ጎንደር፡ ጥንታዊው የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጉዳት ደረሰበት

የጉዛራ ቤተ መንግሥት ኢትዮጵያን ከ1556-1589 ዓ.ም ድረስ በመሯት በአፄ ሰርፀ ድንግል የታነፀ ነው

በዘንድሮው ክረምት የሚጥለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጉዛራ ቤተ መንግሥት ጉዳት ደረሰበት።

በዝናብ አማካኝነት ጉዳት የደረሰው ነሐሴ 4 ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ ነው ሲሉ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባይ ምላሹ ጌቱ በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጉዳት የደረሰበት በ1998 ጥገና የተደረገለት የቤተመንግስቱ መወጣጫ ደረጃ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ጥገናው ሙሉ ለሙሉ አለመሆኑ እና ደረጃው ሲጠገንም በአፈር እና ኖራ ቅልቅል መሆኑ ለአደጋው መከሰት ምክንያት ነው ብለዋል።

ዝናቡ አፈሩን በመጥረጉ መወጣጫ ደረጃው መደርመሱን አቶ አባይ አስታውቀዋል።

ከ400 ዓመታት በላይ የቆየው ቅርስ ዝናብ እና ፀሐይ እየተፈራረቀበት አደጋ እንዳንዣበበት በመናገር ኃላፊው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጉዛራ ቤተመንግሥት የደረሰበት አደጋ ከዓለም ቅርስነት መዝገብ እንዳይወጣ ስጋት ይፈጥራል ወይ ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው "ሙሉ ለሙሉ አይደለም የፈረሰው። መወጣጫ ደረጃው ብቻ ነው።

ስለዚህ ከዓለም ቅረስነት የሚያሰርዘው አይደለም የተደረመሰው። በነበረው ልክ አስተካክሎ መስራትም ይችላል። ደረጃውም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን ግማሹ ነው የፈረሰው። ስለዚህ ለመስራት የሚያዳግት ስላልሆነ የሚያሰርዘው አይደለም" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥገና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበበው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ቅርሱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጎንደር አብያተ መንግስታትን ጨምሮ ከሌሎች ስምንት ቅርሶች ጋር መሆኑን ጠቁመዋል።

አደጋው የደረሰው በቅርቡ መለስተኛ ጥገና የተደረገለት የዋናው መግቢያ መወጣጫ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቅርሶቹ ላይ የሚደረጉት ጥገናዎች ሙሉ ጥገና ሳይሆን የተናደ ወይም ያዘመመን የግንብ ክፍል የመደገፍ ዓይነት ሥራ ብቻ እንጂ ተጠቃሎ ሁሉንም የሚያጠቃልል የጥገና ስራ አልተካሄደም ብለዋል።

ለዚህ መፍትሔ ያሉት ደግሞ ሙሉ ጥናት በማካሄድ የጥገና ሥራ ማከናወን ነው።

የጉዛራ ቤተ መንግሥት ኢትዮጵያን ከ1556-1589 ዓ.ም ድረስ በመሯት በአፄ ሰርፀ ድንግል የታነፀ ነው

"የተወሰነውን ክፍል የመጠገን ሥራ አንሠራም። ጥናት ተካሂዶ ሲጠናቀቅ በቅደም ተከተል መሠረት ለሚቀጥሉት ከ50-70 ዓመታት የማያሳስብ ጥገና እንሠራለን። ያንን ለማድረግ ጥናት የሚያደርጉትን አወዳድረን በዋጋም በልምድም ጥሩ የሆኑትን መርጠናል። ልምድ ያላቸው ናቸው። የጥገና ጥናት ውል አዘጋጅተን በሚቀጥለው ሳምንት እንፈራረማለን። መስከረም ጋማሽ ላይ ጥናት ጀምረው በሦስት ወር ያጠቃልላሉ። ያንን ይዘን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንሄዳለን ማለት ነው" ብለዋል።

አበባው አያሌው፤ ጉዛራ ቤተመንግስት ላይ ስለደረሰው ጉዳት በተመለከተ "የፈረሰውን ለመሥራት ግን ጥናቱ እስኪያልቅ አንጠብቅም። አንድ ቡድን ወደ ቦታው ይሄዳል። ያለውን የጉዳት መጠንን እና በአፋጣኝ የሚያስፈልገውን አጥንቶ ይመጣል እንጂ ጥናቱ እስኪያልቅ አንተወውም። ከክልሉ ባህልና ቱሪዝምም ጋር እየተነጋገርን ነው" ሲሉ ምላሻቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጉዛራ ቤተ መንግሥት ኢትዮጵያን ከ1556-1589 ዓ.ም ድረስ በመሯት በአፄ ሰርፀ ድንግል የታነፀ ነው።