ለአደጋ የተጋለጡ ሦስት የትግራይ ቅርሶች

ትግራይ በጥንታዊ ቅርሶች የታደለች ብትሆንም ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አላገኘችም በሚል ብዙ ቅሬታዎች ይሰማሉ። ለዚህም ምክንያቱ በአግባቡ የማስተዋወቅ ሥራ አለመሠራቱ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህ ባሻገርም አንዳንድ የትግራይ ቅርሶች ተገቢ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ። አደጋ ከተጋረጠባቸው ጥንታዊ ቅርሶች መካከል ውቕሮ ክልተኣውላዕሎ ያሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።
እንዳ አብርሃ ወአጽብሃ
ከአለት ተወቅረው ከተሠሩ ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስትያናት አንዱ እንዳ ኣብርሃ ወኣጽብሃ ነው።
ይህ ጥንታዊ ህንፃ ከውቅሮ ከተማ በስተምዕራብ በ17 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በአራተኛው ክፍለ ዘመን ሁለት ታዋቂ የአክሱም ነገስታት (አብርሃ እና አፅበሃ) ማስታወሻ እንዲሆን በስማቸው እንዳሠሩት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ቤተክርስትያኑ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋርጠውበታል።
የቤተክርስትያኑ ጥንታዊ ስዕላት በተባይ ተበልተው አደጋ ውስጥ ወድቀዋል። ስዕላቱደብዝዘዋል፤ እየጠፉም ነው። በስተደቡብ የሚገኘው የህንፃው አካል በመሰነጣጠቁበሚያሰጋ ሁኔታ ይገኛል።
የህንፃው ውስጣዊ ክፍልና ላይኛው ጣሪያም ተቃጥሎና ጨልሞ ይታያል። ይህ ደግሞ በዘመነ ዮዲት ጉዲት የደረሰ ጉዳት እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ለዚህም እሰከአሁን የተደረገለት ጥገና የለም።
በተለይም በህንፃው መግብያ በር ላይ የሚገኝ 'ዓምደወርቅ' ተብሎ የሚጠራ እና ከአቅሙ በላይ ተሸክሞ የሚገኝ ምሰሶ አስቸኳይ ጥገና እንደሚያስፈልገው ያለበት ይዞታ ይመሰክራል። ይህ ምሰሶ በህንፃው ከሚገኙ 42 ምሰሶዎች አንዱ ሲሆን፡ በዮዲት ጉዲት ጉዳት ደርሶበት በእንጨት የተጠገነ ነው።

ይህ ጥንታዊ ህንፃ 'ሳንድስቶን' ከሚባል የመፈረካከስ ባህሪ ካለው አለት የተሰራ በመሆኑ ከግዜ ወደ ግዜ የማርጀት ባህሪ እየታየበት ነው፤ በተለይም አንዳንድ የህንፃው አስደናቂ ምሰሶዎች እንዳይቆረጡ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ቄስ ተኽላይ አጽበሃ የቤተክርስትያኑ ቄሰ ገበዝ ሲሆኑ ቤተክርስትያኑ ከጥዋቱ 3 ሰአት እስከ 12 ሰአት ክፍት እንደሆነና በውጭ ቱሪስቶች በብዛት የሚታይ እንደሚጎበኝ ገልፀውልናል። ቢሆንም ግን ከትልቅ እንጨት ተቀርፆ የተሰራው ጥንታዊው ትልቁ የቤተክርስትያኑ በር ጭምር ለአደጋ ተጋልጧል።
ከቢቢሲ ባልደረቦች ጋር ተጉዘው ቤተ ክርስትያኑ ላይ ላይ ስለተጋረጠው አደጋ ማብራርያ የሰጡንን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርሶች ጥበቃ ከፍተኛ ኃላፊ አቶ ጎይተኦም ዕቡይ ቅርሶቹን መጠበቅ የማን ኃላፊነት ነው? ስንል ጠየቅናቸው ነበር።
ቅርሶቹን የመጠገን ኃላፊነት የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እንደሆነና ይህንንም በተደጋጋሚ እንዳሳወቁዋቸው ይገልፃሉ። በአስቸኳይ ጥገና ካልተደረገም አደጋው ወደ ከፋ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችልም ያሳስባሉ።

እንዳ ጨርቆስ ዉቕሮ
ጨርቆስ ውቕሮም ከውቕሮ-ገርዓልታ አብያተክርስትያናት አንዱ ሲሆን ከውቕሮ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ዓዲግራት ከተማ መውጫ በስተግራ ይገኛል።
ይህ ቤተክርስትያንም በአብርሃ ወአፅበሃ እንደተሰራ ይነገራል። ሶስት ቤተመቅደሶች ፣ ሶስት በሮች እና ሶስት መስቀሎች እንዲኖረው ተደርጎ እንደተሰራ ሊቃውንት ይናገራሉ።
ህንፃው ጥንታውያን ከሆኑ ቅርሶች አንዱ ቢሆንም እንዴት ሆንክ የሚለው ያለ አይመስልም። የቤተክርስትያኑ ዋነኛው ክፍል የሆነው ቤተመቅደስ በተለይም በክረምት ግዜ ዝናብ ስለሚገባበት ለከባድ አደጋ ተዳርጓል።
በቤተክርስትያኑ ቅጥር ያገኘናቸው አባ ገብረሚካኤል በየነ ስለ ቤተክርስትያኑ ጥንታዊነት ያወጉን ሲሆን "ይሁን እንጂ በአስቸኳይ ጥገና ያስፈልገዋል። ክረምት ላይ ወደ ቤተመቅደሱ ዝናብ እየገባበት ተቸግረናል" አሉን። በቤተመቅደሱ ትልቅ በርሚል በማስቀመጥ የሚገባውን ውሃ እንደሚያቁሩት እና አንዳንድ ግዜም ታቦቱን ከቦታው ለማንቀሳቀስ እንደሚገደዱ በሃዘኔታ ገልፀዋል።
ከማህሌት አልፈን ወደ ቤተመቅደሱ ውስጥ መግባት ስለማንችል አጋጠመ የተባለውን አደጋ ማየት ባንችልም ከዛ ውጪ ባለው የህንፃው አካል የደረሰውን ጉዳት በማየት ግን ስለሁኔታው መመስከር ከባድ አይደለም።

ከቤተክርስትያኑ ጣርያ ላይ ወጥተን ከህንፃው በላይ የተለያዩ አለስፈላጊ ተክሎች እና አረሞች በቅለውበት የቤተከርስትያኑ አለቃ ሲያርሟቸው መመልከት ችለናል። ከፍተኛ የአባቶች ጥበብ ያረፈበት ጥንታዊ ህንፃ በእንክብካቤ እና ተገቢ ጥገና እጦት ምክንያት እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ደርሶ መመልከት ልብ የሚሰብር ነገር ነው።
ከአሁን በፊት የባህል እና ቱረዝም ቢሮ በስስ አለት (ቃፀላ) እና ስሚንቶ በማድረግ ከላይ ክፍተቱን ለመድፈን ቢሞክሩ እንኳን ወደ ውስጥ የሚገባው ውሃ መንበረ ታቦቱን ማበላሸቱን እንዳላቆመ የቅርስ ጥበቃ ባለሞያው አቶ ጎይተኦም ዕቡይ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በህንፃው ጥንታዊ ጣርያም ጉዳት እየደረሰ ነው። ጉዳቱ ከአብርሃ ወኣፅብሃ ቤተክትርስትያን ሲነፃፀር ነዋሪዎች እና የቤተክርስትያኑ ተገልጋዮች በቀላሉ ሊከላከሉት የሚችሉት አደጋ የነበረ ቢሆንም ይህ ባለመደረጉ አሁን ለከፋ ደረጃ ደርሷል።
"ህብረተሰቡን በማስተማር መከላከል ይቻል ነበር። ወጪው ትንሽ ነው፤ እየደረሰ ያለውን አደጋ ግን ከባድ ነው" ይላሉ።
የቤተክርስትያኑ ገበዝ እና ተገልጋዮቹ ግን አሁንም የሚመለከተው አካል አስቸኳይ እና ችግሩን ከስር መሰረቱ የሚፈታ ጥገና እንዲያደርግለት ይጠይቃሉ።
የአፄ ዮሃንስ ቤተ መንግሥት - አጉላዕ
ከምስራቃዊ ዞን ከክልተአውላዕሎ ወረዳ ሳንወጣ ብዙም ያልተነገረለት ግን ልዩ ታሪክ ያለው ስፍራ በአጉላዕ ከተማ ይገኛል።
ይህችን በማደግ ላይ የምትገኝ የአጉላዕ ከተማ ከበስተደቡብ ወደ ምእራብ የሚያልፍ እና ወደ 'ገረብ ግባ' የሚገባ አንድ ወንዝ ከመሻገራችን በፊት ከርቀት ስንመለከት አንድ እንደመፈራረስ ያለ ትልቅ ህንፃ ማስተዋል ቻልን።
ወደ አከባቢው ስንቀርብም የህንፃው ቅጥር ግቢ ፈራርሶ ኦና ሆኖ ይታያል። በደቡባዊ ትግራይ በአደጋ ላይ የሚገኘው በለስም በህንፃው ጣርያ ላይ በቅሎ እሱም ሌላ ችግር ሆኖ ይገኛል።
የንጉሰ ነገስት አፄ ዮሃንስ አራተኛ በመቐለ ከተማ የሚገኝ እና አሁን እንደ ሙዝየም ሁኖ እያገለገለ ካለው በፌደራል መንግስት ከሚተዳደር ትልቁ ቤተመንግስት ውጪ፡ ሌላ ቤተመንግስት እንዳላቸው ትንፍሽ ያለ ሚድያም ያለ አይመስልም።

በተለይም ከጥንት ጀምሮ በትግራይ እና በኤርትራ ለሚገኝ የቤት አሰራር ማሳያ የሆነው ይህ ቤተመንግሥት፡ በትግራይ መዲና መቐለ ከሚገኘው የንጉሱ ቤተመንግስት ቀድሞ እንደተሰራ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ንጉሰ ነገስት አፄ ዮሃንስ ይህን ቤተመንግስት ሲሰሩ ለትግራይና ዓፋር ያማከለ ስትራተጅይካዊ ቦታ አደርገው እንደመረጡት ምሁራን ይናገራሉ።
በህንፃው ቅጥር ግቢ ሰፊ ሜዳ ያለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እየታረሰ መሆኑን በአይናችን አየን። በመስመር ሲያርሱ (ክሓርሱ) ያገኘናቸው አንድ ገበሬ 'ምን እየሰሩ ነው? ስንላቸው በልበ ሙሉነት "ጤፍ እየዘራው" አሉን።
በቅጥር ግቢው በሬዎች ተፈትተው፣ ሞፈር እና ቀንበር አንሰራፍተው፣ ከብቶች እና የጋማ ከብቶች በግድግዳው እየተሻሹ ምግባቸውን ሲበሉም ተመለከትን።
ገና ወደ ቅጥር ግቢው ስንደርስ የፈራረሰው የቤተመንግስቱ የላይኛው አካል 'አድኑኝ፤ ብሎ የሚጮህ ይመስላል። የቤተመንግስቱ ውስጣዊ ክፍልም ቢሆን የተቆፋፈረ ነው።
በጣም ቢዘገይም ከአምና ጀምሮ፡ ቤተመንግስቱን ወደ ሙዝየም ለመቀየር እየተሞከረ መሆኑን የሚያሳዩ አንዳንድ መሳርያዎች ቦታው ላይ ይገኛሉ።

"ቤተመንግስቱ ቀደም ሲል አንደኛውን ፈርሶ ነበር ማለት ይቻላል፤ በኋላ ግን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥንታዊነቱን እና ቅርስነቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ጥገና እንዲደረግለት ተወሰነ" ይላሉ የቅርስ ጥበቃ ባለሞያ አቶ ጎይቶኦም።
ከዛም በመቀጠል የከተማዋ አስተዳደር እንዲረከበው እንደተደረገና ርክክቡን ተከትሎ ግን ወደ ልማት መግባት ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል።
"እንደ አንድ የቅርስ ባለሞያ ያሳዝነኛል። አንድ ህንፃ ቶሎ ወደ ልማት እንዲገባ ካልተደረገ ለአደጋ መጋለጡ ማይቀር ነው። ትልቅ ታሪክ ያለው ቦታን በመንከባከብ ለትውልድ የማስረከብ ስራ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ያሳያል" ይላሉ አቶ ጎይቶኦም።
ያናገርናቸው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ድግሞ ከአሁን በፊት ህንፃውን ለማፍረስ የሞከሩ አካላት እንደነበሩ ገልፀውልናል።
በአጠቃላይ ይህ በተወሰኑ አካባቢዎች የታዘብነው በጥንታዊ ቅርሶች እየደረሰ ያለ አደጋ እንጂ ከአክሱም ሐወልት ጀምሮ በክልሉ አደጋ ላይ የሚገኙ እና አስቸኳይ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ታላላቅ ቅርሶች መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።












