ኮሮናቫይረስ፡ አፍሪካ በወረርሽኙ ሳቢያ ከተጎዳው ምጣኔ ሐብት ለማገገም 1.2 ትሪሊየን ዶላር ያስፈልጋታል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፍሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካጋጣት የኢኮኖሚ ውድቀት ለማገገም እንዲሁም የጤና ወጪ 1.2 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም [አይኤምኤፍ] አስታወቀ።
ገንዘቡ ያስፈልጋታል የተባለው ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት መሆኑ ተገልጿል።
የተቋሙ ዳሬክተር ክርስታሊና ጆርጂቫ እንዳሉት ዓለም አፍሪካ ከገባችበት ቀውስ እንድታገግም ለመደገፍ ዓለም ብዙ መስራት አለበት ብለዋል።
በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ያነሰ ነው፤ ነገር ግን የዓለም ባንክ በወረርሽኙ ሳቢያ ተጨማሪ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካዊያን ለከፋ ድህነት የመጋለጥ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል።
በወረርሽኙ ሳቢያ የሥራ እድሎች በመታጠፋቸው እና የቤተሰብ ገቢ በ12 በመቶ በመቀነሱ የደረሰው የኢኮኖሚ ተፅእኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ እየታየ የነበረውን ጠንካራ እድገት እየቀለበሰው መሆኑን የገንዘብ ተቋሙ ዳሬክተር በበይነ መረብ በነበራቸው የተቋሙ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ችግሩንም ለማቃለል በርካታ አፍሪካ አገራት መንግሥታት ከልማት እቅዳቸው 2.5 በመቶ ያስወጣቸውን ፖሊሲዎች አስተዋውቀዋል።
አይኤም ኤፍ የአፍሪካ አገራት ከደረሰባቸው ተፅዕኖ እንዲያገግሙ 26 ቢሊዮን ዶላር የለገሰ ቢሆንም፤ የግል አበዳሪዎች እና በሌሎች አገራት ድጋፍ ቢኖርም፤ አሁንም ግን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት አለ ብለዋል።
"አንዳንድ አገራት ከብድር አግልግሎትና ተጨማሪ የማህበራዊና ጤና ወጪዎች መካከል እንዲመርጡ የሚያስገድዳቸውን የዕዳ ጫናዎች እየተጋፈጡ ነው" ብለዋል ኃላፊዋ።
ይህንን ችግር ለመፍታትም ተበዳሪዎች ብድራቸውን የሚከፍሉበት ጊዜ እንዲራዘም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ለብድር የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ ማቅረብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ወደ 37 ሺህ የሚጠጉት ሕይወታቸውን አልፏል።












