ኮሮናቫይረስ፡ ማኅበራዊ ርቀት ጉንፋንን ከነጭራሹ ያጠፋው ይሆን?

የኮሮናቫይረስን የሚቃወም እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2014 በብራዚል አማዞን ጫካ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት ጎሳዎች የማይረሳ ዓመት ነው። ስማቸው ሳፓናዋ የሚባል ሲሆን ከጎረቤት አገር ፔሩ የመጡ ሌሎች ጎሳዎች መንደራቸውን ወርረውባቸው ነበር።

ይህን ወረራ የሸሹት የዚህ ጎሳ አባላት ከዚህ በፊት አይተውት ከማያውቁት ስልጣኔ ጋር ተዋወቁ። ሰዎቹ ከዚህ በፊት ከሌሎች ሰዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አድርገው የማያውቁ ሲሆን እኛ የምናውቀውን ዘመናዊ ዓለም ከነጭራሹ ስለመኖሩም አያውቁም ነበር።

ከጥቅጥቁ ጫካ ሲወጡ ያገኟቸው ሰዎችም ከሚመለከተው የብራዚል መንግስት ያቋቋመው ድርጅት ጋር አገናኟቸው። እዛው ሆነውም ሶስት ሳምንታትን አሳለፉ።

እነዚህ ሰዎች አብዛኛዎቻችንን የሚያሰቃዩን እንደ ጉንፋን የመሳሰሉ በሽታዎችን አያውቋቸውም ነበር። ነገር ግን በቀናት ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ አብዛኛዎቹ ጤናቸው ተቃወሰ። ጉንፋን እና ትኩሳት ያሰቃያቸው ጀመር። ደግነቱ በተደረገላቸው ህክምና አንዳቸውም ሕይወታቸው ሳያልፍ መዳን ቻሉ።

በወቅቱ የያዛቸው በሽታ ተላላፊ ስለነበር እራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡና አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ተደርገው ነበር። በዚህም ምክንያት በሳምንታት ውስጥ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ዋለ። የጉንፋን ወረርሽኙም ጉዳት ሳያስከትል ጠፋ።

ስለዚህ ጉንፋንን የማያውቁ ማህበረሰቦች አሉ ማለት የተቀረው ዓለምም ጉንፋንን አይንህን ለአፈር ብሎ ማጥፋት ይችል ይሆን ወይ የሚለውን ጥያቄ እንዲነሳ ያስገድዳል።

በሳለፍነው ጥር ወር ላይ አውስትራሊያ ውስጥ 6962 ሰዎች በድንገት በጉንፋን መያዛቸው ተሰምቶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ኮቪድ-19 ቻይና ውስጥ ብቻ የተወሰነ ከባድ ጉንፋን ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ ወረርሽኙ መላው ዓለምን አዳርሶ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ነበር። በዚህም ምክንያት በርካታ አገራት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል አገዱ፣ የአውሮፕላን በረራዎችን አቋረጡ፣ ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ ማስተላለፍ ጀመሩ።

የፈረንጆቹ በጋ ወቅት ሲመጣ ጉንፋን የተለመደ ነበር። ነገር ግን እንደ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ ባሉ አገራት የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቃቸውና ሌሎች ጥንቃቄዎችን ማድረግ በመጀመራቸው በጉንፋን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።

መርፌና ብልቃጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው ከዚህ በፊት ከነበሩት የጉንፋን ወቅቶች አንጻር ዘንድሮ ከነጭራሹ የለም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ነገሮች ተቀይረዋል።

ኒው ዚላንድም ቢሆን ዘንድሮ በጉንፋን የተጠቃ ምንም ዜጋ አላገኘሁም ያለች ሲሆን ባለፈው ዓመት ግን የጉንፋን ምርምራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት ጉንፋን መያዛቸው ተረጋግጦ ነበር።

በርካቶችም ይህ የሆነው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን በመጠበቃቸውና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግ በመጀመራቸው ነው ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በመላው ዓለም ይመዘገቡ የነበሩ የጉንፋን አይነቶች ጠፍተዋል። 'ፍሉማርት' በመባል የሚታወቀው የጉንፋን መከታተያ ስርአት በመስከረም ወር በመላው ዓለም መመዝገብ የቻለው 12 በላብራቶሪ የተረጋገጡ በጉንፋን የተያዙ ሰዎችን ብቻ ነው።

ከቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ሳራ ኮቤይ እንደሚሉት ደግሞ ምናልባት በጉንፋን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የቀነሰው ሰዎች ወደ ሆስፒታል ለመምጣት ፍርሀት ስላለባቸውና ከኮሮናቫይረስ ጋር እንዳይመሳሰልባቸው ስለሚሰጉ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ይህ ማለት በጉንፋን የሚያዙ ሰዎች ከዚህ በፊት ከነበረው አልቀነስም ማለት አይደለም ይላሉ። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በጉንፋን ይያዙ ነበር፤ አሁን ግን ከነጭራሹ የሚያዙ ሰዎችን ማግኘት ከባድ ሆኗል።

ስለዚህ ያለው ብቸኛ መልስ ሊሆን የሚችለው አካላዊ ርቀት በመጠበቃችንና ንጽህናችንን በአግባቡ እየተከታተልን ስለምንጠብቅ ነው ብለዋል የበሽታ ስርጭት ባለሙያዋ ሳራ።

ጉንፋንከነጭራሹከሰውልጆችሕይወትየመጥፋትዕድልይኖረውይሆን?

የሰው ልጅ እድሜ ልኩን ከጉንፋን ጋር አልኖረም። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ ጉንፋን ለመጀመሪያ ጊዜ የያዘው ምናልባትም ከ10 ሺ ዓመታት በፊት ከሚያረባቸው የወፍ ዝርያዎች እንደሆነ ይገመታል።

ጉንፋንን ሁሌም አስቸጋሪ የሚያደርገው እራሱን ስለሚቀያይር እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይነገራሉ። አንድ ሰው በአንድ የጉንፋን ቫይረስ ከተያዘ በኋላ በሽታ የመከላከል ስርአቱን ስለሚገነባ መልሶ አይዘውም። ነገር ግን ቫይረሱ እራሱን ትንሽ ቀይሮ ሲመጣ እንደ አዲስ ሰውነታችንን ያጠቃል።

ለዚህም ነው በዓለማችን ላይ ከሚኖሩት 7 ቢሊየን በላይ ሰዎች መካከል በየዓመቱ 10 በመቶ የሚሆኑት ጉንፋን የሚጠቁት።

ምናልባት የሰው ልጅ አሁን እየሄደበት ባለው አካሄድ ቀጥሎ ጉንፋንን ማጥፋት ቢችል እንኳን አንድ ሰው ከሆነ ጊዜ በኋላ በጉንፋን መያዙ አይቀርም። ይህ ደግሞ ቫይረሱ በቀላሉ ዓለምን እንዲያዳርስ ይረዳዋል።

አሜሪካ ውስጥ የተነሳው ጉንፋን አፍሪካ ሲደርስ ሌላ አይነት ቫይረስ ይሆናል። ከአውስትራሊያ የመጣው ቫይረስ ቻይና ሲደርስ እራሱን ቀያይሮ አዲስ አይነት ባህሪ ይዞ ይመጣል።

ለዚህም ነው ቫይረሱ በቀላሉ እራሱን መቀያየር የሚችለውና እንዳይጠፋ የሚሆነው።

ምንም እንኳን ጉንፋን እንዲህ በቀላሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠፋ ነገር ባይሆንም አሁን ያለው ወረርሽኝ የቫይረሱን እድገትና ስርጭት በእጅጉ እንደገታው ግን ማስተዋል ከባድ አይደለም።

ኮሮና
Banner