ትግራይ ፡ ምርጫው "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው" የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, HOUSE OF FEDERATION
በትግራይ ክልል በመጪው ረቡዕ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን በመሆኑ "እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌለው ነው" ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተገለጸ።
ምክር ቤቱ ዛሬ [ቅዳሜ] ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው ላይ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የምርጫ እንቅስቃሴን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ መወያየቱ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ፣ እንዲሁም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከአገሪቱ የበላይ ሕግ ጋር የሚቃረን በመሆኑ ተፈጻሚነት እንደሌለው ገልጿል።
በዚህም ምክር ቤቱ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ መሰረት በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው በማለት፣ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ "ሕገ ወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን መሆኑና በቀጣይም ምክር ቤቱ ለትግራይ ሕዝብ ካለው ውግንና አንጻር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳት እንዳይደረስ ችግሮችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል" ብሏል።
በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ምርጫ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ የለም በማለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰናቸው ይታወሳል።
በዚህም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም የትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫውን እንደሚያካሂድ አሳውቆ የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል።
ክልሉ ምርጫውን እንዲያስፈጽምለት ብሔራዊውን የምርጫ ቦርድ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ በተናጠል ምርጫውን ለማካሄድ የቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበሉ፤ የትግራይ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ የምርጫ ዝግጅት በማድረግ ድምጽ ለመስጠት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ምርጫን በሚመለከት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ተግባራዊ የማደረግ ግዴታ ቢኖርባቸውም፣ የትግራይ ክልል ከዚህ ውሳኔ ውጪ በሚቃረን ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ እንቅስቀሴ እያደረገ መሆኑን ለምክር ቤቱ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተጠቅሷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው በዚህ አስቸኳይ ስብሰባው ላይ የትግራይ ክልል መንግሥት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን መሆኑን፣ በዚህም ክልሉ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ ሕገ መንግሥቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ስልጣን እንደሚቃረን ገልጿል።
በዚህም የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ አስፈፃሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ አዋጅ የተላለፉ ውሳኔዎችና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት "እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው" በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ውሳኔ አስተላልፏል።
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ "የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ሕገ ወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው" መሆኑን ምክር ቤቱ አመልክቷል።
በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ 2̌.7 ሚሊዮን ሰዎች መመዝገባቸውና ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን መግለጹ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት የድምጽ መስጫው ቀን ረቡዕ ጳጉሜን 04/2012 ዓ.ም እንደሚሆን መገለጹ ይታወሳል።














