናየው የትግራይ ፍላጎት ይሄ ነው እንጂ በጨረባ ምርጫ፣ የውሸት ምርጫ አድርጎ መንግሥት መሰየም አይፈልግም። ስለዚህ የመነጠል ስሜት አይሰማንም።

የሕዝባችን ፍላጎት አይደለም የሚል ነገር አንስተዋል፤ እንደምናየው ከሆነ ሕዝቡ በንቃት ተሳትፎ እያደረገ ነው። ክርክሮች እየተካሄዱ ነው፤ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መነቃቃት አለ፡፡ እርስዎ ደግሞ የህዝባችን ፍላጎት አይደለም እያሉ ነው፡፡ መቼስ ሁለት የትግራይ ሕዝብ የለም፡፡ እና የሕዝባችን ፍላጎት አይደለም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው፡፡ መለኪያችሁ ምንድነው? ሕዝቡ ተገደን ነው የምንመርጠው ሲል አልሰማነው'ኮ፡፡

እንግዲህ ስትጨቆን ተጨቁኛለሁ ለማለት እንኳን ነጻነት ያስፈልግሃል። የትግራይ ሕዝብ አይደለም በዚህ ደረጃ ወጥቶ ይሄ ምርጫ ሕጋዊ አይደለም ብሎ ለመውጣት ይቅርና ለመኖርም ለሕይወቱም እየሰጋ ያለበት ከፍተኛ አፈና ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ነጻነቱ ተረጋግጦለት የትግራይ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ቢጠየቅ በትክክል ይሄንን ሊፈልገው አይችልም።

ምክንያቱም የታገለለትና የኖረለት ዓላማ ይሄ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ የታገለውና የኖረው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ጸንታ እንድትኖር፣ በሕግና በሥርዓት እንዲተዳደር፣ ዴሞክራሲና ልማት እንዲጎናጸፍና ከኢትዮጵያዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ለመኖር ነው።

ነገር ግን በዚህ መልኩ ተነጥሎ የጭቆና ገፈት እየቀመሰ፣ አገር ይበዘብዝና ይመዘምዝ የነበረ አንድ ቡድን መፈንጫ ሆኖ ባለበት ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት እየተንጸባረቀ ነው ለማለት በጣም አስቸጋሪ ነው።

ያየናቸው የፖለቲካ ክርክሮችም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከህወሓት ጋር የጥገኝነት ግንኙነት ያላቸው፣ እንዲሁም አቅም ፈጥረው መገዳዳርና መወዳደር የማይችሉ፣ በቅርብ ጊዜ በደም ፍላትና በአንዳንድ ጊዜያዊ ቅሬታዎች የተፈጠሩ ናቸው።

እናም ይሄ የትግራይ ሕዝብን የሚመጥን አይደለም። ያየኸው የሚዲያ ድራማ የትግራይን ሕዝብ ፍጹም የማይመጥን ነው። አብዛኞቹ ፓርቲዎች ያኮረፉ በጣም ጽንፈኛ ብሔርተኞች ናቸው። የትግራይ ሕዝብ ደግሞ እንዲህ አይነት ብሔርተኝነት አይፈልግም።

የትግራይ ሕዝብ እራሱን አክብሮ ሌላውንም አክብሮ በትብብር መኖር እንጂ በዚህ መልኩ ከፈጠራት አገር ተነጥሎ መኖር አይሻም። ስለዚህ የታየው ነገር በሙሉ ከትግራይ ሕዝብ ታሪክና ፍላጎት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሕጋዊ ምርጫ ሲካሄድ የተሻለ እንቅስቃሴ፣ የተሻለ የዴሞክራሲ ምህዳር እንደሚፈጠር ምንም ጥርጥር የለውም።

መቀሌ ቢሮ ከፍታችኋል ሲባል ነበር በዋነኛነት የምትንቀሳቀሱትና ቢሯችሁ የሚገኘው ግን በአዲስ አበባ ነው። እርስዎ አሁን ስለ ሕዝቡ ስሜትና ፍላጎት ሲያወሩኝ ከፍ ባለ የእርግጠኝነት ስሜት ነው የሕዝቡን ስሜት በዚያ ደረጃ ለማወቅ ቀረብ ማለት ያለባችሁ አይመስላችሁም? ለመሆኑ ወደ ምትወክሉት ሕዝብ የማትገቡት ለምንድነው? ስለሕዝብ እንዲህ በርቀት ሆኖ ማውራት ድፍረት አይሆንባችሁም?

ሲጀመር እኛ ትግራይ ውስጥ አለን። ትግራይ ውስጥ በጣም ብዙ አመራሮች አሉን፤ ደጋፊዎችም አሉን፤ ቢሮዎችም አሉን። አንድ ሁለት ቢሮ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ የሚሆኑ ብዙ ቢሮዎች አሉን። እኛ አሁን በሚፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ ያልፈለግነው ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ነው።

ይቅርታ ላቋርጥዎ፤ የሚጨበጥ የሚዳሰስ አድራሻና ቢሮ አላችሁ? እዚህ ቦታ እዚያ ቦታ ብለው ሊነግሩኝ ይችላሉ?

አዎ አሉ፤ ምን መሰለህ። እና አሁን በሚፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ ያልቻልነው እንደነገርኩህ በኮቪድ ምክንያት ነው። እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ባጋጠመበት ጊዜ እንደሚታሰበው እንቅስቃሴ አድርጎ አባላት ለመመልመል በምናስበው ደረጃ በሰፊው እንዳንሄድ እራሳችንን ገታ ያደረግነው ነገር ነው። ነገር ግን ብዙ አመራሮች መቀለ ውስጥ ናቸው። አመራሮቹ እንግዲህ አዲስ አበባ ለስልጠና ይመጣሉ፡፡ ከዚህም ወደዚያ ይሄዳሉ።

ይቅርታ በድጋሚ ላቋርጥዎ፡፡ የሚሉኝ አመራሮች በኅቡ ነው የተሰማሩት? እንቅስቃሴያቸው የኅቡ ነው ወይስ በይፋ?

ይንቀሳቀሳሉ ግን ምን መሰለህ። አባሎቻችን ብዙ እክል ይደርስባቸዋል ብዙ ተጽእኖ አለባቸው። ለመንቀሳቀስም ነጻነት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የስምሪቱ ጉዳይ የኛ ጉዳይ ነው። ሁለተኛ በምንፈልገው ደረጃ እየሄደ ነው ያለው። እክሎች ግን አሉ። ከህወሓት ጠብ አጫሪነት ጋ ተያይዞ፣ ግን በቂ ነው።

ትግራይ ውስጥ ያለን እንቅስቃሴ በቂ የሚባል ነው። ለጊዜው አባሎቻችንና ቢሯቸው በደንብ እንዲታወቅ አንፈልግም። ምክንያቱም ብዙ አደጋዎች ሊደርሱ ስለሚችሉና ከጊዜ ወደጊዜም አንዳንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እየተፈጠሩ ስለሆነ፤ የአባሎቻችንና የአመራሮቻችን ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር ግልጽ እንዳይሆኑ የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ።

ነገር ግን እንቅስቃሴያችን አሁንም በቂ ነው ብለን ነው የምናምነው። ትግራይ ውስጥ ያሉ አመራሮች አሉ በቂ እንቅስቃሴም እያደረጉ ነው።

ሁለተኛ ነገር ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ አይደለም የሚገኘው። አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 1.5 ሚሊየን የሚሆኑ ትግራዋይ አሉ። በሌሎች አካባቢዎችም በርካታ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ስለዚህም እናገናቸዋለን፣ አባላትን እንመለምላለን፣ በአጠቃላይ ፓርቲውን ስናየው ደግሞ ብልጽግና አገራዊ ፓርቲ ነው።

ስለዚህ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ አይደለም የምንታገለው። ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ነው የምንታገለው። ስለዚህ ሁሉም አገራችን ነው፤ ሁሉም ትግራዋይ ያለበት፣ ኢትዮጵያዊ ሀሉም የኢትዮጵያ ክፍል ይመለከተናል።

በቀጥታ ከሚመለከተን የትግራይ ሕዝብም ጋር በቂ ተደራሽነት አለን። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ደግሞ ያሉ መዋቅሮች ምን እንደሚመስሉና ያለውን የአባላት ብዛት በትክክለኛው ጊዜ ግልጽ የምናደርግ ይሆናል።

ይቅርታ አቶ ነብዩ፣ ቀደም ሲል በትግራይ ክልል እንደልብ እንዳንንቀሳቀስ ያደረገን የኮቪድ-19 ወረርሽን ነው ብለው ነበር፤ ነገር ግን ኮቪድ-19 አዲስ አበባም አለ። እናንተ ደግሞ በአዲስ አበባ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው።

ኮቪድ-19 ሁሉም ጋር ያለ ችግር ነው። አዲስ አበባ ኮቪድ የለም አላልኩህም። ሁሉም ጋር አለ፤ በመላው ዓለም አለ። እናም ወረርሽኙ የሚያሳድረው ተጽእኖ የታወቀ ነው። ትግራይ ውስጥ አንድ ልዩነት ላስቀምጥ፣ ለምሳሌ ወደ ክልሉ ለመግባት ወደ ለይቶ ማቆያ እንድትገባ ትደረጋለህ። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ሳይሆን ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር ነው።

አዲስ አበባ ላይ ግን ከውጭ አገር ካልሆነ በስተቀር ከክልል የሚመጣ ሰው ለይቶ ማቆያ እንዲገባ አይደረግም። ነገር ግን ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ወደ ትግራይ ስትገባ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት አለ። ይሄ ሆን ተብሎ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ነው። ምንም እንኳን ወረርሽኙ በሁሉም ቦታ ያለ ቢሆንም በትግራይ ግን እንዲህ አይነት ለየት ያሉ ሁኔታዎች አሉ።

ከዚህ በፊት በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ የህወሓት ከፍተኛ አባላት የብልጽግና ትግራይ አባላት ሆነዋል ብለው ተናግረው ነበር። እነማን እንደሆነ መግለጹ አደጋ ስለሆነ ነው ወይስ እንዲሁ ለፕሮፓጋንዳ የተጠቀማችሁት ነገር ነው?

በይፋ ወጥተው የተቀላቀሉ አሉ፤ በየጊዜው ቃለ መጠይቅ ይደረግላቸዋል። ትከታተላቸዋለህ ብዬ አምናለው። ሌሎችም ያ ፍላጎት ያላቸው፤ በግልጽ አባል መሆን እንደሚፈልጉ የሚገልጹ ብዙ የህወሓት አመራሮችና አባላት አሉ። እኛንም ኮሚኒኬት እያደረጉን ያሉ አባላት አሉ።

እነዚህ በከፍተኛ የህወሓት አመራርነት ላይ ያሉ ናቸው?

አዎ አሁንም ያሉና ወደእኛ መምጣት የሚፈልጉ፣ ፍላጎት ያላቸው አሉ። ምክንያቱም ታውቀዋለህ በህወሓት ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚል ተጨምድዶ የተያዘ ብዙ ለውጥ የሚፈልግ ካድሬ አለ። ምናልባት የዴሞክራሲ ባህል ቢመጣ ፓርቲው ውስጥ ስንት ሰው የተለየ ሀሳብ ሊያራምድ እንደሚችልና ወደ ብልጽግና ሊሄድ እንደሚችል፤ ሌላው ቢቀር ድርጅቱን ለቆ የራሱን ሕይወት መኖር የሚፈልግ ምን ያህል እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ፓርቲው ውስጥ አምባገነንነት ስላለ ካድሬው ፍላጎቱን እንዳይገልጽ እንደሚደረግ ለሁላችንም ግልጽ ነው። እናም ይህንን ስንል ፕሮፓጋንዳ አይደለም፤ በተጨባጭ ብዙ የተቀላቀሉን አሉ። አሁን በቀጣይነትም እንደውም በቅርቡ ቃለ መጠይቅ በመስጠት ወደ ብልጽግና መቀላቀላቸውን በይፋ የሚገልጹ ከፍተኛ አመራሮችም አሉ።

ከፍተኛ ሲሉ አቶ ነብዩ በማዕካዊ ኮሚቴ ደረጃ እንደዚያ ማለትዎ ነው?

አዎ። ከላይ ጫፍ ላይ ካሉትም ሊሆን ይችላል።

ይሄ ትልቅ ዜና ነው የሚሆነው መቼስ…

አዎ! ብልጽግናን መቀላቀል የሚፈልጉና የሚቀላቀሉ በቅርቡ ይኖራሉ። እንዳልኩህ ህወሓት ውስጥ ትንሽ የዲሞክራሲ ቅንጣት ቢኖር ብዙ ነገር ይታይ ነበር። ነገር ግን እንደደምታውቀው ህወሓት የአፈና የሴራ ሥርዓት ነው።

ብዙ አመራሮች ብዙ አመራሮች ከድርጅቱ እንዳይወጡ ጫና እንደሚደረግባቸው አንዲሁም እስከመታገትና ወደሌላ እንዳያማትሩ በቤተሰብ ማስፈራራትን የመሳሰሉ በጣም ብዙ ጫናዎች በማድረግ ነው እንጂ አመራሩን ተቆጣጥረው የያዙት፤ ዴሞክራሲ ቢኖር ምናልባት ህወሓት ፈርሶ ሊያድር የሚችል ፓርቲ ነው።

አቶ ነብዩ እርስዎ ላይ ግን በቀጥታም ሆነ በቤተሰብዎ ላይ የደረሰ ዛቻ ወይንም ማስፈራራት አጋጥምዎት ያውቃል?

እኔ ጣጣዬን ጨርሼ መጥቻለሁ። ከዚህ በፊት የግራስሩት እንቅስቃሴ ስለነበረ እዚያ ላይ ብዙ ወከባዎች፣ እስር፣ እንግልትና እስከ 18 ዓመት የሚያስቀጣ ክስ አሁንም ድረስ አለ።

እኔ ያው በዚያ እንቅስቃሴ በመቀሌና በዙሪያዋ ሁለት ዓመት ሙሉ እንቅስቃሴ ነበረ እና እዚያ ብዙ ነገር እኔ ላይ ነው የደረሰው። ቤተሰቤ ላይ የደረስ ብዙም ነገር የለም።

እንቅስቃሴውም ጠንከር ያለ ስለነበረ ፈትነውም እንደማያሸንፉ ስለሚያውቁ ነገርየው ብዙም አልተለጠጠም። ነገር ግን አንዳንድ ተጽእኖዎች ይኖራሉ። ሌላው ቢቀር የሥነልቦና ተጽእኖ ይኖራል ቤተሰብ ላይ። እኔ ላይም ብዙ ነገር ደርሷል። እስከመደብደብ ደርሻለው፤ ታስሬ ወጥቻለው፤ ክስም አለብኝ።

እሱ በሚዲያም ይታወቃል እሱን ማለቴ አልነበረም አቶ ነብዩ፤ ወደዚህ ወደ ብልጽግና ከመጡ ወዲህ ማለቴ ነው የትለየ ነገር አለ?

ወደ ብልጽግና ከመጣሁ በኋላ ብዙም አይደለም ጫናው። ይመስለኛል ተስፋ ቆርጠዋል። መግቢያም ስላጡበት፣ የእኔን አያያዝም፣ የእኔን የትግል ስልትም ስለሚያውቁት ነገርየውን ለመንካት የደፈሩ አይመስለኝም። ሌላው ጋ በጣም ብዙ ጫና ይደርሳል፤ እኔ ጋ ግን እስከዚህም አይደለም። ወይም ደግሞ ለተራ ትንኮሳ እኔን የሚፈልጉኝም አይመስለኝም። ምናልባት ከዚያ በላይ ሌላ ኮንስፓይረሲ ሊኖራቸው ስለሚችል መነካካት አልፈለጉ ሊሆን ይችላል።

ለማንኛውም ይሄ ትግል ነው። የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲከበር ነው እየሰራን ያለነው። ይሄ ደግሞ ቅዱስ አላማ ነው። ይዘነው የተነሳነው ዓላማ ትልቅ ስለሆነም ነው ምንም ማድረግ ያልቻሉት። ሕዝብም ስለሚያየው፣ ብዙ ደጋፊም ስላለው ምንም ማድረግ ስላልቻሉ ይመስለኛል…።

ይህ ማለት አንዳንድ ጫናዎች የሉም ማለት አይደለም። እኔ ጋ ጎልቶ የወጡ ነገርኦች ግን ለጊዜው የሉም።

ጎልተው የወጡ ጫናዎች ከሌሉ ታዲያ አቶ ነብዩ፤ መቼ ነው ወደ ትግራይ የሚሄዱት? መቼ ነበር ለመጨረሻ ጊዜስ ትግራይ የነበሩት?

ያው ቀኑን የመወሰኑ ሥራ የእኛ ነው። የግድ ለሚዲያ መናገር ግዴታም የለብንም፤ ትክክልም አይደለም። ምክንያቱም የደኅንነት ጉዳይም አለበት። ትልቅ የሰኪዩሪቲ ጉዳይ ነው። ከአምባገነን ጋር ነው እየታገልን ያለነው እና በዚህ ሰዓት እንዲህ እናደርጋለን እያልን ሚዲያ ላይ መረጃ መስጠት አይጠበቅብንም። ዞሮ ዞሮ ግን ሥራ ላይ ነን ያለነው።

አዲስ አበባ ላይ አለህ ማለት ሥራ እየሰራህ አይደለም ማለት አይደለም። ትግራይ ተግባራዊ ሥራ የሚሰሩ የዘርፍ አመራሮች አሉ። እኛም የምንሰራውን እዚህ ሆነን እንሰራለን። አስፈላጊ ሆኖ ባገኘነው ጊዜ ደግሞ በይፋ ወደዚያ እንንቀሳቀሳለን። እዚያ ቤዝ እናደርጋለን።

ይሄ ማለት ግን እስካሁን ሥራ እየተሰራ አልነበረም ማለት አይደለም። ከበቂ በላይ ሥራ እየተሰራ ነው። እንዲያውም እኔ እዚህ መቆየቴ በጣም ብዙ ጥቅሞች ነበሩት። እንቅስቃሴ በቦታው ላይ ከመገኘት አንጻር ብቻ መያያዝ የለበትም። አሁን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ነው።

እንዳይሄዱ የሚያደርግዎ ግን ምንድነው፤ ስጋት ነው፤ አይደለም እንዴ?

ስጋት አይደለም። ስጋት ሳይሆን ስትራቴጂና የአስፈላጊነት ደረጃ ነው። አሁን ስለሄድክ ያቀድከውን ነገር ታሳካለህ ማለት አይደለም። የተፈጠረውን የፖለቲካ ድባብ [ክላይሜት] ታውቀዋለህ። ሕዝባችንም እንዲሰጋ አንፈልግም። እኛ ከሄድን ብዙ ሥራ መስራት ስለምንጀምር በተለይ ሕዝቡንም በብዙ ስጋት መወጠር ነው የሚሆነው። ይደርሳል። ሁሉም ነገር ይደርሳል። የትግሉ ሙሉ ቁመናም ጊዜውን ጠብቆ ይደርሳል። ድሉም ይደርሳል። ሁሉም ነገር እጃችን ውስጥ ነው ያለው።

ሕዝባችንም እንዳይጎዳ ማሰብ ስላለብን ነው…። ነገሮችን ካከረርናቸው ዞሮ ዞሮ ሕዝብ ነው የሚጎዳው። ለሕዝብ አስበን ነው እንጂ ሰግተን አይደለም የምለው ለዚህ ነው።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ሕገወጥ ነው ብሎታል እናም ማዕከላዊው መንግሥት ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ ብዙዎች የሚጠብቁት ነው። ለመሆኑ መንግሥት ሊወሰዱ ስለሚችሉ ቀጣይ እርምጃዎች የትግራይ ብልጽግናን ያማከረው ነገር አለ? ያቀረባችሁትስ አማራጭ አለ?

በመጀመሪያ ብልጽግና አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ነው። ስለዚህ በፓርቲያችን በተለይ በቀጥታ ከትግራይ ህዝብ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ የእኛ ሐሳብና ምክር ብዙ ነው ማለት ይቻላል፤ እንደውም እኛ ነን የምንመራው።

ፓርቲና መንግሥት የሚለያዩት መስመር እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። የግድ ሁሉን ነገር እኛ እንወስናለን ማለት አይደለም። የፌደሬሽን ምክር ቤት የራሱ የሆነ አሰራር አለው፤ የራሱ የሆነ ቁመናም አለው። በዚያ ደረጃም መንግሥትና ፓርቲ ተከባብረን ነው የምንሰራው። ስለዚህ ጉዳዩ በዋነኛነት የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። የእኛ ሐሳብም በተለያየ መልኩና መንገድ ይጠየቃል። በተለያየ ውይይት ይነሳል። ሁሌም ሐሳባችን እየተዋሀደ ሄዶ ነው ወደ ውሳኔ የሚደርሰው።

ጦርነት አያስፈግም፤ ለሕዝባችንም ሰላም፣ ጤንነትና ብልጽግና እንጂ ጦርነት ልናሰማው፤ አሁንም ወደ መሰዋዕትነት ልናስገባው አያስፈልግም። የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ ድሮ ያበቃለት ነገር ነው መሆን ያለበት እንጂ አሁንም ኢትዮጵያውያን እርስ በራሳችን የምንዋጋበት ምንም ምክንያትም የለንም።

እንደ ብልጽግናም፤ አይደለም ጦርነት ተብሎ የሚገለጽ ይቅርና ተራ ግጭት እንኳን አስፈላጊ አይደለም ብለን ነው የምናምነው። በተለይ ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት ወይም ግጭት እንዲገጥመው አንፈልግም። የትግራይ ሕዝብም ለነጻነት የታገለው ከመሰዋዕትነት ወደ መሰዋዕትነት እየተገላበጠ ለመኖር አይደለም።

ፓርቲያችንም በሰላም፣ በአንድነት፣ የተሻለና አካታች የሆነ ሥርዓት ተፈጥሮ እንዲኖር ነው የሚፈልገው። የፌደሬሽን ምክር ቤትም የወሰነው ውሳኔ ተቋሙን የሚመጥን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪልነቱን የሚያረጋግጥ፣ በጣም የበሰለና የሰከነ ሰላማዊ ነው።

ምናልባት ሰዎች የጠበቁት ሌላ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምክር ቤቱ መወሰን ያለበትን ነገር ወስኗል።

ከዚያ በኋላ ግን ሲተነተን ምን ሊሆን እንደሚችል አስፈጻሚው አካል ምን እንደሚወስን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደግሞ ምን አይነት ውሳኔ እንደሚወስን አብረን የምናየው ይሆናል።

ናንተ በኩል ለሕዝባችን ይሄ ቢሆን፣ በህሓት ላይ ይሄ ቢደረግ ብላችሁ ያቀረባችሁት ምክረ ሐሳብ ግን የለም?

አኛም ብንሆን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ነው ያሰመርነው። ነግር ግን ሰላም አንድ ወገን ስለፈለገው ብቻ ላይሳካ ይችላል። የማይሳካ ከሆነ በኋላ አይተን፣ ተወያይተን የምንወስነው ነገር ነው የሚሆነው።

ዞሮ ዞሮ ግን ሰላምና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ውሳኔ መወሰን አለበት ብለን ነው የምናምነው። እንግዲህ ነገሮች በጣም እየከፉ የሚሄዱ ከሆነ ከዚህ በላይ እያየን ደግሞ ተገቢ የሆነ ሕጋዊ የሆነ ውሳኔ እየተወሰነ ነው የሚሄደው፤ እሱን ሁላችንም አብረን የምናየው ይሆናል።