ኤርትራ ፡ ኤርትራዊያንና የሌላ አገር ዜጎች ለምን በጀልባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ያቋርጣሉ?

በትንሸዬ ጀልባ ላይ ያሉ ብዙ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በዩናይትድ ኪንግደም ኬንት አውራጃ ሙቀቱ አይሏል። የተረጋጋው የባሕር ወጀብ በንፋስ ወዲያ ወዲህ ይላጋል፤ በዝምታ።

ኤርትራዊያንና ሌሎች አምባገነን መሪዎቻቸው ፊታቸውን ያዞሩባቸው ዜጎች በተመሳሳይ ጸጥታውን ተገን አድርገው ይሻገራሉ፤ በዝምታ። እንግሊዝ ባሕር ሰርጥን. . . ።

የእንግሊዝ ባሕር ሰርጥ፤ ዩናይትድ ኪንግደምንና ፈረንሳይን የሚያገናኘው አጭሩ የባሕር ላይ አቋራጭ ነው።

ይህ ስፍራ ወደ እንግሊዝ ለመሻገርና አዲስ ኑሮ ለመጀመር ላቆበቆቡ ስደተኞች ተመራጩ ነው። ለምን?

አንደኛ ይህ የባሕር ሰርጥ በርካታ የመርከቦች እንቅስቃሴ ያለበት በመሆኑ ትኩረት አይስብም። ሁለተኛ አየሩ ምቹ ነው። አየሩ ምቹ ሲሆን የባሕሩ ወጀብ ዝግ ያለ ነው።

የኬንት ነዋሪዎች ጠዋት ሲነሱ ባሕር ዳርቻው አካባቢ ቤሳቤስቲ የሌላት እርጉዝ ሴት ያገኛሉ። ከወጀቡ ተገፍታ የወጣች ሴት።

መሽቶ በነጋ ቁጥር ስደተኞችን የሚተፋው ይህ ባሕር በርካታ በጦርነትና በድህነት ከሚታመሱ አገሮች የሚነሱ ስደተኞችን አስተናግዷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚሁ መንገድ ከአውሮፓ አገራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተው አዲስ የጥገኝነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

ቁጥሮች በራሳቸው ብዙ ይናገሩ ይሆናል።

በዚህ ዓመት ብቻ 4ሺህ ሰዎች በሦስት መቶ ትንንሽ ጀልባዎች ቁጢጥ ብለው ተሻግረዋል።

ባለፈው ሐሙስ ዕለት ብቻ 235 ሰዎች ተመዝግበው እንግሊዛዊያን ጉድ እያሉ ነበር። እንዲህ ዓይነት ቁጥር በአንድ ቀን ተመዝግቦ አያውቅም።

በነገራችሁ ላይ የፈንሳይ የባሕር ተቆጣጣሪዎች አደን ስለሚወጡና ጀልባዎችን በአካባቢው ስለሚያስቆሙ እንጂ ከዚህ ቁጥር እጥፍ የሆኑ በርካታ ጀልባዎች በየቀኑ ኬንት በደረሱ ነበር።

ብዙዎቹ ጀልባዎች በጣም ትንንሽና ለአደጋ የሚያጋልጡ ሆነው በዚያ ላይ በሕጻናትና አቅመ ደካሞች ይታጨቃሉ።

በዚያ ላይ ያ መስመር እጅግ ብዙ መርከቦች የሚመላለሱበትና አደገኛ ነው።

በዓለም አቀፍ የባሕርና የውቅያኖስ ሕግ በባሕር ላይ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ያለ ሰዎችን ከአደጋ መታደግ ለአገሮች ግዴታ ነው።

ባለፈው የፈንጆች ዓመት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገቡ የውጭ ዜጎች (ለሥራና ለትምህርት) 677ሺህ ናቸው።

49 ሺህ ሰዎች ደግሞ የጥገኝነት ጥያቄ ማመልከቻ አስገብተዋል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ በእንግሊዝ የባሕር ሰርጥ (English Channel) በጀልባ ተሳፍረው የመጡት አንድ እጅ ቢሆኑ ነው።

ነገር ግን የጥገኝነት ጥያቄ ከዩናይትድ ኪንግደም ይልቅ በሌሎች የአውሮፓ አገራት ይበዛል።

ለምሳሌ ያለፈውን ዓመት አሐዝ ብቻ ብንመለከት 165ሺህ 600 ሰዎች በጀርመን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበዋል።

በፈረንሳይ ደግሞ 129ሺህ የተለያዩ አገራት ዜጎች አስጠጉን ብለዋል። በስፔን ደግሞ 118ሺህ ሰዎች ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከዚህ አንጻር ዩናይትድ ኪንግደም ጥብቅ ድንበር፣ ጥብቅ የጥገኝነት ፖሊሲ እንዳላት መገመት ይቻላል።

አንድ ሰው የእንግሊዝን ምድር ሳይረግጥ የጥገኝነት ጥያቄ ለማሳካት በጣም ፈታኝ ይሆንበታል። ስለዚህ በተገኘው አጋጣሚ ወደ አገሪቱ ለመግባት ይሞከራል።

ቀደም ሲል ስደተኞች በከባድ መኪናና በጭነቶች ውስጥ ተደብቀው ነበር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገቡት።

ባለፈው ዓመት 39 ቬትናማዊያን እንደ ማቀዝቀዣ በሚያገለግል ከባድ ተሸከርካሪ ውስጥ ታጉረው ወደ አገሪቱ ሲገቡ እዚያው መኪናው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ደንጋጤን ፈጠረ።

ክስተቱን ተከትሎ ጥብቅ ቁጥጥር ተጀመረ።

በከባድ መኪና ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መግባት እጅግ አደገኛ እየሆነ ሲመጣ ትንንሽ ጀልባዎች አማራጭ ሆኑ።

ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በጀልባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገቡት ውስጥ ወደመጡበት የአውሮፓ አገር የተመለሱት 155 ሰዎች ብቻ ናቸው።

በቀጣይ 600 የሚሆኑትን በተመሳሳይ ወደመጡበት ለመመለስ ሐሳብ አለ።

ዩናይትድ ኪንግደምን የሚናፍቁት የየትኞቹ አገራት ዜጎች ናቸው?

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ብቻ 200 ሰዎች በጀልባ ገብተዋል፤ ኬንት፣ ዩናይትድ ኪንግደም።

ስደተኞቹ በብዛት የምን አገር ዜጎች ናቸው? ብለን ከጠየቅን የሚከተለውን መልስ እናገኛለን።

የመን፤ ሰነዓ ውስጥ በዝናብ ፈረሰ ህንጻ ፍርስራሽን የሚያጸዱ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የመን፤ ሰነዓ ውስጥ በዝናብ ፈረሰ ህንጻ ፍርስራሽን የሚያጸዱ ሠራተኞች

1ኛ፡የመን

ከዓለም እጅግ ካጡ ከነጡ ድሀ አገራት ተርታ የምትመደበው የመን በእርስ በርስ ጦርነት ደቅቃለች።

ጦርነት በአጥንቷ አስቀርቷታል።

በደቡባዊ የአረቢያ ሰላጤ የምትገኘው የመን ላለፉት 10 ዓመታት ሳኡዲ አረቢያና አጋሮቿ ያላዘነቡባት የቦምብ ዓይነት የለም። በዚህ ዘመን በዓለም ላይ እንደ የመን ሕጻናት በጦርነት ያለቀበት ስፍራ የለም።

ለተወሰነ ጊዜ ረገብ ብሎ የነበረው ጦርነት ድጋሚ እያገረሸ ይመስላል። ኢራን በአንድ በኩል የሁውቲ ሚሊሻን ደግፋ፣ ሳኡዲና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሌላ በኩል የሱኒ መንግሥትን ደግፈው በየመን ላይ ጡንቻቸውን እየፈተኑ ይገኛሉ።

ይህ ጦርነት ዜጎቿ አገር ጥለው እንዲጠፉ አድርጓል። የሚላስ የሚቀመስ ቀርቶ ቦምብ የማይረብሸው ንጹህ እንቅልፍ ካላገኙ እንዴት በዚያች አገር ሊጸኑ ይችላሉ?

የኤርትራ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤርትራና ኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት በድንበር ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል

2ኛ፡ኤርትራ

ቀይ ባሕርን ተደግፋ ከሳኡዲ አረቢያ ማዶ፣ ከኢትዮጵያ በስተሰሜን የምትገኘው ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኤርትራ በአፍሪካ እጅግ ድሀ ከሚባሉ አገራት ተርታ ትሰለፋለች።

ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ ኤርትራዊያን ከገዛ አገራቸው ኤርትራ ውጭ ነው የሚኖሩት። ይህ አሐዝ የዚያችን ትንሽ አገር ጠቅላላ ሕዝብ አንድ አምስተኛ ያክላል።

የኤርትራ ዜጎች አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱበት አንዱ ምክንያት የግዴታ የውትድርና አገልግሎትን በመሸሽ ነው። ማንኛውም ዕድሜው ከ18 እስከ 50 ዓመት ያለ ዜጋ በማንኛውም ጊዜ ተጠርቶ ለዓመታት በወታደርነት እንዲያገለግል ሊገደድ ይችላል።

የኤርትራ ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ደቋል። ለዚህም ምክንያቱ ለዓመታት ቆይቶ የነበረው የድንበር ፍጥጫና የአምባገነን አገዛዝ መኖር ናቸው።

ከነጻነት ጀምሮ ለሦስት አስርታት ለሚጠጋ ጊዜ አገሪቱን በፈርጣማ ክንዳቸው እየመሩ ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህ ሁሉ ቁምስቅል ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የጣለባት ማዕቀብ ኤርትራን አፍረክርኳት ቆይቷል።

አሁን ለአገሪቱ እንደ ተስፋ የሚነገርላት ነገር ቢኖር ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት በመጀመሯ ምጣኔ ሃብቷ ሊነቃቃ ይችላል የሚል ነው።

የኤርትራ ዜጎች በብዙ ቁጥር በዩናይትድ ኪንግደም ይኖራሉ። በአሁን የበጋ ወቅትም ወደዚያው የሚያመሩት ከየመኖች ቀጥሎ ኤርትራዊያን ናቸው።

ቻድ ነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻድ ነዳጅ ማስተላለፊያ ትቦ

3ኛ፡ ቻድ

ቻድ የባሕር በር የላትም። ወደ ሰሜን በሚጠጋው የማዕከላዊ አፍሪካ ክፍል ነው የምትገኘው። በረሃማ አገር ናት።

እዚያም እንደ ኤርትራ ሁሉ መንግሥትን መቃወም አይፈቀድም።

ቻድ ወርቅና ዩራኒየም አላት። በቅርቡም ከነዳጅ ላኪ አገሮች ተርታ ተመድባለች። ሆኖም ከፈረንሳይ ነጻነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት እንደታመሰች አለች።

የእርስ በእርስ ጦርነቱ አረብ-ሙስሊሞች ነን በሚሉ ሰሜናዊያንና ክርስቲያን በሆኑ ደቡቦች መካከል ነው።

ቻድ የረባ አውራ ጎዳና እንኳን የላትም። መሠረተ ልማቷ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በርካታ ሕጻናት በቻድ በበሽታ ይሞታሉ። ድህነት ጥላውን እንዳጠላ ነው። ረሀብ ቶሎ ቶሎ ይጎበኛታል።

የዚህች አገር ሕዝቦች ከየመንና ከኤርትራ ቀጥሎ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በጋውን እየጠበቁ በጀልባ ይጎርፋሉ።

ግብጽ ኢኮኖሚዋ በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግብጽ ኢኮኖሚዋ በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ነው

4ኛ፡ ግብጽ

85 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ግብጽ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉልበተኛ አገር ናት።

የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ግብጽ የስዊዝ ካናል ባለቤትና ከአፍሪካ ወደ እስያ የሚወስደው መስመር ላይ መተላለፊያ ሆና ታገለግላለች። ስዊዝ ካናል በዓለም በጣም ብዙ መርከቦችን በማስተላለፍ የሚታወቅ ወደብ ነው።

ፖለቲካዋ ስክነት የለውም። በተለይም የፀደይ አብዮትን ተከትሎ አብዱልፈታህ አልሲሲ ከመጡ ወዲህ የተቃውሞ ድምጾች ታፍነዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት በግብጽ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ሆኗል። አሁን ደግሞ ወረርሽኙ በቱሪዝም ላይ የተንጠለጠለውን ኢኮኖሚዋን ክፉኛ ተፈታትኖታል።

ይህም በመሆኑ ሕዝቦቿ ከአውሮፓ ከተሞች እየተነሱ በዩናይትድ ኪንግደም አዲስ ሕይወት ለመመስረት ይታትራሉ።

በአባይ ወንዝ ላይ በጀልባ የምትጓዝ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጦርነትና ተቃውሞ ባለፉት ዓመታት ሱዳንን ጎድቷታል

5ኛ፡ ሱዳን

ሱዳን በአፍሪካ አህጉር ትልቅ የቆዳ ስፋት ካላቸው አገር አንዷ ናት። ለወራት የዘለቀ ተቃውሞ አምባገነኑን አልበሽርን ከሥልጣን አስወግዷል። ሱዳን ለዘመናት ከጦርነት አልወጣችም።

አንድ ነጥብ ተኩል ሚሊዮን ሕዝቧን የበላው የደቡብና የሰሜን ሱዳን ጦርነት በዚህ ረገድ ይጠቀሳል። በምዕራብ ሱዳን ዳርፉር ግዛት 2 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል።

እንደ አውሮፓዊያኑ በ2011 አገሪቱ ለሁለት ተከፈለች፤ ደቡብ ሱዳን አዲስ አገር ሆና ወጣች።

መንግሥት ነጻ ሚዲያዎችን እንደልብ አያሰራም። የመናገር ነጻነት የተገደበ ነው። አማካይ የመኖርያ ዕድሜ 63 ነው።

የአገሪቱ ዜጎች ስደት ሊያስመርጣቸው የሚችል ብዙ ምክንያት አላቸው።

ኢራቃዊያን ባግዳድ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢራቃዊያን ባግዳድ ውስጥ

6ኛ፡ ኢራቅ

ኢራቅ ታላቅ አገር ነበረች። የአሜሪካኖች ወረራ ከአገርነት ወደ የጦርነት አውድማ ቀየራት። ከሳዳም ወዲህ ኢራቅ ቁምስቅሏን አይታለች።

37 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ኢራቅ ከቡሽ ወረራ በኋላ አገሪቱ በሐይማኖቶች ተከፋፍላ ሰላም ርቋታል። ሰላም አለመኖሩ ምጣኔ ሀብቷ እንዳያንሰራራ አድርጎታል እንጂ ሀብታም መሆን የምትችል አገር ናት።

በዓለም የነዳጅ ክምችት 2ኛ መሆኗ ሳይዘነጋ ዜጎቿ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት ብዙ ይቆፍራሉ።

የእንሊዝ መንግሥት በቀጣይ ምን አስቧል?

አሁን በጀልባ ወደ ግዛቱ የሚያቋርጡ ስደተኞች ቁጥር እያሳሰበው ያለው መንግሥት፤ ፈረንሳይ ጀልባዎቹ ከመነሳታቸው በፊት ቁጥጥር እንድታደርግ፣ ጉዞ ከጀመሩ በኋላም ጉዟቸውን እንድታስተጓጉል እየጠየቀ ነው።

በእንግሊዝ ፓርላማ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ልዩ ኮሚቴ ሁለቱ አገራት ትብብራቸው ምን እንደሚመስልና ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ እየመከረ ነው።

መንግሥትን የሚተቹ ወገኖች እንደሚሉት ሁለቱ አገራት ስደተኞችን የሚያቀባብሉ ደላሎችን አይቀጡ ቅጣት እንዲቀጡ ማድረግ አለበት ይላሉ።

ለስደተኞች መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ድርጅቶች ደግሞ መንግሥት ደንበሮቹን ቢከፍትና የጥገኝነት ጥያቄን በአግባቡ ማየትና መቀበል ቢጀምር በሕገ ወጥ ጀልባ ጉዞ የባሕር ድንበርን በማቋረጥ የድሀ ዜጎች ነፍስ አይቆረጥም ነበር ይላሉ።