የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን ማን ነበሩ?

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተገደሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት ከአራት ወራት በፊት ነበር።
በወቅቱም በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ የተጣለባቸው ኃላፊነት "ከባድ፣የሚያስጨንቅና በውስብስብ ፈተናዎች የተሞላ..." ሲሉ ነበር የገለጹት።
ደቡብ ጎንደር ጋይንት ያደጉት ዶ/ር አምባቸው መኮነን ሲሳይ የ48 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ።
በልጅነታቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርቶችን አብልጠው ይወዱ እንደነበር የሚነገርላቸው ዶ/ር አምባቸው ሕልማቸው መምህር መሆን ነበር።
የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ትግሉን ከተቀላቀሉ ከ5 ዓመታት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በርቀት አጠናቀዋል።
የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ነው። የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በሚገኘው ኬዲአይ የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በቅድመ ምረቃም ሆነ በድኅረ ምረቃ ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ምጣኔ ሐብትን ነው።
ከኮሪያ ተመልሰው ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በምጣኔ ሐብት ዙርያ ከእንግሊዙ ኬንት ዩኒቨርስቲ ነው ያገኙት።
በበጀት እጥረት ምክንያት ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለማቋረጥ ጫና እንደነበረባቸው፤ ደኞቻቸው ገንዘብ በማዋጣት ጭምር ያግዟቸው እንደነበር ከዚህ ቀደም ካፒታል ለተሰኘው ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ዶ/ር አምባቸው ከትጥቅት ግሉ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። ዋናነት ከሚጠቀሱት መሀል በአማራ ክልል የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ለአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣የአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነቶች ይገኙባቸዋል።
በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኾነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል።ከዚያ በኋላም የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ሰርተዋል።
ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ለአጭር ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሕዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው እስከ ተሾሙበት ጊዜ ድረስም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ ሚኒስትር ኾነው አገልግለዋል።
ዶ/ር አምባቸው ከለውጡ በኋላ ለርዕሰ ብሔርነት ታጭተው እንደነበርና ሕዝቡም ሆነ ፓርቲያቸው በፖለቲካው ተሳትፏቸው እንዲቀጥሉ በመፈለጋቸው ሐሳባቸውን መቀየራቸው ሲነገር ነበር።















