የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ትናንት እና ዛሬ

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካና እንቅስቃሴ በስፋት ተስተውሏል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይም ብሔራቸው በሚመለከቱ ጉዳዮች ድምፃቸውን አሰምተዋል፣ በብሔር እርስ በርስ ተጋጭተዋል፤ በብሔር ተኮር ጥቃትም ሕይወታቸውን እስከማጣት ደርሰዋል።
ዘንድሮም ተማሪዎች ከክልላቸው ውጪ ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አንሄድም ብለው እንደነበርም አይረሳም። መጻሕፍትን ከሚሸከሙ እጆች ይልቅ በትር በዝቷል። እስክርቢቶን ለመጻፍያ ሳይሆን ሌላ ተማሪን ለመውጋት አገልግሎት ላይ ውሏል። ሲጠቃለል 'ዱላና ድንጋይ የትምህርት መሣሪያ ሆኑ' እየተባለ ነገሩ በምፀት ተነግሯል።
ወላጅ ልጆቹን በኩራት ሳይሆን በሥጋት ወደ ዩኒቨርሲቲ የላከበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ሥጋቱ አይሎባቸው ልጆቻቸውን በመጨረሻው ሰዓት ከትምህርት ገበታ ያስቀሩም ጥቂት እንደማይሆኑ መገመት ይቻላል።
"ዩኒቨርሲቲ ምኑን ዩኒቨርሲቲ ሆነ?"
በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ተሳታፊ የነበሩት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ36 ዓመታት በማስተማራቸውም የተማሪዎች ፖለቲካዊ ጥያቄንም ሆነ እሱን ተከትሎ የሚነሱ እንቅስቃሴዎችን ለመረዳት ቅርብ ናቸው።
ከሳቸው ጊዜ የ 'መሬት ላራሹ' የተማሪዎች ንቅናቄ አንፃር የቅርብ ዓመታቱም ኾነ የዛሬዎቹ የተማሪዎች ፖለቲካዊ ጥያቄና እንቅስቃሴዎች በብዙ መልኩ የተለዩ ናቸው ይላሉ።
ያኔ ተማሪው የሚያምፀው በሥርዓቱ፤ የሚቃወመውም ሥርዓቱን ነበር የሚሉት ዶ/ር የራስ ወርቅ በአንድ ዓላማ በአንድ ላይ መቆም የሳቸው ጊዜ የተማሪዎች ንቅናቄ መገለጫ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ያሁኑ ግን "ተማሪው በብሔር ተከፋፍሎ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ክፍፍሉ ከብሔርም ወርዶ ጎጥም ይደርሳል። ሃይማኖትም ሁሉ ይኖራል" በማለት ያነፃፅራሉ።
ባለፉት ዐሥርና እንደዚያ ዓመታት በዛሬዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄዎች ምክንያት የዩኒቨርሲቲ ቅጥሮች ውስጥ በሚገኙ ንብረቶች ላይ ውድመት ደርሷል።
እሳቸውና የሳቸው ጊዜ ተማሪዎች ደጅ ከፖሊስ ጋር ይጋጩ እንጂ የዩኒቨርሲቲ ቅጥር ላይ ጉዳት አያደርሱም ነበር። ዩኒቨርሲቲዎችን መደብደብ በጭራሽ የሚታሰብ ነገር እንዳልነበር የሚናገሩት ዶ/ር የራስ ወርቅ "ይልቅ ዩኒቨርሲቲው የንቅናቄው ካምፕና ምሽግ ነበር" ይላሉ።
ተማሪ በተማሪ የተደበደበበትና የተሳደደበትን የቅርብ ጊዜውን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭት በምሳሌነት በማንሳት የአሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ጥያቄ "ፀባዩም፣ ዓላማውም እንደገናም የትግል መሣሪያዎቹም ከኛ የተለዩ ናቸው" ይላሉ።
ቤተ መጻሕፍት ተቀምጦ የሚያነብ ተማሪ ከኋላዬ ተመታሁ ብሎ የሚሰጋ ከሆነ፣ በተማሪዎች መኝታ እርስ በርስ ተፈራርተው እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ከሆነ፣ ሴት ተማሪዎች እንደፈራለን እያሉ የሚሰጉ ከሆነ "ዩኒቨርሲቲ ምኑን ዩኒቨርሲቲ ሆነ?"ይላሉ ዶ/ር የራስወርቅ።
ዩኒቨርሲቲ የሚለው ቃል "ዩኒቨርሳል" (ትልቁ ዓለም) ከሚለው ቃል የመጣ፣ የአስተሳሰብ አድማስን የሚያጎለብት፣ ነገሮችን አስፍቶ የሚመለከት ቢሆንም ዛሬ ግን እንደ ብሔርና ሃይማኖት ያሉ ልዩነቶች አይለው የአገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ነባራዊ እውነታ ከዚህ በተቃራኒው መሆኑ አለመታደል እንደሆነ ይናገራሉ።
ከ"ዩኒቨርሳሊስት" ይልቅ ብሔር ብሔር በመባሉ ግን ተማሪው ላይ አይፈርዱም። ምክንያቱ ደግሞ ተማሪው የዛሬው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት ነፀብራቅ ነው ብለው ማመናቸው ነው።
እሳቸውና የሳቸው ዘመን ተማሪዎች አተያይና የተማሪዎች ንቅናቄም ከጊዜው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንፃር የተቃኘ ነበር። "ምናልባት በዚያ ጊዜ ስለዓለም አቀፋዊነት፣ ስለ ሆቺ ሚንና ቼጉቬራ ስናወራ የነበርነው እኛም የዚህ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብንሆን ከዛሬው ተማሪ የምንለይ አንሆንም ነበር" ይላሉ።
የተማሪ ጥያቄ ማንሳትም ሆነ ቁጭቱን መግለፅ የሚወገዝ ሳይሆን የሚመሰገን ነው የሚሉት ዶ/ር የራስወርቅ የአሁኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ አቀራረብና የእንቅስቃሴው ኢላማ ግን መስመር የሳተ በመሆኑ ሊቀየር ይገባል ባይ ናቸው።
"የያኔና የአሁኑን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ማነፃፀር በጣም ይከብዳል"
ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብዛት፣ ከአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች መለዋወጥ አንጻር ሁለቱን የተማሪ ትውልድ ማወዳደር እጅጉን ከባድ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳታፊ የነበሩትና ስለ ኢትዮጵያ አብዮት መጽሐፍ የጻፉት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ናቸው።
ለእነሱ በቀላሉ መቀራረብና መግባባት ብሎም በአንድ ርዕዮተ ዓለም መሰባሰብ ቀላል ነበር። ተማሪው የሚከተለው ማርክሲዝም ሌኒንዝምን እንደነበርም ፕሮፌሰር ገብሩ ያስታውሳሉ።
"ዋናው ዓላማችን በአፋጣኝ የኢትዮጵያን ዕድገት ማየት፣ ገበሬውና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የነበረው ሰፊው ሕዝብ ከዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ነበር የተሰባሰብነው፣ የታገልነው፣ የቆሰልነውና የሞትነውም" ይላሉ።
እንደ እሳቸው እምነት የብሔር ፌደራሊዝሙ ተማሪው ላይ ትልቅ ተፅእኖ አሳድሯል። በዚህም በሳቸው ጊዜ አሰባሳቢና አዋሃጅ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ግን ከፍተኛ ልዩነት የሚንፀባረቅባቸው ሆነዋል።
ባለፉት ዓመታት ኢህአዴግ ትምህርት ቤቶች ላይ የሠራው የፖለቲካ ሥራ (በተለይም ተማሪዎችን አባል ማድረግ) ያሳደረውን ተፅእኖም ይጠቅሳሉ።
አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም በዕድሜም ሆነ በብቃት ለእነሱ ዘመን ምሁራን ሳይሆን ለተማሪዎቻቸው የቀረቡ መሆንን ዶ/ር የራስወርቅና ፐሮፌሰር ገብሩ እንደ አንድ ችግር ጠቅሰዋል።
ፖለቲከኞችና ፅንፈኛ ብሔርተኞች ዩኒቨርሲቲዎችን የራሳቸው የጨዋታ ሜዳ ማድረጋቸውም ለፕሮፌሰር ገብሩ ከፍተኛ ችግር ነው።
የትምህርት ዝቅጠት እና የሥነ ሥርዓት ጉድለትም ሌላው እንደ ችግር ያነሱት ጉዳይ ነው።
ከጠቀሷቸው ምክንያቶች በመነሳት የሳቸውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ከዚህኛው ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው በማለት ይደመድማሉ።
እንደ ዶ/ር የራስወርቅ ሁሉ ፕሮፌሰር ገብሩም ለዛሬው ሁኔታና ምስቅልቅል እሳቸው 'የተበደሉ' በሚሏቸው የአሁኑ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ አይፈርዱም።
"ፖለቲካው ንግድ አልሆነም ነበር"
የ60ዎቹ ትውልድ ከአሁኑ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች እንደሚለይ ይናገራሉ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም።
የመጀመሪያው በሳቸው ጊዜ የነበረው የጋራ አጀንዳና የአንድነት ጉዞ ቀርቶ ጭራሹኑም ተማሪዎችን የሚያስማማ ነገር መጥፋቱ ነው።
"መሬት ላራሹና የብሔር እኩልነት የሁሉም አጀንዳ ነበር። ያኔ የብሔር ጥያቄ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ነበረውም" በማለት ያስታውሳሉ።
ሁለተኛውና ዋናው ልዩነት የሚሉት በሳቸው ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ወደ ድርጅቶች ይሄድ የነበረው ለትግል እንጂ የሆነ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት ያልነበር መሆኑን ነው። "ፖለቲካ እንደዛሬው ወደ ንግድነት አልተቀየረም ነበር ። ከመንግሥትም ሆነ ከማንም ለሚገኝ ትርፍ ሳይሆን ለዓላማ ነበር።"
በዩኒቨርሲቲዎች ብቻም ሳይሆን በመላ አገሪቱ ፖለቲካን ወደ ንግድ መለወጡ የኢህአዴግ ትልቁ ጥፋት እንደሆነም ይደመድማሉ ፕሮፌሰር መረራ።
የተወሰኑ መመሳሰሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ "ይነስም ይብዛ ይሄኛውም ተማሪ የራሱ አጀንዳ ይኖረዋል" ይላሉ።
እሳቸው እንደሚያስታውሱት የብሔር ጥያቄ በዚያ ጊዜም ተነስቷል። ኢትዮጵያዊ ማን ነው? የሚሉ ዓይነት ጥያቄዎችም መነሳት ጀምረው ነበር። ታዲያ የዛሬው ልዩ ነገር ምንድን ነው?
"መከፋፈሉ ያኔ የጀመረ ቢሆንም ዛሬ ብዙ የቻይና ግንቦች በዝተዋል" የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ የዛሬውና የሳቸው ጊዜ የብሔር ጥያቄ አረዳድም በጣም መለያየቱን ያስረዳሉ።
"ያኔ የተማሪን ልብ የሚስበው ሶሻሊዝም ነበር። ዛሬ ደግሞ የተማሪው ልብ ብሔር ላይ ነው"
አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደው፣ አብዮቱም አልፎ፣ የተማሪዎች ንቅናቄ ቦታውን በልዩነት ላይ ለተመሠረቱ ድርጅቶች መልቀቀ ሲጀምር የተፈጠረው ነገር ዛሬ ላይ አድርሶናል፤ በዚህም ልዩነቶች እየሰፉ ግጭቶችም እየበዙ መጥተዋል ሲሉ ይደመድማሉ።












