ትግራይ፡ በትግራይ በምርጫ ሥርዓትና በምክር ቤት መቀመጫ ብዛቱ ላይ ለውጥ ተደረገ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው በክልሉ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የምርጫ ሥርዓት ለውጥና በምክር ቤቱ ውስጥ ባለው የመቀመጫ ብዛት ላይ ጭማሪ አደረገ።
ምክር ቤቱ በስብሰባው የክልሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48ን በማሻሻል ነው የምክር ቤቱ የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምርና እስካሁን የነበረውን የምርጫ ሥርዓት ያሻሻለው።
በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት በክልሉ ከዚህ በፊት የነበረውን የአብላጫ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት በመቀየር በ"ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት" እንዲተካ በማድረግ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ መቀመጫዎች ውስጥ 80 በመቶዎቹ የአብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት የሚያዙ ሲሆን፣ 20 በመቶው ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ለተወዳዳሪ ድርጅቶች እንደሚከፋፈል ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም አስካሁን ድረስ በክልሉ ምክር ቤት የነበረው የመቀመጫ ብዛት 152 ሲሆን፤ በማሻሻያው መሰረት አሁን 38 መቀመጫዎች ተጨምረው ወደ 190 ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ዛሬ በጸደቀው የመቀመጫ ድልድል መሰረት የተጨመሩት 38 መቀመጫዎች ወይም ከአጠቃላዩ የምክር ቤት መቀመጫ 20 በመቶው በምርጫ የተወዳደሩ ድርጅቶች ከተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የሚያገኙት ድምጽ ተሰብስቦ ባገኙት የድምጽ ብዛት አንጻር የሚከፋፈሉት ይሆናል ተብሏል።
ምክር ቤቱ እንዳለው እነዚህ ድርጅቶች የተመደቡትን መቀመጫዎች ለመከፋፈል የሚችሉት ቀድመው የተወካዮቻቸውን ስም ለምርጫ ኮሚሽኑ ማገስባት ሲችሉ መሆኑም ተገልጿል።
እነዚህ መቀመጫዎች ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ የተተዉ በመሆናቸው የግል ተወዳዳሪዎች ከ38ቱ መቀመጫዎች ምንም ድርሻ እንደማይኖራቸው ተነግሯል።
በአገሪቱ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ቢደረግም የትግራይ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለየ ምርጫውን በተናጠል ለማካሄድ ወስኖ እየተዘጋጀ እንደሆነ ይታወቃል።














