ካለሁበት 43፡" የናይሮቢ ነዋሪ በጣም የዋህ ህዝብ ነው"

የፎቶው ባለመብት, Flimon Atakilti
ፊልሞን አታኽልቲ እባላለሁ። በናይሮቢ ኬንያ ነው የምኖረው። ናይሮቢ መኖር ከጀመርኩኝ ሶስት አመታት ሆኖኛል። ቤተሰቦቼ እዚህ ስለሚኖሩ ከነእሱ ጋር አብሮ ለመስራት ብዬ ነው ወደ ናይሮቢ የመጣሁት።
በናይሮቢ ከተማ ኢስሊ በሚባል አካባቢ በአንድ የኢትዯጵያ ሬስቶራንት ስራ አስኪያጅ ነኝ። የምኖረው ደግሞ ዌስትላንድ በሚባል ሰፈር ነው።
ኬንያን ከኢትዮጵያ ጋር ሳወዳድራት በተለይ ናይሮቢ በጣም በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች አረንጓዴ ከተማ ናት። የአየር ሁኔታዋም በጣም ደስ የሚልና ተስማሚ ነው።
በናይሮቢም ይሁን በአጠቃላይ በኬንያ ብዙ ተፈጥሯዊ የመዝናኛ ስፍራዎች አሉ። ይህ ደግሞ ለናይሮቢ ከተማ ተጨማሪ ውበት ፈጥሮላታል።
ኡጋሊ፣ ማራጓይ እና ጊቴሪ፡ በጣም ተወዳጅ የኬንያ ባህላዊ ምግቦች ናቸው። እኔ ግን የእንጀራ አፍቃሪ ስለሆንኩኝ፤ ለኬንያ እና ለሌሎች ሀገራት ምግቦች እስከዚህም ነኝ።

የፎቶው ባለመብት, FILMON ATAKLTI
በተለይ ደግሞ እንጀራ በሽሮ በጣም ነው የምወደው። አብዛኛውን ጊዜ እንጀራ ነው የምመገበው። ሃገሬ ሁሌም ይናፍቀኛል፤ በተለይ ደግሞ በመቐለ ከተማ የምትገኘው ያደግኩባት ጅብሩኽ ቀበሌ እጅግ ትናፍቀኛለች።
የሚገርመኝ ነገር ያደግኩበት አካባቢ አሁን ከምሰራበት ኢስሊ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ጋር በጣም ነው የሚመሳሰለው። ኢስሊ ማለት በናይሮቢ ትልቁ የንግድ ገበያ ነው። ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ነጋዴዎች ኢስሊን ሳይረግጡ፤ ሳይገበያዩ አይመለሱም። በተለይ ደግሞ የሶማሌያ ዜጎች።
በጦርነት ምክንያት ቀዬያቸውን ጥለው ለሚመጡ ስደተኛ ሶማልያውያን ሁለተኛ ቤታቸው እንደ ማለት ነች። በጣም በርካታ ሶማልያውያን በዚሁ አከባቢ ይገኛሉ።
ኢስሊ ትልቅ ገበያ ስለሆነ ሁሌም ግርግር አይለየዉም። ለዚህም ነው ካደግኩበት ጅብሩክ ጋር የሚመሳሰልብኝ።
ጅብሩክ በመቐለ ከተማ በሰፊው የሚታወቅና ግርግር የሚበዛበት ሰፈር ነው። እናም አብሮ አደጎቼን ሳገኛቸው ከጅብሩክ ወደ ጅብሩክ ነው መጣሁት እላቸዋለሁ።

የፎቶው ባለመብት, FILMON ATAKLTI
መጀመሪያ የመጣሁ አካባቢ የሰዎቹን ባህሪ መረዳት ከብዶኝ ትንሽ ተቸግሬ ነበር። ከዚያ ውጪ ግን እምብዛም ያስቸገረኝ ነገር አልነበረም።
በኬንያ አስቸጋሪ የሚባለው ወቅት ምርጫ ሲደርስ ፤ በተለይ የዛሬ ዓመት የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍፁም አልረሳውም። የኬንያ ፖለቲካ ከባድ ነው።
በምርጫ ወቅት ሁሉም የሚያሰፈልገውን ገዝቶ ቤቱን ዘግቶ ይቀመጣል። ምክንያቱም ንግድ ቤቶችም ዝግ ይሆናሉ።
በሰላማዊ ሰልፍ ወቅት የድጋፍም ይሁን የተቃውሞ ሰልፍ ከሚያደርጉ ሰዎች ውጪ ማንም ሰው ዝር አይልም። በተቀናቃኝ የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች ደጋፊዎች መካከል ደም ያፋሰሰ መጥፎ ሁኔታም ተፈጥሮ ያውቃል።

የፎቶው ባለመብት, FILMON ATAKLTI
በናይሮቢ ሁኔታው በጣም ከባድ ስለነበረ፤ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሞምባሳ በምትባለው የባህር ዳርቻ ከተማ ነው ያሳለፍኩት።
በተረፈ የናይሮቢ ነዋሪ በጣም የዋህ ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ከተማው የሚታወቅበት መጥፎ ልማድ አለ። እሱም ሙስና ነው። ናይሮቢን የመቀየር ዕድል ቢሰጠኝ፤ መጀመሪያ የማጠፋው በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሙስና ነበር።
ሃገሬ ኢትዮጵያ ሁሌም ከአይኔ አትጠፋም። ሁሌም ትናፍቀኛለች። አሁን በቅፅበት ራሴን የሆነ ቦታ መላክ ብችል፤ በሃገሬ በተለይ መቐለ ላይ ብገኝ ደስ ይለኛል።

ለላየን ፅጋብ እንደነገራት
የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦














