እስራኤል 2,000 ቤተ እስራኤላውያንን ለመቀበል ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል 2,000 ቤተ እስራኤላውያን ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቀደች። ይህም ለዓሠርታት ለዘለቀው ጥያቄያቸው ምላሽ የሰጠ ውሳኔ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ እስራኤል ለመጓዝ ለዓመታት ሲጠባበቁ ከነበሩ ወደ 8,000 የሚጠጉ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መካከል ናቸው።
ቤተ እስራኤላውያኑ፤ እስራኤል የመኖር መብት ጥያቄያቸው ለዓመታት ሲነሳ የነበረ ነው። ለአብዛኞቹ አይሁዳውያን የእስራኤል ዜግነት የማግኘት መብት የሚሰጠው ሂደት ለነሱ አይሠራም።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980ዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚሥጥራዊ ተልዕኮ ወደ እስራኤል ተወስደዋል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ያኔ ከሄዱት ቤተ እስራኤላውያን ጋር የደም ትስስር አላቸው።
ሆኖም ግን ከዛ በኋላ ወደ እስራኤል መሄድ የተፈቀደላቸው ጥቂቶቹ ብቻ ሲሆኑ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኙ ማቆያዎች ይገኛሉ።
ማኅበረሰቡ ከቤተ እስራኤላውያን የዘር ግንድ የሚመዘዝ ሲሆን፤ በ1880ዎቹ አውሮፓውያን ሚሽነሪዎች ክርስቲያን አድርገዋቸው ነበር።
ከዛ ግን ወደ አይሁድ እምነት ተመልሰዋል። ሆኖም የእስራኤል የአገር ውስጥ ሚንስትር እንደ ሙሉ የአይሁድ እምነት ተከታይ እውቅና አልሰጣቸውም።
እስራኤል እንዲሄዱ መፈቀድ አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው እስራኤል በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ሳይቀር መከፋፈል ፈጥሯል።
አንዳንድ ቤተ እስራኤላውያን፤ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች እስራኤል የመኖር መብት አላቸው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይሁዳዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው በማለት ሐሳቡን አይቀበሉትም።
በቅርቡ በስደተኞች ጉዳይ ሚንስትርነት የተሾሙት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ኒና ታማኖ-ሻታ በበኩላቸው፤ 2,000 ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል እንዲገቡ በመፈቀዱ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በትዊተር ገጻቸው "በጣም ደስ ብሎኛል" ሲሉም ጽፈዋል።
ሚንስትሯ እስከ ቀጣዩ ዓመት ማገባደጃ ድረስ ቤተ እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለመውሰድ ቃል ገብተው ነበር።
ቤተ እስራኤላውያን መጀመሪያ ላይ ወደ እስራኤል የተወሰዱት ከሱዳን የስደተኞች ማቆያዎች ነበር።
በ1980ዎቹ መባቻ ላይ የእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ ጉዟቸውን እንዳመቻቸም ይታወሳል። ውሳኔውን ያስተላለፉት የያኔው ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።
በቀጣይም በ1991 በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል ተወስደዋል።
ቤተ እስራኤላውያኑ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ጋር ተዋህደው ለመኖር ያሚያደርጉት ጥረት ቀላል አይደለም። ብዙዎቹ ሥራ አጥ ሲሆኑ፤ መድልዎም ይደርስባቸዋል።












