ቲፋኒ ሃዲሽ፡ ጥቁርነትና ይሁዳዊነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዘር ግንዷ ከኤርትራና ከአሜሪካ የሚመዘዘው ተዋናይቷ ቲፋኒ ሃዲሽ በአይሁዳውያን እምነት ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ባት ሚትዝቫህን አክብራለች።
ባት ሚትዝቫህ የሚባለው አንዲት ታዳጊ አስራ ሁለት አመት ሲሞላትና፤ በእምነቱም ዘንድ ነፍስ ማወቋ ሲረጋገጥ፤ መፅሀፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱትን የሃይማኖቱን ህግጋትም ሆነ ትእዛዝ መፈፀም የሚያስችላትን እድሜ ማረጋገጥ የምትችልበትን ቀን የሚከበርበት ነው።
ለቲፋኒ ሃዲሽ ግን በአርባኛ አመቷ ሲሆን ይህንን እለት ያከበረችው፤ በኔትፍሊክስም ለእይታ በበቃው ብላክ ሚትዝፋህ (የጥቁር ሚትዝፋህ) የይሁዳዊነት መሰረቷን ስታከብር የሚያሳይ ነው።
ጉዞዋ ብዙ ጥቁር አይሁዳውያን ትልቅ ከሆኑ በኋላ ዘራቸው ከዛ መሆኑን ሲያውቁ የሚያደርጉትን እንዲሁም የአይሁድ እምነትን በትልቅነታቸው ሲቀበሉ የሚያደርጉትን ጉዞ ያንፀባርቃል።
ቲፋኒ ኤርትራዊና አይሁዳዊ አባቷን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘችው በ27 አመቷ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ወዲያው ይሁዳዊነቷን አልተቀበለችም፤ የዲኤንኤ ምርመራ ማድረጓን ተከትሎ ነው ስረ መሰረቷን የተቀበለችው።
የእብራይስጥ ቋንቋን እንዲሁም መፅሃፈ ቶራህን ማጥናት ጀመረች፤ ባት ሚትዝቫህን ያከበረችበትንም ምክንያት ስትናገር አፍሪካዊነቷን እንዲሁም ይሁዳዊነት መሰረት ለማክበር ነው።
ቲፋኒ ይህንን ማድረጓም ብዙ አፍሪካዊ አሜሪካውያን የዘር ግንዳቸውን እንዲፈልጉ ሊያበረታታቸው እንዲሁም ሊያነሳሳቸው እንደሚችል ነው።
የአይሁዳዊነት መንገዶች
በተለምዶ ይሁዳዊነት በዘር የሚተላለፍ፤ አንድ ሰው አያቱ ወይም ቤተሰቡ የዘር ግንድ ከዛ የሚመዘዝ ከሆነ ከእምነቱ ጋር ብዙዎች ግንኙነት ይፈጥራሉ። አንዳንዶች ደግሞ የዘር ግንዳቸው ከዛ የሚመዘዝ ባይሆንም ይሁዳዊነትን በራስ በመነሳሳት የሚቀበሉ አሉ።
በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የአይሁዳውያንን ቁጥር ማወቅ ከባድ እንደሆነ የብላክ ጂውስ ኦፍ አፍሪካ መፅሃፍ ደራሲ ዶ/ር ኤዲት ብሩደር ይናገራሉ።
"በአፍሪካ ውስጥ ከሌላው አለም ጋር አንድ አይነት የሆነ ይሁዳዊነት አይደለም፤ በተፃራሪው የሚቀያየር ነው" ብለዋል።

በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የይሁዲውያን የህዝብ ቁጥር ያለው በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ብዙዎቹም ቤተሰቦቻቸው ከአውሮፓ የተሰደዱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያንንም በሌላው አለም ማንነታቸው ሳይታወቅ ለዘመናት የኖሩ ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 1975 በእስራኤል መንግሥት እውቅና ተሰጥቷቸዋል። አብዛኛዎቹ ወደ አርባ ሺ የሚገመቱት በጎርጎሳውያኑ 1970-1991 ባለው ጊዜ በምስጢራዊ ዘመቻዎች ወደ እስራኤል እንዲመጡ ተደርገዋል።
አሁንም ቢሆን በአህጉሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ጥቁር ይሁዳውያን የሚገኙ ሲሆን፤ አንዳንዶቹም ማህበረሰቦች በተለያየ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል።
እንደ ቲፋኒ ያሉት የዘር ግንዳቸውን በዲኤንኤ ማረጋገጥ የቻሉ ሲሆን እንደ ሚካኤል ሎሞቴ ያሉት ደግሞ የይሁዲነት ማንነታቸውን በሌላ መንገድ ነው ማወቅ የቻሉት።
በጎርጎሳውያኑ 1960ዎቹ ነው በእንግሊዝ ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኘው የሁል ከተማ ያደገው፤ ሚካኤል ሎሞቴ ስለ ጉዞው ለቢቢሲ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Michael Lomotey
ከነጭ እንግሊዛዊ እናትና ከጥቁር ጋናዊ አባት የተወለደው ሚካኤል ሁለቱም ወላጆቹ ይሁዳውያን ናቸው።
ስለ ቤተሰቦቹ ማንነትም ሆነ መሰረት ጎርመስ እስኪል ድረስ የሚያውቀው ታሪክ አልነበረም።
"ቤታቸው ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት ከጋና መሰረቱ የተመዘዙ ባህሎች ይመስሉኝ ነበር" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።
አባቱ ጭንቅላታቸው ላይ ትንሽ ቆብ ያደርጉ ነበር፤ በእብራይስጥ ቋንቋም ያወሩ ነበር።
"ስለ ይሁዳውያንም ሆነ አይሁዶች ምንም ተብለን አናውቅም" ብሏል።
ወላጆቹ ስለ ይሁዳዊነት ምንም ብለው ለምን እንደማያውቁ ባይረዳም ከቤት ሲወጣ በአስራ ስምንት አመቱ መፅሀፈ ቶራህን አባቱ ሰጥተውታል።
"መፅሀፉን በጥልቀት ሳነበውና ስረዳው የሁሉም ነገር መነሻ እንደሆነ ተረዳሁኝ፤ ብርሃን እንደተፈነጠቀልኝ ነው የተሰማኝ" ብሏል።
በዛን ወቅትም ነው የማንነቱን መሰረት ፍለጋ የገባው፤ በዚህም ፍለጋ ላላ ካሉ በጣም አጥባቂ ይሁዲዎች አጋጥመውታል።

ሚካኤል በሰሜናዊ ለንደን በሚገኝ አጥባቂ ባልሆነ ምኩራብም ያመልካል።
ወደዛም ያመራው ከተለያዩ ዘር፣ ባህል የመጡ ለምሳሌም ጥቁር፣ እስያውያን፣ ነጮች ይሁዳውያን መኖራቸው ነው።
ሚካኤል የቲፋኒን ይሁዳዊ ማንነቷን የመቀበል ዜና ሲሰማ ደስታ ተሰምቶታል።
"ሰዎች በማንነታቸውና በመሰረታቸው ኩራት እንዲሰማቸው ልናበረታታቸው ይገባል" የሚለው ሚካኤል እንዲህ በአደባባይ ስለ ማንነቷም መናገሯ ኩራት እንደፈጠረበት አልደበቀም።
ይሁዳዊ መሆን
ይሁዳዊ ማንነታቸውን በተለያየ መንገድ ፈልገው የሚያረጋግጡ ሰዎች አሉ።
ማንነትንም ሆነ እምነትን መቀየር ግላዊና ምስጢራዊ እንደመሆኑ መጠን ብዙዎችም ይህንኑ ጉዟቸውን ይፋ አያደርጉም።
ከነዚህም መካከል ቤዛ አበበ አንዷ ናት
ከሃይማኖት ገለል ካሉ ቤተሰቦች የተወለደችው ቤዛ ይሁዳዊነትን መጀመሪያ ያወቀችው በቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ ነው። እምነቱን ማጥናት፤ እብራይስጥ ቋንቋን መማር ነበረባት። ለስድስት ወራት ያህልም ፈታኝ የሚባለውን ጥናት በፅናት አድርጋለች።

"በአጠቃላይ አራት አመታት ያህል ወስዶብኛል። ትንሽ የተወሳሰበ ሂደት ነበረው፤ ነገር ግን ተወጥቸዋለሁ። ቁርጠኛነቴንም ያዩ ሰዎች ረድተውኛል" ብላለች።
ብዙዎችም እንዲህ በአስቸጋሪ ሁኔታ ለምን ማለፍ እንደፈለገች ሲጠይቋት ቤዛም በምላሹ " ነፍስ የምትፈጠረው ይሁዳዊ ሆና ነው። ብትቀየርም በሆነ መንገድ እዚህ መንገድ ላይ ብትደርስ፤ ራስን የማግኘት ጉዞ ነው" በማለት ታስረዳለች።
በሌላ ቋንቋ ነፍስ ማን እንደሆነች፤ጉዞዋ የት እንደሆነች ታውቃለች፤ ያንን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
በዓለም ላይ የሚገኙ የይሁዳውያን እምነት ተከታዮች የቲፋኒ ሐዲሽ ባት ሚትዝፋህን ማክበር ዜና በደስታ ነው የተቀበሉት " የምስራች" መልዕክቶችም በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ተዥጎድጉደዋል።
ቤዛም በዚህ ዜና ከተደሰቱት መካከል ናት " በዚህ መንገድ ማንነቷን መቀበሏ በጣም ነው ያስደሰተኝ" ብላለች።












