ኢትዮጵያ፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ምርጫ ላይ ከተወያየ ምን ሊወስን ይችላል?

ኮሮጆ

በአገሪቱ ካሉት ምክር ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከክልሎች የተወጣጡ ተወካዮች በፌደራል ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የሚመክርና ውሳኔ የሚያሳልፍ ሸንጎ ነው።

ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ቀርበውለት ከነበሩ ሕጋዊ ጉዳዮች ውጪ ከክልሎች አንጻር ጉልህ የሚባሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመውት አያውቁም።

በዚህ ዓመት ግን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የተከሰተው የምርጫ መራዘም የሕግ ትርጓሜን መጠየቁና የትግራይ ክልል በተናተል ምርጫውን ለማካሄድ መወሰኑ የምክር ቤቱን ትኩረት ከጠየቁ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ሆነዋል።

በመጪው ሳምንት ረቡዕ፤ ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም የሚካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ ሕግን የጣሰ ነው በሚል እንዳይካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልልን ቢያሳስብም፤ ክልሉ ምርጫውን ለማከናወን ጫፍ ደርሷል።

ምክር ቤቱ ጽፎት በነበረው ደብዳቤ ላይ የትግራይ ክልል የተሰጠውን ማሳሰቢያ ሳይቀበል ቀርቶ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ድርጊቱ የሚገፋ ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ" አስጠንቅቆ ነበር።

እነሆ አሁን ምርጫው ሊካሄድ አራት ቀናት ሲቀሩት ምንም እንኳን የስብሰባው አጀንዳ ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለዛሬ [ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012] አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባ እንደሆነ ከመግለጽ ውጪ ስለአጀንዳው ያለው ነገር ባይኖርም፤ የትግራይ ክልል ግን በዚህ ስብሰባ በክልሉ ውስጥ በሚካሄድ ምርጫ ላይ የሚሰጥን ውሳኔ እንደማይቀበለው ቀድሞ አሳውቋል።

በተጨማሪም ክልሉን የሚወክሉ ስምንት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አስቸኳይ ስብሰባ አጀንዳ ቀድሞ አልደረሰንም በሚል እንደማይሳተፉ ከማሳወቃቸው ባሻገር በፃፉት ደብዳቤ ላይ ይህ አካሄድ የምክር ቤቱን የአሠራርና ሥነ-ምግባር ደንብን የሚጥስ ነው ብለዋል።

በዚህም ሳቢያ አባላቱ ለውይይት የሚቀርበው አጀንዳው ካልደረሳቸው ስብሰባው ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገሩ አሳውቀዋል። የትግራይ ክልል በበኩሉ ምርጫውን ለማስተጓጎል የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ 'ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል' ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ይህንንም በተመለከተ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባላት የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ከሚደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በእነሱ በኩል ምን የሚሰጋቸው ነገር እንዳለ ተጠይቀው "እንደዚህ ዓይነት አሠራር ስላልተለመደ እንጂ፤ የቅዳሜው አስቸኳይ ስብሰባ አያሰጋንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም "የምክር ቤቱ አባላት የሚወያዩበትን አጀንዳ ሳያውቁ አይሄዱም። በማያውቁት አጀንዳ ለመሳተፍ ምን ሊያደርጉ ትሄዳሉ?" ሲሉ ጠይቀዋል።

"ስብሰባው ዲሞክራሲያዊ ክርክር የሚካሄድበትና የተለየ ሐሳብ የሚቀርብበት መድረክ ይሆናል ብለን አናምንም። ለዚህ ነው አንደሄድም ያሉት።"

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ካሳሁን በቀለ በበኩላቸው አስቸኳይ ስብሰባው በተያዘለት ቀን እንደሚካሄድ አረጋግጠው፤ ነገር ግን ለአባላት "የአስቸኳይ ጊዜ አጀንዳን ማሳወቅ ግዴታ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ተናግረዋል።

"አጀንዳው ምን እንደሆነ አልተገለፀም። በፊትም ቢሆን አይገለፀም። አባላቱ ወደ ስብሰባው ልክ ሲገቡ አጀንዳው ይበተናል። በአፈ-ጉባዔ የተጠራ ስብሰባ ስለሆነ እንደዚህ ነው የሚደረገው" ሲሉ ከዚህ በፊት የነበረውን ሁኔታ ይገልጻሉ። ባለሙያው አክለው "ይህ አሠራር ከዚህ በፊት የነበረ ነው፤ አዲስ ነገር አይደለም" ይላሉ።

አቶ ካሳሁን፤ የሥነ-ምግባር ደንቡ ላይ "አጀንዳውን ሊገልፅ ይችላል እንጂ፤ ይገደዳል አይልም" ሲሉ የትግራይ ክልል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ያነሱትን የደንብ ጥያቄ የግዴታ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህ አገላለጽም "ሊገልጽ ይችላል ማለት፤ ላይገልጽም ይችላል ማለት ነው በሌላ ቋንቋ።"

የስብሰባው ይዘት ምን ሊሆን ይችላል?

ብዙዎች የቅዳሜው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ከመጪው የትግራይ ክልል ምርጫ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ነዋሪነታቸውን ኔዘርላንድስ ያደረጉት የአስተዳደርና ዴሞክራዊ አማካሪ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር)፤ "ከባድ ውሳኔ ተላለፈ ከተባለ ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ ይችላል" ይላሉ።

ለመሆኑ ጣልቃ መግባት ማለት ምን ማለት ነው?

"እንግዲህ ከባድ የሚባለው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ። ከዚያ ባነሰ ግን ከበጀት ጋር የተገናኘ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል፤ አሊያም በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ሊጥል ይችላል።"

ምሁሩ ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች በሊሆኑ ይችላሉ መታየት እንዳለባቸው እንጂ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ያሳስባሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ 'ምርጫውን ህወሓት እስካሸነፈ ድረስ ችግር የለበንም' የሚል እንድምታ ያለው ንግግር አድርገዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ጦር ሠራዊቱ ጣልቃ ይገባል የሚል እምነት የለኝም" ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን በተመለከተ አደም (ዶ/ር) ሰፊ እንደሆነ አውስተው፤ ዋናው ጥያቄ ሕገ-መንግሥቱን ይንዳል አይንድም የሚለው እንደሆነ ይናገራሉ።

"ያደርገዋል አያደርገውም የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፤ ከመቻል አንፃር ግን ሊወስዳቸው የሚችሉ ብዙ እምርጃዎች አሉ።"

ፌዴሬሽን ምክር ቤት አንድን ግለሰብ ወንጀል ፈፅሟል ብሎ ባይልም ፌዴራል መንግሥቱ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ግን ሊያዝ ይችላሉ ይላሉ አደም (ዶ/ር)።

ፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ የትግራይ ክልል ውሳኔ ሕገ-መንግሥቱን አደጋ ላይ ጥሏል ብሎ ከፈረጀ ግለሰቦችን ሊከስ ይችላል ሲሉም አክለው ያስረዳሉ።

የትግራይ ክልል ተወካዮች ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ መቅረታቸው ውሳኔውን ያልተሟላ ሊያደርገው ቢችልም ሌሎች ተወካዮች በጠቅላላ ስብሰባው ላይ ከተገኙ ስምንቱ የትግራይ ክልል አባላት መቅረታቸው ምላተ ጉባኤውን (ኳረም) አያጓድለውም ይላሉ።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ የፌዴራል መንግሥቱ የማስፈፀም ግዴታ አለበት የሚሉት አማካሪው ፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነቱን አለመወጣቱ እንደ ወንጀል ሊታይ ይችላል ይላሉ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩበትና ቀደም ሲል መካሄድ የለበትም ብሎ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የጻፈበት በትግራይ ክልል ምርጫ ሊካሄድ ተቃረበበት ጊዜ የጠራው ስብሰባ አጀንዳው ባይገለጽም የምርጫው ጉዳይ አንዱ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ከ2.7 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪ ለመምረጥ መመዝገቡ በተነገረበት በትግራይ ክልል ውስጥ በተናጠል በሚካሄደው ምርጫ ላይ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነውን ህወሓትን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች በተፎካካሪነት ቀርበዋል።