ምርጫ፡ በትግራይ ክልል ከግማሽ በላይ የግል ተወዳዳሪዎች ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸው ተገለጸ

በትግራይ ክልል ምርጫ ለመወዳደር ከተመዘገቡ 11 የግል ተወዳዳሪዎች መካከል ስድስት ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ መረሳ ፀሐዬ ገለጹ።
በትግራይ ክልል በግል ከሚወዳደሩ ፖለቲከኞች አንዱ አቶ አታክልቲ ገብረሥላሴ ከክልላዊው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ለምርጫ ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙኅን የአየር ሰዓት እንደሚያገኙና የምርጫ ኮሚሽን የሕትመት ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አምነው ውድድሩን ቢቀላቀሉም፤ ለጥያቄዎቻቸው ቀና ምላሽ ባለማግኘታቸው ራሳቸውን ከምርጫው ለማግለል መወሰናቸውን አስረድተዋል።
“በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሰው መሰብሰብና ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ መቀስቀስም አይቻልም። ስለዚህም በራድዮና በቴሌቭዥን መቀስቀስ ካልቻልኩ፣ ወጪዬ ተሸፍኖ በተለያዩ ቦታዎች ሐሳቤን የምገልጽባቸው መግለጫዎች ካልለጠፍኩ እንዴት እቅዴን ለሰው አስተዋውቃለሁ?” ሲሉ ቅሬታቸውን አቶ አታክልቲ ገልጸዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ ድጋፍ ሊሰጣቸው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን የገለጹት ፖለቲከኛው፤ “እቅዴን ለሰው ማሳወቅ ካልቻልኩ በምርጫው መሳተፌ ትርጉም የለውም” ሲሉ አስረድተዋል።
በጀትን በተመለከተ አንስተው የነበረውን ጥያቄ ሲያብራሩም፤ “የኛ ጥያቄ ብር ስጡን ሳይሆን ወጪያችንን ሸፍኑልንና አስፈላጊውን ግብዓት አሟሉልን ነው” ብለዋል።
በክልሉ 11 የግል ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው እንደነበርና፤ ባለፉት ሳምንታት ከበጀት እንዲሁም ከአየር ሰዓት ጋር በተያያዘ ጥያቄና ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል።
አቶ አታክልቲ ባለፉት ጊዜያት የመልካም አስተዳደር እጦትን፣ የመሬት አስተዳደርንና ሥራ አጥነትን በተመለከተ ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር በማስታወስ፤ “ችግሮቹ ሊፈቱ ባለመቻላቸው ቅሬታ ከማቅረብ በዘለለ ምክር ቤት ገብቼ የሕዝቡን ድምጽ ለማሰማትና ምክር ቤቱ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ ለመታገል አስቤ ነበር በምርጫው የተመዘገብኩት” ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም ግን ከኮሚሽኑ የሚጠብቁትን ድጋፍ ባለማግኘታቸው በውድድሩ መግፋት እንዳልቻሉ አስረግጠዋል።
ከክልላዊው ምርጫ ራሳቸውን ካገለሉት መካከል ገሚሱ በምርጫው በግል እጩነት ለመወዳደር የ1 ሺህ ሰው የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ያልቻሉ ሲሆኑ፤ የተቀሩት በጀት ስላልተሰጣቸው እንዲሁም የአየር ሰዓት ባለማግኘታቸው ነው ራሳቸውን ያገለሉት።
የምርጫ ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ፤ በአቅም ውስንነት ምክንያት ለግል ተወዳዳሪዎች የገንዘብ እና የመገናኛ ብዙሃን አየር ሰዓት ማቅረብ እንደማይችል አስታውቋል።
በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ በርካታ ድምጽ ሰጪዎችን እየመዘገበ መሆኑን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መረሳ ፀሐዬ፤ እስከ 2.6 ሚሊዮን ሕዝብ የድምጽ መስጫ ካርድ ይውስዳል ተብሎ ቢጠበቅም፤ እስከ ሀሙስ በሚቆየው ምዝገባ እስከ 3 ሚሊዮን መራጭ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው አስታውቀዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ክልሉ ሄደው የምርጫውን አፈጻጸም መታዘብ ይችላሉ ብለዋል።
አቶ መረሳ በምርጫው የሚወዳደሩት 5 ፓርቲዎች ነሐሴ 17 ቀን 2012 ዓ. ም. የመጀመሪያውን ክርክር ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በቀጣይ 4 ክርክሮች በፓርቲዎች መካከል ይከናወናሉ ብለዋል።














