ካለሁበት 42 : ''የጠበቀ ቤተሰባዊ ፍቅራቸውና ትስስራቸው ከኢትዮጵያውያን ጋር ያመሳስላቸዋል''

አስመረት በርሄ እንጀራ ስትጋግር

የፎቶው ባለመብት, አስመረት በርሄ

አስመረት በርሄ እባላላሁ። ተወልጄ ያደግኩት ጎንደር ክፍለ ሃገር ሲሆን፤ እ.አ.አ. በ1995 እስራኤል ለጉብኝት መጥቼ ሁኔታው ስለተመቸኝ እዚሁ ቀረሁ። ከአራት ወይም አምስት ወራት በኋላ ትዳር በመመስረቴ ጥሩ የመሰንበት ምክንያት ሆነልኝና ይሀው እዚህ እገኛለሁ።

መቼም ካገርህ ወጥተህ ሌላ ቦታ ስትሄድ ዋናው አስቸጋሪ ነገር ቋንቋ ነው። ምክንያቱም ቋንቋውን የማያውቅ ሰው መስማትም፤ መናገርም እንደማይችል ሰው ነህ ማለት ነው። እኔ ግን እድለኛ ሆኜ አክስቴ ጋር ስለገባሁኝ ብሶቴንና ችግሬን የመግለጽና ሲከፋኝ የምጽናናበት አጋጣሚ ነበረኝ።

ቋንቋውን ለመልመድ አራት ወይም አምስት ወራት ብቻ ነው የፈጀብኝ። ወዲያው ደግሞ ስራ ጀመርኩኝ። በመሃል ግን ፍቅር ያዘኝና ወደ ትዳር አለም ገባሁ። በህይወቴ የተከፋሁበትና ያዘንኩበት ወቅት ደግሞ ፍቅሩ ጠምዶኝ ከሃገሬ ካስቀረኝ ባልቤቴ የተለያየንበት ወቅት ሲሆን፤ የማይድን ጠባሳ ስለጣለብኝ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ መናገር አልፈልግም።

እስራኤል በጣም ቆንጆ ሃገር ናት። ደግሞም የመጀመሪያ የስደት ቦታዬ ስለሆነች ሁለተኛ ሃገሬ ናት። እውነቱን ለመናገር ሃገሬ ያለሁ መስሎ ነው የሚሰማኝ። ወዲያውኑ የፈቃድ ወረቀቴን ስላገኘሁና ሁለት ዓመት ሲሞላኝ ደግሞ አገሬንና ዘመዶቼን ለማየት ዕድል ስላጋጠመኝ እንግዳነት አልተሰማኝም።

ከእስራኤላውያን የምወደው ነገር ማሕበራዊ ኑሯቸውን ነው። ከዛም አልፎ የጠበቀ ቤተሰባዊ ፍቅራቸውና ትስስራቸው ከኢትዮጵያውያን ጋር ያመሳስላቸዋል። ለቤተሰባዊ ፍቅር ትልቅ ቦታ ያላቸው ሲሆን፤ ይሄ ደግሞ ከክቡሩ ባህላችን ጋራ በደንብ ያመሳስለዋል። እስራኤል እንደ አቅምህ ሰርተህ ልትኖርባት የምትችልባት ሃገር ነች። ብዙ ከኢትዮጵያ የሚለያት ነገር ለእኔ አይታየኝም። ምናልባት የከተማ እድገቱና ብልጽግናው ላይመጣጠን ይችላል፤ ሆኖም ግን እኔ በሃገሬ ላይ ያለሁ ስለሚመስለኝ ሰፊ ልዩነት አይታየኝም።

አስመረት በርሄ ቡና ስታፈላ

የፎቶው ባለመብት, አስመረት በርሄ

ሌላኛው እስራኤልውያን ከእኛ ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ደግሞ የእንግዳ አክብሮት፤ አቀባበል፤ ቤተሰባዊ ፍቅርና መተሳሰባቸው ነው። እነሱ ተጣልተው እንኳን መሃላቸው መግባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ያጋጠመኝ ምንም መጥፎ ነገር ስለሌለ በበኩሌ ለእኔ ሩህሩሆች፤ አዛኞችና የሰው መብት የሚያከብሩ አድርጌ ነው የምገልጻቸው።

የተለየ ችሎታ ቢኖረኝ መቀየር የምፈልገው ነገር ቢኖር፤ የእስራኤልና የዓለም የሰላም ዋስትና ለማረጋገጥ እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያንን አብረው በፍቅር የሚኖሩበት ሁኔታ ማመቻቸትና የሁለቱም ሃገራት እናቶች ለቅሶ ማቆም ነው። ለሃገራችን ኢትዮጵያም እንዲሁ።

እስራኤል ጸሓይ የምትወጣበት ሃገር ነው ስለሚባል በየቀኑ ጠዋት ከመኝታዬ መስኮት አጠገብ በመቆም ፀሐይ ስትወጣ የሚንቀሳቀሱትን መኪናዎች እያየሁ ወደ አምላኬ ጸሎቴን ማድረስ ነው። በህይወቴ ሙሉ ደስ የሚለኝ ነገር ነው። ይህ የዕለት ተዕለት ተግባር እንደ ቁርስ ልማዴ ሆኖ የቀረ ነገር ነው።

ከሃገሬ የሚናፍቀኝ ነገር ቢኖር የወላጆቼን ፍቅር፤ ከዛም ቀጥሎ መለያችን የሆኑ ባህሎቻችን የሚንጸባረቁባቸው ህዝባዊ በዓላት ናቸው። ባለሁበት ሃገር ላይ ሆኜም በደንብ አከብራቸዋለሁ።

የኢትዮጵያ ባህላዊ በየአይነቱ ምግብ

የፎቶው ባለመብት, አስመረት በርሄ

እኔ በብዛት የማዘወትረው ምግብ ቢኖር እንጀራ ነው። እስራኤል ውስጥ 'ምስራቅ' የሚባል የሃበሻ ምግብ ቤት ከፍቻለሁ። እኔ ደስ የሚለኝ እራሴ የሰራሁት ምግብ ነው። በተለይ ደግሞ ማህበራዊ የሚባለውና ከተለያዩ የጎመን ዘርና ስጋ የሚዘጋጅ ሆኖ በአንድ መአድ ብዙ ጣዕም ያላቸወን የምግብ ዓይነቶች የሚገኝበት ነው። ከእስራኤላውያን ደግሞ 'ስኒጸል' የሚባል የተለያዩ ቅመሞችን በመደባለቅ በዘይትና በዱቄት የዶሮ ስጋ በመጥብስ የሚዘጋጅ ሲሆን ይህ ምግብ ምርጫዬ ነው።

ወደ አገሬ ለመሄድ ሳስብ በማንኛውም ጊዜ ማረፍ የምፈልገውና የምመኘው ተወልጄ ያደግኩባት ጎንደር ስትሆን፤ ከዚያ ቀጥሎም ወላጆቼ የሚኖሩባት መቀለ ከተማ ናት።

Presentational grey line

ለአኤደን ሃይለሚካኤል እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦