የትግራይ ክልል የፌዴሬሸን ምክር ቤቱ ምርጫ አታካሂዱ የማለት ስልጣን እንደሌለው ጠቅሶ ምላሽ ሰጠ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በ21/11/2012 ለተጻፈው ደብዳቤ ትናንት ሰኞ እለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ምላሻቸውን በያዘው ደብዳቤ ላይም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ለክልሉ ምርጫ አታካሂዱ ብለው የመጻፍ ሥልጣን እንደሌላቸው አሳስበዋል።
አፈ ጉባኤው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ደብዳቤ ሕገመንግሥታዊ መሰረት የሌለው በማለት የገለፁት ሲሆን፣ "የሕገ መንግሥት መርሆዎችን የሚጥስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን የሚጻረር" በመሆኑ የትግራይ ክልል መንግሥትና ህዝብ እንደሚቃወሙት ገልፀዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ በፃፉት ደብዳቤ ላይ ምክር ቤቱ ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ እንዲራዘምና የምክር ቤቶችንና የፌደራል አስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና የስራ ዘመን ለማራዘም የወሰነውን ውሳኔ አለመቀበሉን በመጥቀስ የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓትን የሚጎዳ አካሄድ መሆኑን ገልጿል።
አክለውም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ ስነምግባር ህግ ማውጣቱ፣ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙና የምርጫ ሂደት መጀመሩ "ኢ ህገመንግስታዊ ነው" ካለ በኋላ፣ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ጣልቃ እንደሚገባ ገልጧል።
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት አፈጉባኤ በበኩላቸው ደብዳቤው የተጻፈው የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በሌለበት እና ክልሉ ምርጫ ይራዘምልኝ ብሎ ባልጠየቀበት ሁኔታ እንደሆነም በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ክልሉ የምርጫ ሕግ የማውጣት፣ ምርጫ ኮሚሽን የማቋቋም እና ምርጫ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳለው የጠቀሱት አፈ ጉባኤው፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ፌደራል መንግሥት በክልሉ ሕገ መንግሥታዊ መብት ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ እና በዚሁ ጣልቃ ገብነት ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ እነሱው ናቸው በማለት አስጠንቅቀዋል።
"የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚያካሄደው ምርጫ ኃላፊነትን መወጣት እንጂ ከፍላጎት የሚመነጭ አይደለም" ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ውሳኔውም የክልሉ መንግሥት ውሳኔ በክልሉ ህገመንግሥት መሰረት የተመሰረተ ነው ብለዋል።
ህገ መንግሥቱ በየአምስት አመቱ ምርጫ እንዲደረግ ያስገድዳል በማለትም ምርጫ ማካሄድ ለህገመንግሥታዊ ስርዓቱ ዋስትና መስጠትና ኃላፊነትን መወጣት ያመለክታል እንጂ ለህገመንግሥቱ አደጋ ሊሆን አይችልም በማለት ደብዳቤው አስፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ ደብዳቤው ህገመንግሥቱን የሚጥስና ህጋዊ ውጤትም ሊያስከትል አይችልም በማለት በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል ብሏል።
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫ እንዲደረግ በምክር ቤት መወሰኑ፣ የምርጫ ስነምግባር ህግ ማውጣቱ፣ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙንና የምርጫ ሂደት መጀመሩ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 13፣ 39 እና 52 መሰረት ለህገመንግሥቱ ስርአት ያለውን ታማኝነትና ተገዢነት ያሳያል ይላል ደብዳቤው።
ፌዴሬሽኑ በህገመንግሥት ትርጓሜ ሰበብ ምርጫ ለማራዘም ያሳለፈውን ውሳኔ ኢህገመንግሥታዊ በማለትም፣ የክልሉ ምክር ቤት ምርጫ ለማራዘም ምንም አይነት ህገመንግሥታዊ ሥልጣን የለውም በማለት ክልሉም የጣሰው ነገር የለም ሲል አስተባብሏል።
አፈጉባኤው አክለውም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ክልሎች ምርጫ ይራዘምልኝ ብለው ያቀረቡት ጥያቄ እንደሌለ በመጥቀስ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ባልቀረበለት ጥያቄ "ውሳኔ መስጠትና ማስፈፀም አይችልም" ሲሉ ገልፀዋል።
አፈ ጉባኤው የአገሪቱ ሕገመንግሥት አንቀጽ 9(3)ን በመጥቀስ መንግሥት የሚመሰረተው በምርጫ መሆኑን ካስረዱ በኋላ፣ ይህ አንቀጽ በክልሉ ህገመንግስትም "ገዢ አስገዳጅና የማይጣስ" መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በህገመንግሥቱ አንቀጽ 56 እና 73 አንድ ፓርቲ ስልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ አብላጫ ድምጽ ካገኘ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ ህገመንግስት አንቀጽ ውጪ ስልጣን መያዝ ህገወጥ መሆኑን በማስቀመጥ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በምርጫ የራሱን መንግሥት ለማቋቋም መወሰኑ ህገመንግስታዊ ነው ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገመንግሥታዊ ክፍተትን በህገመንግሥት ትርጉም ለመሙላት፣ ያሉት ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል ስልጣንና 6ኛው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ትርጉም መስጠቱ፣ "በሂደቱም በውጤቱም ህገ መንግሥቱን የሚጥስ" በመሆኑ የትግራይ ክልል እንደማይቀበለው በጊዜው መወሰኑን አስታውሰዋል።
ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ በአንቀጽ 8 (2) (3)፣ 9(3)፣ 38፣ 56፣ 73 መሰረት ኢ ህገመንግሥታዊ ነው በማለት፣ በክልል መንግሥትና በፌደራል መንግሥት ደረጃ ያለውን ዜጎች አስተዳደራቸውን የማደራጀት፣ የማስተዳደር ስልጣን አሳጥቷል ሲሉ ገልፀውታል።
አክለውም ህገ መንግሥታዊ ቀውስ ፈጥሯል ብለዋል። የመንግሥትንም ስልጣን ኢ ህገመንግሥታዊ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።















