ትግራይ ክልል ፡ የልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አማራ ክልል ኮብልለዋል መባሉን አስተባበለ

ስድሳ የሚሆኑ የታጠቁ የትግራይ የልዩ ኃይል አባላት ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን የአማራ ክልል ሲያስታውቅ የትግራይ ክልል በበኩሉ ጉዳዩን "ተረት ተረት ነው" በማለት አጣጥሎታል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ከትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ወደ አማራ ክልል እየመጡ መሆኑን ጠቅሰው 60 የሚሆኑ የታጠቁ የልዩ ኃይል አባላት ወደ ክልሉ ከነትጥቃቸው መግባታቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህ ኃይሎች ከወልቃይትም ከራያ አካባቢ፣ አማራ የሆኑና እና አብዛኛዎቹ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሰው አባላቱን ተቀብለው ትጥቅ በማስፈታት በአንድ ካምፕ ማስቀመጣቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ወደ አማራ ክልል የኮበለሉ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት አሉ ስለመባሉ በቢቢሲ የተጠየቁት የትግራይ የክልል የሕዝብና መንግሥት ግንኙነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐዱሽ ካህሱ፤ "ይህ የበሬ ወለደ ንግግር ካልሆነ በስተቀር እውነት አይደለም" ብለዋል።
"ምናልባት ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ነው እየሄደ ያለው የሚለውን እነርሱ ይመልሱ እንጂ፤ ከትግራይ ወደ አማራ ክልል የሚሄድ የለም" ብለዋል።
በሌላ በኩል አቶ ግዛቸው "የማንነት እና ወሰን ጥያቄን የአማራ ክልላዊ መንግሥት ትቶታል የሚለው ትክክል አይደለም" ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄዎች እያነሳ መሆኑን ጠቁመው የማንነት እና ወሰን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ ሃቀኛ ፌደራሊዝም ትግበራ እና ሌሎችም አቋም የተያዘባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።
ጥያቄዎቹ ውስብስብ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ጥያቄዎቹ በፌደራል ደረጃ የሚመለሱ መሆኑን ጠቁመው ኢኮኖሚ ሪፎርም እና መሠረተ ልማት ላይ የተወሰኑ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
"በወልቃይ እና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች አፈና፣ እስራት እና እንግልት እየደረሰባቸው ነው" ብለዋል። ይህንን ለማስመለሰም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ክልሉ ይንቀሳቀሳል ብለዋል።
"ህወሓት ምርጫ አካሂዳለሁ" ብሎ ሕዝቡን "መከራ እያበላ" ነው ያሉት አቶ ግዛቸው፤ ችግሩ ከዚህ በላይ እየከረረና አደብ የማይገዛ ከሆነ ፌደራል መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር የሚያስችል አቅምና ሥልጣን ስላለው፤ በዚህ መሠረትም ህወሓትና የትግራይ ሕዝብን በመለየት ሕግ ማስከበር እንዳለበት አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።
"አሁንም የወሰን ጥያቄ መኖሩንና የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ እያሉ ነው፤ ነገር ግን ይህን የሚሰማቸው የለም" ብለዋል። በመሆኑም "ከአማራ ክልል በኩል የሚሰማው ወሬ ከተረት ተረት ያለፈ ሐቅ የለውም" ሲሉ አቶ ሐዱሽ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"የአማራ ክልል መንግሥት ለትከንኮሳ አይነሳም" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቸው፤ ክልሉ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ብቻ ነው የሚያስፈልገው የሚል እምነት አለው ብለዋል።
ከወልቃይት እና ጠገዴ ውጭ ያሉ የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎችም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመንግሥት ቀርበው በሕግ እንደሚፈቱ መታወቅ አለበት ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል።
መግለጫውን የሰጡት የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ዳሬክተር ክልሉ ወደ ሠላም ወደ አንድነት የመጣበት ወደ ልማት ፊቱን ያዞረበትና ከሌሎች ክልሎች በተነጻጻሪነት የተሻለ ሠላም ያለበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።















