ዩኒቨርሲቲ ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ "ዩኒቨርሲቲዎች"

የፎቶው ባለመብት, Federal ministry of Education
በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደራጃ ቁጥራቸው ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ መካካል አስራ አንዱ በዚህ ዓመት ሥራ የጀመሩ አራተኛ ትውልድ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
ከዚህ ቀደም በነበሩት ዙሮች በተገነቡት ዩኒቨርሲቲዎችም የመሰረተ ልማት ችግር ቢኖርም፤ በአዲሶቹ ላይ ግን ይበረታል።
ግንባታቸው እንኳን ሳይጠናቀቅ፣ አጥር ሳይኖራቸው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና በአጠቃላይ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፈታኝ መሆናቸው እየተገለፀ ነው።
በቅርቡ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በሴት ተማሪዎች ላይ የመድፈር ሙከራ መደረጉ የቅርብ ጊዜ አንድ ማሳያ ነው።
ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም። በዚህ ዩኒቨርሲቲ የሚወሰንም አይደለም። የመሰረተ ልማት አለመሟላት የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን መማር ማስተማር ሂደት እያወከ ተማሪና አስተማሪዎችንም እየፈተነ ይገኛል።
መፀዳጃ የሌላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች
"ከተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ተነጥሎ፣ በጊዜያዊ መልክ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ ምሽት ላይ ተማሪዎች ወጥተው መፀዳጃ ቤት መጠቀም ይቸገራሉ። ስለዚህ ፖፖ የገዙ ተማሪዎች እንዳሉ አውቃለሁ" ያለን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ግቢ የመጀመሪያ ድግሪውን የተከታታለና አሁንም ሁለተኛ ድግሪውን በዚያው በመስራት ላይ የሚገኘው እያሱ አማረ ነው።
እሱ እንደሚለው መፀዳጃ ቤቶቹ ለሴቶችም ለወንዶችም አይመችም፣ ከንፅህና አንፃርም እጅግ ከደረጃ በታች ነው። ይህም ለተከታታይ ስድስትና ሰባት ዓመታት ሳይስተካከል አለ።
"የሚገርመው በተማሪዎች መመገቢያ ስፍራ ውሃ አይቀርብም ነበር" በማለት በመጀመሪያ ዲግሪው ወቅት የነበረውን ያስታውሳል።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ይተዳደር የነበረው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ራሱን ችሎ ትምህርት መስጠት የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነው። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዩኒቨርሲቲው መምህር በግቢው ያለው የውሃ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ይገልፃሉ።
"የውሃ እጥረት በመኖሩ ዩኒቨርሲቲው ውሃ የሚያከፋፍል ቦቴ መኪና ተከራይቶ በየተማሪዎቹ ማደሪያ ህንፃዎች ስር በተቀመጡ ትንንሽ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ይሞላሉ፤ ተማሪዎቹ ልብስ ለማጠብም ሆነ ለመተጣጠቢያ የሚጠቀሙት ከዚሁ ከተጠራቀመው ውሃ ነው" ይላሉ መምህሩ።
ተማሪዎቹ ለመጠጥ የሚጠቀሙት ይህንኑ ውሃ እንደሆነም ይገልፃሉ።
መቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ በዚህ ዓመት 1500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።
በዩኒቨርሲቲው በዕፅዋት ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ተማሪ የሆነችው ወጣት አበበች መስፍን ዩኒቨርሲቲው ገና አዲስ መሆኑን አጥርም እንደሌለው ትናገራለች።
በግቢው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ለመስራት ቁፋሮ በመኖሩ በጋ አቧራ፤ ዝናብ ሲዘንብ ጭቃ በመሆኑ ለመንቀሳቀስ እንደሚያስቸግርም ትገልፃለች።

የፎቶው ባለመብት, Mministry of Education
ይሁን እንጂ አካባቢው የውሃ እጥረት ባለመኖሩ የኒቨርሲቲውም ጋር እንዲህ ዓይነት ችግር የለም ያለችው ተማሪዋ፤ ወደፊት ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉ ተስፋ አድርጋለች።
ልማር ብሎ ለአደጋ መጋለጥ
እያሱ ችግሩ የውሃና የመፀዳጃ ብቻ አይደለም ሲል መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ያነሳል።
አዲስ የተገነቡ ህንፃዎችን ውሃ ለማጠጣት በሚል፤ ውሃ ለማጠራቀም በጥልቅ ተቆፍረው የተተው ጉድጓዶች በዝናብ ውሃ ተሞልተውና በሐረግ ተሸፍነው ከዕይታ በመሰወራቸው አንድ ተማሪ ወደ ቤተ-መፃህፍት ደርሶ ሲመለስ ጉድጓዱ ውስጥ እንደገባና በብዙ ፍለጋ በጉድጓዱ ውስጥ ሞቶ እንደተገኘ ያስታውሳል።
እያሱ እንደሚያስታውሰው ተማሪው የመጀመሪያ ድግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ ነበር።
ይሄ ችግር ሙሉ በሙሉ ባለመፈታቱ ዛሬም ተማሪዎች ተቆፍረው በተተዉ ጉድጓዶች ውስጥ እየገቡ ለመሰበር አደጋ እየተዳረጉ እንደሆነ ይገልፃል።
በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ሃላፊ ሆኑት አቶ ብርሃን ሽመልስም የተማሪዎች ሻይ ክበብ እንኳ እንደሌለ ይናገራሉ።
ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ገና ግንባታው ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ወደፊት ችግሮች እየተፈቱ ይሄዳሉ የሚል ዕምነት አላቸው።
ያነጋገርናቸው የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርም በበኩላቸው የመሰረተ ልማት አገልግሎት ብቻም ሳይሆን ችግሩ የመማር ማስተማሩንም ሂደት ያስተጓጎለ እንደሆነ ይናገራሉ።
የተሟላ ቤተ-ሙከራ አለመኖር፣ የበይነ-መረብ አገልግሎት በቀላሉ አለማግኘታቸው፤ ለተማሪዎች መስጠት ያለባቸውን የተግባር ሥራዎች እንዳይሰጡ እንቅፋት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።
ይህ ደግሞ የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ግልፅ መሆኑን ይናገራሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ
"በአራተኛ ትውልድ ወይም በዚህ ዓመት ሥራ የጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ እንደመሆናቸው ሁሉም መሰረተ ልማት መቶ በመቶ ተሟልቶላቸዋል ማለት አይቻልም" ይላሉ በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ወ/ሮ ሃረጓ ማሞ።
ዋና ዋና የሚባሉት ነገሮች የተሟሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ፤ ባልተሟሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሟላ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በቅርቡ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በሚማሩ ሴት ተማሪዎች ላይ ያጋጠመው የመድፈር ሙከራ በመጥቀስ ጥያቄ የቀረበላቸው ሃላፊዋ "በአካባቢው የውሃ ችግር በመኖሩና ዩኒቨርሲቲውም አንዱ የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ ለውሃ ችግር ተጋልጧል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በቀጣይ እንዲስተካከሉ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችም በቂ የሆነ ግንዛቤ ይዘዋል" በማለት መልስ ሰጥተዋል።
እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተናግዷቸው ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አዳዲስ የተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ምቹ እስከሚሆኑ መጠበቅ ያልተቻለው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ቀርቦላችው
"ዩኒቨርሲቲውን ሥራ ለማስጀመር የተቀበልናቸው ተማሪዎች ናቸው፤ እነርሱም ቢሆኑ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ራሳቸውን ችለው በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ ነው የሚገኙት። ጉድለት ያለባቸውንም ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው" ሲሉ ይገልፃሉ።
ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርገው አካል ዩኒቨርሲቲዎቹን መርቆ ለመክፈት እንጂ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ነገሮችን የመከታተል ጉድለት እንዳለ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
ሃላፊዋ ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እንዳለው ዓመቱን ሙሉ የዩኒቨርሲቲዎችንም የመመልከት ሥራ እንደሚከናወን ይናገራሉ።
በምልከታው መሰረትም የጎደሉ ነገሮችን የማሟላት እርምጃዎችም እንደሚወሰዱ ለማስረገጥ ይሞክራሉ።
መሬት ላይ ያለው ነገር በርግጥም ይህ ከሆነ ከዓመት ዓመት ተማሪዎች በማይፈቱ ችግሮች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከባድ ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።












